በአዲስ አበባ በአንድ ግሮሰሪ በረንዳ የፈነዳ ቦምብ በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa police
በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ግሮሰሪ በረንዳ ላይ ሐሙስ ኅዳር 29/2015 ዓ.ም. የፈነዳ ቦምብ በሰባት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ማድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ፍንዳታው የደረሰው ምሽቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ዊኬር በተባለ ግሮሰሪ በረንዳ ላይ እንደሆነም የአዲስ አባባ ፖሊስ አርብ ኅዳር 30/2015 ዓ.ም. በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።
ግሮሰሪው በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ስፍራው ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በዚህ ፍንዳታም በሰባት ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ተጎጂዎች ህክምና እየተከታተሉ መሆናቸውንም አመልክቷል።
ፖሊስ ከፍንዳታው ጋር በተያዘ ምርመራ መጀመሩም ተገልጿል።
ፍንዳታው በማን እና እንዴት ሊደርስ እንደቻለ ያልጠቀሰው ይህ መግለጫ ሆኖም “የከተማችን ሰላም ውሎ ማደር እንቅልፍ የሚነሳቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በጋራ መከላከል ይገባል” የሚል መልዕክት አስፍሯል።
ፖሊስ ፀረ-ሰላም ብሎ የጠራቸውን ኃይሎች ማንነትን ግን በስም አልጠቀሰም።
ሆኖም “የከተማችን ሰላም ውሎ ማደር እንቅልፍ የሚነሳቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሰላማችንን ለማደፍረስ ወደ ኋላ እንደማይሉ ሕብረተሰቡ ተገንዝቦ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ እና አጥፊዎችን በማጋለጥ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥል” የሚል መልዕክትም አስተላልፏል።
አክሎም “በተለይም አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ለጋራ ደኅንነት ሲባል ለጥበቃ እና ለፍተሻ ሥራ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል” በሚል አፅንኦት ሰጥቷል፡፡
በዚሁ መግለጫ ላይ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር በተሰሩ ሥራዎች ወደ አዲስ አበባ የገቡ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ፖሊስ መያዙን አስታውሷል።
በተለያዩ ጊዜያት ወደ አዲስ አበባ ከተማ በርካታ በድብቅ ሊገቡ የነበሩ እና በተለያዩ ስፍራዎች የተደበቁ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማዋ ፖሊስ ሲያሳውቅ ቆይቷል።
ከአንድ ሳምንት በፊትም ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ውስጥ በጦር መሳሪያ ዝውውር በሚጠጠሩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ላይ አደረኩት ባለው ፍተሻ ሽጉጦች፣ ጥይቶች እና የእጅ ቦምቦችን መያዙን ገልጾ ነበር።
በዚህም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 እና 14 ከጦር መሳሪያዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎችን መያዙንና በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገው ብርበራ 5 ሽጉጦች እና 53 ልዩ ልዩ የሽጉጥ ጥይቶች ሲያዙ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በተመሳሳይ 4 ሽጉጥ ከ30 መሰል ጥይት እና 1 የእጅ ቦንብ መያዙን ገልጿል።
እንዲሁም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ፊናንስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ክትትል በአንድ ተሽከርካሪ ውስጥ ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ 15 የእጅ ቦንብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ መግለጹ ይታወሳል።
በዚህም በአጠቃላይ 16 የእጅ ቦንብ፣ 9 ሽጉጥ እና 83 የተለያዩ የሽጉጥ ጥይቶችን ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር በፖሊስ ተይዘው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳውቆ እንደነበር ይታወሳል።












