ከተፈረመ አንድ ወር የሞላው የሰላም ስምምነት፡ ምን ተባለ ምን ተከናወነ?

 የፕሪቶሪያውን የሠላም ስምምነት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የፕሪቶሪያውን የሠላም ስምምነት ይፋ ካደረጉ ዛሬ ኅዳር 23/2015 ዓ.ም. አንድ ወር ደፈነ።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ነው በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ስምምነቱ የተደረሰው።

የደቡብ አፍሪካውን ድርድር የአፍሪካ ኅብረት በበላይነት መርቶታል።

ስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ከህወሓት በኩል ደግሞ የቡድኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ፊርማቸውን አኑረዋል።

ለአስር ቀናት ሲካሄድ በቆየው ድርድር በ 12 ነጥቦች ላይ ከስምምነት ተደርሷል።

ከማክሰኞ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየውን የሰላም ንግግር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሲጎን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ ሲያስተባብሩት ነበር።

አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ደግሞ በድርድሩ ላይ በታዛቢነት ተሳትፈዋል።

ከስምምነቱ በኋላ ምን ተባለ? ምን ተከሰተ?

ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም.

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከህወሓት ጋር በነበረው የሰላም ድርድር “ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ መቶ በመቶ ተቀባይነትን አግኝቷል” ሲሉ ተናገሩ።

“ጀግንነት ማለት ማሸነፍ ብቻ አይደለም። ጀግንነት ማለት ከድል በኋላ ይቅር ማለት ነው። ጀግንነታችን የሚረጋገጠው ካለን አካፍለን በትግራይ የተጎዱ ወገኖቻችንን ማጉረስ ስንችል ነው” ብለዋል።

“ለመላው የትግራይ ሕዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት አላስፈላጊ ጦርነት፣ አላስፈላጊ ጉዳት፣ አላስፈላጊ ኢትዮጵያን አሳልፎ መስጠት በዚህ ይብቃ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጥቅምት 29/2015 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ከፍተኛ የጦር አመራሮች በኬንያ መዲና ናይሮቢ ተገናኙ።

የጦር አመራሮቹ የተገናኙት በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት የማስፈጸም አንዱ አካል በሆነው የትጥቅ ማስፈታት ሂደት ላይ ለመነጋገር ነበር።

የፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ኃይል ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ለተ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ ሰኞ ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም. ረፋድ በናይሮቢ ንግግሩን ጀመሩ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጥቅምት 29/2015 ዓ.ም.

የናይሮቢ ንግግር አንዱ አጀንዳ በትግራይ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ እንደሆነ አሜሪካ አስታወቀች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃለ አቀባይ ኔድ ፕራይስ በስምምነቱ መሠረት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ማፋጠን እንዲሁም በትግራይ እና በአጎራባቾቹ የአፋር እና የአማራ ክልሎች ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ አንደኛው አጀንዳ እንደሆነ ተረድተናል ብለዋል።

የሁለቱ ወገኖች አመራሮች የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን ያስታወቁት ኔድ ፕራይስ “እነዚህ ተጨባጭ እርምጃዎች ሁለቱም ወገኖች ጠመንጃን ጸጥ ለማሰኘት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያንጸባርቃል” በማለት አስረድተተዋል።

 ኅዳር 01/2015 ዓ.ም.

በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት ቢደረስም ወደ ትግራይ ክልል ምግብም ሆነ መድኃኒት እየገባ እንዳልሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

“የግጭት ማቆም ስምምነቱን ተከትሎ ወዲያውኑ ምግብ እና መድኃኒት ወደ ክልሉ ይገባል ብዬ እየጠበቅኩ ነበር። ይህ ሁኔታ ግን እየታየ አይደለም” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በክልሉ የተቋረጡት የቴሌኮም፣ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱም ጠይቀዋል።

አንድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣን ግን ዶክተር ቴድሮስ የሰላም ስምምነቱን ለማደፍረስ እየሞከሩ ነው በሚል ወቅሰው ምግብ እና መድኃኒት ወደ ትግራይ እየደረሰ ነው ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎችም የመብራትና የቴሌኮም አገልግሎቶች ወደነበረበት መመለሱን ጨምረው ተናግረዋል።

ኅዳር 02/2015 ዓ.ም.

ሰባ በመቶው የትግራይ አካባቢ በኢትዮጵያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ሆኖ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እና የተደራዳሪ ቡድኑ አባል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገጻቸው ላይ አሰፈሩ።

“በአገር መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ባልሆኑ አካባቢዎች ጭምር፣ በትግራይ ክልል ውስጥ ከየትኛውም ጊዜ በላይ እርዳታ እየቀረበ ነው” ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን።

የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ለፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት፣ ኤኤፍፒ አምባሳደር ሬድዋን የተናገሩት “ተጨባጭ መረጃን መሠረት ያደረገ አይደለም” ማለታቸውን ዘግቧል።

ኅዳር 03/2015 ዓ.ም.

