ጦርነቱ ያደረሰው ውድመት እና የመልሶ ግንባታው ተስፋ

በጦርነቱ ከወደሙ ተቋማት መካከል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጦርነቱ ከወደሙ ተቋማት መካከል

ጥቅምት 2013 በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አጎራባች ክልሎች ተስፋፍቶ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ እነሆ አንድ ወር አልፎታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ተወካዮች በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ አልፎም በኬንያ መዲና ናይሮቢ ተገናኝተው ስምምነቱን ከፈረሙ ወዲህ ጦርነት ጋብ ብሏል።

የሚያስፈልገውን ያህል እርዳታ እየገባ አይደለም የሚል ወቀሳ ቢሰማም፣ ወደ ክልሉ እርዳታ እየገባ እንደሆነና መሠረታዊ አገልግሎቶች እየተመለሱ እንዳሉ ተሰምቷል።

ጦርነቱ ያደረሰው ሰብዓዊ ቀውስና የመሠረተ ልማት ውድመት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ በርካታ ዓለም ዓቀፍ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ይህ ደም አፋሳሽ ግጭት በሰላማዊ መንገድ የሚቋጭ ከሆነ ቀጣዩ ከባድ ሥራ በጦርነቱ ከፍተኛ ወድመት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ መገንባት እንደሆነ ተነግሯል።

ለመሆኑ የደረሰው የመሠረተ ልማት ውድመት ምን ያህል ነው? የሚያወጣው ወጪና የሚወስደው ጊዜስ? ኃላፊነቱንስ የሚወስደው ማነው?

የደረሰው ውድመት

ለሁለት ዓመት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት በርካታ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፣ ጥንታዊ ቅርሶች እና ሌሎች ለጥፋት መዳረጋቸውን ባለፉት ሁለት ዓመታት ሪፖርት ተደርገዋል።

አንዳንድ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ ሌሎች ደግሞ በከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፌዴራል መንግሥት በ2013 መቀለን በተቆጣጠረበት ወቅት በመሠረተው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አማካይነት በደረሰው ውድመት ላይ መጠነኛ ዳሰሳ አድርጎ ነበር።

ዳሰሳው የተካሄደው በመቀለና አካባቢዋ ቢሆንም የደረሰው ውድመትና ዘረፋ ከፍተኛ እንደሆነ የሚገልጽ ነው። በክልሉ ውድመት ከደረሰባቸው መካከል የትምህርት ተቋማትና ፋብሪካዎች ይገኙበታል።

የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እንዲሁም የዓዲግራት መድኃኒት ፋብሪካ ውድመት ከደረሰባቸው መካከል ናቸው።

አልፎም ጦርነቱ ወደ አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች በተስፋፋበት ወቅት ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ፋብሪካዎች እና ሌሎች መሠረተ ልምቶች ውድመት ደርሶባቸዋል።

የአማራ ክልል በተደረገ ጥናት አገኘሁት ባለው ውጤት መሠረት ጦርነቱ ወደ ክልሉ ተዛምቶ በቆባቸው ከሰኔ 2013 እስከ ታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. ድረስ ባው ጊዜ 292 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን አመልክቷል።

የትግራይ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ያሠራው ጥናት ደግሞ በርካታ ተሽካርካሪዎች መዘረፋቸውን፤ በኋላ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በትብብር የተወሰኑት እንዲመለሱ መደረጋቸውን ያሳያል።

ኤፈርት የተሰኘው 50 ሺህ ያህል ሰዎች ቀጥሮ ያሠራ የነበረው የትግራይ ኢንዶውመንት ድርጅት የቦርድ አባል የነበሩት መሉ ዓለም የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ሲሰላ 11 ቢሊዮን ይገመታል ይላሉ። አክለው መልሶ ለመገንባት 60 ቢሊዮን ብር ሊጠይቅ እንደሚችል ይናገራሉ።

የትምህርት ሚኒስቴር በአንድ ወቅት ባወጣው መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ከሰባት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መውደማቸውን ገልጦ ነበር።

ሚኒስቴሩ በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችና ከ48 ሺህ የላቁ መምህራን ከትምህርት መራቃቸውን ዘግቧል።

ምንም እንኳ አብዛኛው ውድመት የደረሰው በትግራይ ክልል ይሁን እንጂ በአማራ እና አፋር ክልሎች በርካታ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን መሥሪያ ቤቱ ገልጧል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ተቋም ባወጣው ሪፖርት ትምህርት ቤቶች የጦር ካምፕ ሆነዋል ሲል ወቀሳ መሰዘንዘሩ ይታወሳል።

ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ኤምኤስኤፍ በበኩሉ 2013 አጋማሽ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ሦስት አራተኛ የሚሆኑ የጤና ማዕከላት ላይ ዘረፋና ውድመት ደርሷል ሲል ዘግቧል።

ጦርነቱ በርካታ መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ሰለባ ከማድረጉም በተጨማሪ ጥንታዊ ቅርሶችና የቱሪስት መስህቦችንም ለጉዳት ዳርጓል።

ጥንታዊ ገዳማትና መስጅዶች ጉዳት እንደደረሰባቸውና እንደተዘረፉ ከመዘገቡም በላይ ከጥንታዊ ቤተ-እምነቶች የተሰረቁ ቁሳቁስ አማዞንን በመሳሰሉ የበይነ-መረብ መገበያያ ዘዴዎች በርካሽ ዋጋ ሲሸጡ እንደነበር ተነግሯል።

የተቃጠለ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መልሶ ግንባታ እንዴት ይከናወናል?

