በኦሮሚያ ክልል ‘እጅግ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች’ እየተፈጸሙ እንደሆነ ኢሰመኮ አስታወቀ

ከኦሮሚያ ክልል በግጭት ከተፈናቀሉት መካከል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በግጭቶች እና በጥቃቶች እየደረሱ ያሉ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች እና መፈናቀሎች እጅግ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሆኑ በርካታ አመላካቾች እንዳሉ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

በክልሉ ዞኖች በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚገመቱ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን እና ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎች ደግሞ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን በአምስት ወር ግምገማው ነው ኢሰመኮ የገለጸው።

ኢሰመኮ በርካቶች የተቀጠፉበትን የሰሞኑን ጥቃት ጨምሮ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም እስከ ኅዳር 2015 ዓ.ም የደረሱ ግድያዎችን፣ የአካል ጉዳቶችን፣ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ስለተፈናቀሉባቸው ግጭቶች እና ጥቃት ዛሬ ኅዳር 28/2015 ዓ.ም. ሪፖርት አውጥቷል።

በእነዚህ ዞኖች ከሰላማዊ ነዋሪዎች በተጨማሪ የመንግሥት የፀጥታ እና የአስተዳደር አባላት መገደላቸውን፣ የመንግሥት እና የሲቪል ሰዎች ንብረቶች መዘረፋቸውን እንዲሁም ወድማቸውን አመልክቷል።

በተጨማሪም መሠረተ ልማቶች እና አገልግሎቶች መውደማቸውን ገልጾ ነዋሪዎች ከእነዚህ አገልግሎቶች ውጪ መሆናቸውን ኢሰመኮ አስፍሯል።

በጥቃቶቹ እና በግጭቶቹ ሳቢያ የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ያለ ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ፈታኝ እና አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ኑሯቸውን እንዲገፉ ተደርገዋል ብሏል።

በስድስት ወራት የደረሱትን ግጭቶችና ጥቃቶች ያስከተሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም በመገምገም፣ በሰብዓዊ መብቶች መርሆችና ድንጋጌዎች መሠረት እጅግ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች (grave violation of human rights) ተብለው የሚመደቡ መሆናቸው በርካታ አመላካቾች አሉ ብሏል።

ጥቃቶቹ እየደረሱ ያሉባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

ኢሰመኮ ጥቃቶቹ እና ግጭቶቹ እየደረሱ ያሉባቸውን አካባቢዎች ለማየት ሞክሯል። ኮሚሽኑ በአካል፣ ምርመራ ለማካሄድ ባልተቻለባቸው አካባቢዎች ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን፣ እንዲሁም የመንግሥት ኃላፊዎችን በማናገር በእነዚህ ስፍራዎች ክትትል አድርጓል።

በዚህም መሠረት ጥቃት እና ግጭት እየደረሰባቸው ያሉ ስፍራዎችን በሪፖርቱ አካቷል። እነዚህም ጥቃቶች በሆሮ ጉድሩ፣ በምሥራቅ፣ በምዕራብ ዞን፣በቄለም ወለጋ ዞኖች፣ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ፣ ኢሉ አባቦራ ዞን፣ በቡኖ በደሌ ዞን፣ በምሥራቅ ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና በአርሲ ዞን መሆኑም ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በተለይም በኪረሙ፣ ጊዳ አያና፣ አልጌ፣ ሁሩሙ፣ በአሙሩ፣ ሆሮ ቡሉቅ፣ ጃርደጋ ጃርቴ፣ ቦሰት፣ ግንደበረት፣ ጮቢ፣ ደራ፣ ኩዩ፣ መርቲ ጀጁ እና የአርሲ ዞን አጎራባች ወረዳዎች እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶች እና ጥቃቶችን በመከታተል ላይ እንደሚገኝም ገልጿል።

እነዚህ ጥቃቶችና ግጭቶች የሚከሰቱባቸው አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ እንደሆነና እያስከተሉት ያለው የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ደረጃ አስከፊ ነው ብሏል።

በእነዚህ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች በአይነታቸው እና በቁጥራቸው ጨምረዋል ወይም የመወሳሰብ አዝማሚያ እንዳሳየም ጠቅሷል።

ኢሰመኮ እንደሚለው እነዚህ ታጣቂ ቡድኖች ሙሉ ቀበሌዎችን ወይም ወረዳዎችን ጭምር በመቆጣጠራቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተባብሷል።

እንዲሁም የተጎዱ ሰዎችን ብዛትና ሁኔታውንም በጥልቅ የሚመጥን ምርመራን ማድረግ ፈታኝ አድርጎታል ብሏል። በዚህም ምክንያት እየደረሱ ያሉ ጥሰቶችን በተገቢው የሕግ እና የሰብዓዊ መብቶች መርሆችና ድንጋጌዎች ለመፈረጅ አስቸጋሪ እንዳደረገበትም ኮሚሽኑ ገልጿል።

