ትሬቨር ኖዋ በመሰናበቻ ዝግጅቱ ለእናቱና ጥቁር ሴቶች ምስጋናውን ገለጸ

ኮሜዲያን ትሬቨር ኖዋ

የፎቶው ባለመብት, The Daily Show

ታዋቂው ደቡብ አፍሪካዊ ኮሜዲያን ትሬቨር ኖዋ የደይሊ ሾው የመሰናበቻ ዝግጅቱን ባደረገበት ፕሮግራም ለእናቱና ጥቁር ሴቶች ያለውን ክብር ገልጿል።

ትሬቨር ኖዋ በደይሊ ሾው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅነት ለሰባት ዓመታት ቆይቷል።

በእንባ በተሞላ የመሰናበቻ ፕሮግራሙም በዓለም ላይ ያሉ ጥቁር ሴቶችን አመስግኗል።

“ማን ያስተማረኝ ይመስላችኋል? ማን ቀረጸኝ፣ አሳደገኝ፣ አሳወቀኝ? ከእናቴ ጀምሮ፣ አያቴ፣ አክስቴ፤ በህይወቴ ሁሉ ያሉ ጥቁር ሴቶች ናቸው ለዚህ ስፍራ ያበቁኝ” ሲል ለታዳሚው ተናግሯል።

ትሬቨር በርካታ ተከታዮችን ካፈራው የቀድሞው የደይሊ ሾው የአዘጋጅነቱን ስፍራ ሲረከብ በአሜሪካ ብዙም ታዋቂ አልነበረም።

በመሰናበቻ ፕሮግራሙም ላይ ዝግጅቱን በሚያቀርብበት ስቱዲዮው ውስጥ ታዳሚዎችን ማግኘት ከባድ እንደነበር ተናግሯል። ነገር ግን ባለፉት ሰባት አመታት ውስጥ ትሬቨር ወጣት የፕሮግራሙ ተከታታዮችን ቀልብ መሳብ ችሏል።

በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ክስተቶች አለም አቀፋዊ እይታ እንዲኖራቸውም ማድረግ ችሏል። በነዚህ አመታትም የዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ወቅት፣ ‘ብላክ ላይቭ ማተርስ’ ተቃውሞዎችና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚጠቀሱ ናቸው።

ትሬቨር ስለ አሜሪካ በርካታ ጉዳዮችን ያሳወቁት ጥቁር ሴቶች ናቸው ሲልም እውቅናውን ችሯል። በአንድ አገር ውስጥ በርካታ ነገሮች ሲበላሹ በከፍተኛ ሁኔታ መጀመሪያ ዱላው የሚያርፍባቸው ጥቁር ሴቶች ስለሆኑ እየተከናወኑ ያሉ ጉዳየችን በጥልቀት ይረዳሉ ብሏል።

ለዚህም በመላው ዓለም ያሉ ጥቁር ሴት ጸሃፊዎች፣ እናቶች በአጠቃላይ ጥቁር ሴቶች እያበረከቱ ስላለው አስተዋፅኦም ከልቡ አመስግኗል።

የ38 ዓመቱ ትሬቨር ከቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅነቱ እንደሚለቅ መስከረም ወር ላይ ባሳወቀበት ወቅት በርካቶች እምነት ጥለውበት እንዳልነበር አስታውሷል።

“ለነበረኝ አስደናቂ ጉዞ ምስጋና ከፍ ያለ ነው። በጣም አስገራሚ ነው። ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ነገር ነው” በማለትም ተናግሯል።

ፈረንሳይ በአውሮፓውያኑ 2018 የዓለም ዋንጫን ባሸነፈችበት ወቅት በርካታ ተጫዋቿ ጥቁር ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የአፍሪካ ድል ነው በማለት ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ውዝግብ ውሰጥ መግባቱን ጨምሮ በባለፉት ዓመታት አንዳንድ ውዝግቦች ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ነው።