የአፍሪካ ኅብረትን በመወከል በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ካደረጉት መካከል አንዱ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ናቸው።

ኦባሳንጆ በቅርቡ ሴማፎር በተባለ አንድ ድረ-ገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ በሰሜን ኢትዮጵያ መልሶ ግንባታ ለማከናወን 25 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል።

ካሜሩን ሃድሰን የአሜሪካ ኢንተለጀንስ ኤጀንሲ [ሲአይኤ] የቀድሞ አባል እና የሲኤስአይኤስ አፍሪካ ፕሮግራም ከፍተኛ አማካሪ ናቸው።

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩት ሃድሰን መጀመሪያ የሚሆነው ‘ዶነር ኮንፈረንስ’ ነው ይላሉ። ይህ ማለት የተራድዖ ድርጅቶች ተሰባስበው ምን ያክል ገንዘብ ያስፈልገናል ብለው የሚወስኑበት ውይይት ነው።

የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው ባይሳ ዋቅወያ በበኩላቸው በዩጎዝላቪያ ጦርነት ወቅት የደረሰውን በምሳሌ በማንሳት ስለመልሶ ግንባታ ያላቸው ሐሳብ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

በሙያቸው የተባበሩት መንግሥታትን ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት ምሁሩ በዩጎዝላቪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው ክሮሺያ እና ሰርቢያ ነበሩ ይላሉ።

“ጦርነቱ ከቆመ 27 ዓመታት ሞልቶታል፣ ሆኖም ሙሉ ለሙሉ መልሶ ለመገንባት እስከዛሬም አልተቻለም።”

ሃድሰን፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የእርዳታ ድርጅቶች ሰሜን ኢትዮጵያን በተለይ ደግሞ ትግራይን መልሶ ለመገንባት ይረባረባሉ የሚል እምነት የላቸውም።

የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ምናልባት እጃቸውን ይዘረጉ ይሆን እንጂ፣ ሌሎች ዓለማት እንደሚታየው ዓይነት ርብርብ የማይኖርበት ምክንያት ያስረዳሉ።

“ለትላልቅ ድጋፍ ሰጪዎች መልሶ ግንባት ማለት ኢንቨስት ማድረግ ነው። ለአንዲት አገርና ሕዝቧ ወደፊት የተሻለ ነገር እንዲመጣ መሠረት መጣል ነው። በትግራይ ጦርነት ከተሳተፉት መካከል ከዚህ ውድመት የተማረ የለም። እንደውም በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ወደተመሳሳይ ግጭት እያመሩ ነው።”

ባይሳ፤ አውሮፓዊያኑ ክሮሺያ እና ሰርቢያ ራሳቸውን መልሰው የገነቡት ከዓለም አቀፍ ተቋማት በመጣ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ዳያስፖራውም የበኩል በማድረጉ እንደሆነ ይናገራሉ።

“መሠረተ ልማቱ ውድመቱ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ነበረበት ለመመለስ ተችሏል። ነገር ግን በሰዎች መካከል የተፈጠረውን ቁስል መልሶ መገንባት አልተቻለም።”

ሃድሰን፤ በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል ያለው አለመተማመን ከባድ መሆኑን ጠቅሰው “መጓተት ቢኖርም ለውጥ የለም ብሎ መናገር ፍትሐዊ አይደለም ይላሉ።”

የትግራይ ክልል መዲና ከአንድ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘቷን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጠዋል።

ከኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በተጨማሪ፣ የኢትዮ-ቴሌኮም በሽረ እንዳሥላሴ እና በአከባቢው የስልክ አገልግሎት የሙከራ ሥራ ጀምሯል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል በጦርነት ምክንያት የደረሰውን ውድመት ተከትሎ ለሚያስፈልገው መልሶ ግንባታ ገንዘብ ከየት ይመጣል የሚለው አንዱ ጥያቄ ነው።

ጦርነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ላይ የደረሰው ጫና ማዕከላዊው መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ለታሰበው መልሶ ግንባታ የሚሆን በጀት የለውም የሚሉ ሐሳቦች ይሰማሉ።

እንደ አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝ ሁሉ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው ባይሳ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ መልሶ ግንባታ ላይ ስለሚኖረው ሚና ጥያቄ አላቸው።

“ማውደም ቀላል ነው፤ ነገር ግን የወደመን መተካት የትም አገር ቢሆን ከባድ ነው።”

ምሑሩ መፍትሔው ይሄ ነው ይላሉ፡ “የእኛ ሰው ራሱን አሳምኖ የጠፋው ጠፍቷል፤ ያለፈው አልፏል፤ ነገር ግን አሁን ወገባችንን ጠበቅ አድርገን፤ ከዜሮ ጀምረን እናድጋለን ብሎ መነሳት አለበት።