በእነዚህ አካባቢዎች የታጠቁ ኃይሎች የትኞቹ ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኮሚሽኑ ጥቃት እና ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ለሰዎች መገደል እና ለንብረት መውደም ምክንያት ያላቸውን ታጣቂ ኃይሎች አስፍሯል።

በዚህም መሠረት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ በመንግሥት እራሳቸውን እንዲከላከሉ በሚል የታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከሌሎች ክልሎች ጭምር እንደመጡ እና በተለምዶ በአካባቢው የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸውን የሚነገር የታጠቁ ቡድኖች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው ኃይል ይንቀሳቀሳሉ ብሏል።

እነዚህ የታጠቁ ቡድኖች እና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለያዩ ወቅቶች እርስ በርሳቸው በሚያደርጓቸው ውጊያዎች፣ በሌላ ወቅትም በተናጠል በሚያደርሷቸው ጥቃቶች ሳቢያ የበርካቶችን ሕይወት እንደቀጠፉም ተገልጿል።

በተጨማሪም እነዚህ ኃይሎች ለበርካቶች የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት እንደዳረጉም አስፍሯል። በአንዳንድ ቀበሌዎች ወይም የገጠር ከተሞች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ወይም በከፊል መውደማቸው ተጠቅሷል።

በግጭት ሳቢያ ከሚደርሱ ግድያዎች፣ መፈናቀል፣ አካል ጉዳት እና ውድመት ከሚደርሱት በተጨማሪ ታጣቂዎች ወይም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች አካባቢዎችን በተቆጣጠሩበት ወቅት የሚያደርሷቸው ጥቃቶች አሳሳቢ እንደሆኑም ተጠቅሷል።

ታጣቂ ቡድኖች አካባቢዎችን በሚቆጣጠሩበት ወቅት መንግሥትን ወይም ሌላኛውን ታጣቂ ቡድን ትደግፋላችሁ በሚል በርካታ ግድያዎችና ጥሰቶች ይፈጸማሉ ብሏል።

በተጨማሪም ዝርፊያዎች፣ በግዳጅ የሚጠየቁ የገንዘብ ክፍያዎች ነዋሪዎችን ለከፋ ስቃይ መዳረጋቸውም ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

በሌላ በኩል በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም እንዲሁ ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋላችሁ በሚል ከፍርድ ውጪ ግድያዎች መፈጸማቸውን መረጃዎች አግኝቻቸለሁ ብሏል።

እንዲሁም መንግሥት ታጣቂ ቡድኖችን ኢላማ በማድረግ በሲቪል ሰዎች የመኖርያ ሰፈሮች አቅራቢያ በሚፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች፣ ሕገ ወጥና የዘፈቀደ እስሮች፣ ተጠርጠሪዎችን የማሰቃየት ተግባራት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነም ከኢሰመኮ ሪፖርት መረዳት ይቻላል።

የፖለቲካ አመለካከትን ወይም ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋላችሁ ከሚሉ ግድያዎች በተጨማሪ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ሆን ተብለው መፈጸማቸው አሳሳቢ እንደሆነም ገልጿል።

መፍትሔ

ኢሰመኮ የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥቱ ተቀናጅተው በአፋጣኝ እና በሙሉ ትኩረት በመሥራት ዘላቂ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥቷል።

የነዋሪዎችን ደኅንነት ማስጠበቅ፣ አፋጣኝ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ሁሉንም ባለድርሻዎች ማስተባበር እንዲሁም በቂ የፀጥታ ኃይልም ሊሰማራ እንደሚገባም አሳስቧል።

የፀጥታና የደኅንነት ሁኔታ የመፍጠሩን ኃላፊነት ጨምሮ በአካባቢዎቹ መድረስ የሚገባውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ማስተባበር የሚችል መዋቅር እንዲዘረጋ ጠይቋል።

በዚህም ከፍተኛ የክልሉን እና የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃላፊዎች፣ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንዲሁም የተጎጂዎች ተወካዮችን ያካተተ የአፋጣኝ ሁኔታዎች/የልዩ ሁኔታ ጊዜያዊ መዋቅር በአፋጣኝ ሊቋቋም እንደሚያስፈልግም ጠቅሷል።

“በእነዚህ ዞኖች ውስጥ በአሁኑ ወቅት የሚገኙ ነዋሪዎች ያሉበት በተዋጊ ቡድኖች መካከል መውጫ የሌለው አጣብቂኝ ውስጥ መጠለፋቸው ቢያንስ በተሟላ መልኩ ለመግለጽ/ለማስተጋባት የሚያስችል ሁኔታ እንኳን አለመኖሩ ከደረሰው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተነጥሎ ሊታይ የማይገባ ሲሆን አጠቃላይ ሰቆቃው ከዚህ የበለጠ ሊቀጥል ስለማይችል ሳይውል ሳያድር ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ ሊደረግለት ይገባል” በማለት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መግለፃቸው በመግለጫው ሰፍሯል።