ደቡብ አፍሪካ ላይ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ስምምነት ዝርዝር አተገባበርን በተመለከተ የመንግሥት እና የህወሓት ከፍተኛ የሠራዊት አዛዦች ቅዳሜ ኅዳር 03/2015 ዓ.ም. ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ ስምምነት ፈረሙ።

ስምምነቱን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ጄኔራል ታደሰ ወረደ የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች በተገኙበት ሲፈርሙ የፕሪቶሪያው ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 ኅዳር 02/2015 ዓ.ም.

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ የሰላም ስምምነቱ በታቀደለት መንገድ እንዲፈጸም መንግሥት እየሠራ መሆኑን ገልጾ፤ ለዚህም በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ስር ባሉ አብዛኞቹ የትግራይ አካባቢዎች እርዳታ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንና መሠረታዊ አገልግሎቶች ቀስ በቀስ ሥራ እየጀመሩ ነው ብሏል።

የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው የእርዳታ ጭነቶች ወደ ጦርነት ቀጠና ለመግባት ፈቃድ እየተጠባበቁ እንዳሉ ተናግረዋል።

ኅዳር 04/2015 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ መንግሥት ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች “ወደ ማኅበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ ለማስቻል” ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ሊያቋቁም መሆኑን አስታወቀ።

ይህንን ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ ደንብንም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያጸደቀ ሲሆን፣ ደንቡ ከጸደቀበት ዕለት ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑም ተገልጿል።

በአገሪቱ ያሉ ጦርነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት እና የመጨረሻ እልባት እንዲበጅላቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም በዚህ መግለጫ ተጠቅሷል።

የቀይ መስቀል አውሮፕላን በሽረ

የፎቶው ባለመብት, ICRC

ኅዳር 06/2015 ዓ.ም.

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር የእርዳታ መድኃኒት የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ መድረሳቸውን አስታወቀ።

የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት በዘላቂነት ተኩስ ለማቆም እና በወታደራዊ ዝርዝር ሁኔታዎች ላይ ከተስማሙ በኋላ እርዳታ ወደ ትግራይ መድረሱን ሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሲገልጽ የመጀመሪያው ነው።

ኅዳር 07/2015 ዓ.ም.

ኤርትራ ሠራዊቷን ከትግራይ የማታስወጣ ከሆነ ማዕቀብ ሊጣልባት እንደሚችል አንድ የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናገሩ።

በስም ያልተጠቀሱት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ፣ ማክሰኞ ኅዳር 06/2015 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት በአሁኑ ወቅት ከኤርትራ ጦር በተጨማሪ የአማራ ልዩ ኃይል እና የአፋር ሚሊሻ በትግራይ ይገኛሉ ያሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የደረሱት የሰላም ስምምነት ኃይሎቹ እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱ እንዲከበር እና ተፈጻሚ እንዲሆን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ “ማዕቀብ ለመጣል አናንገራግርም” ብለዋል።

ኅዳር 11/2015 ዓ.ም.

የኤርትራ ጦር በትግራይ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ እንዲያቆም እና ከትግራይ በአስቸኳይ እንዲወጣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ህወሓት ጠየቀ።

ህወሓት ይህንን ጥሪ ያቀረበው ቅዳሜ ኅዳር 10/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ሲሆን፣ የኤርትራ ጦር በትግራይ ሕዝብ ላይ “ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍ እየፈጸመም ነው” ብሏል።

በዚህም መግለጫ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት በኤርትራ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።

ኅዳር 12/2015 ዓ.ም.

ከተደራዳሪዎቹ ዋነኞቹ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና አቶ ጌታቸው ረዳ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እሁድ ዕለት ኅዳር 11/2015 ዓ.ም. ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጄኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤ ድርድሩ የተለመደውን ዓለም አቀፍ የሰላም ድርድር መስፈርት የሳተ እንደነበረና የኢትዮጵያ መንግሥት መቀለ ከተማን በመቆጣጠር የውይይት ውጤቱን ለመቀየር ያልተሳካ ጥረት አድርጓል ብለዋል።

ተደራዳሪዎቹ ከስምምነት ላይ ሊደርሱ የቻሉት በጠንካራ “[የትግራይ ኃይሎች] የመከላከያል ጠንካራ አቋም እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት” መሆኑ ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ሁሉም ፍላጎቶቻቸው ባይሟሉም መሠረታዊ የተኩስ አቁም አላማቸውን ማሳካት መቻላቸው ተናግረዋል። 

ኅዳር 14/2015 ዓ.ም.

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሰላም ስምምነቱ ዙሪያ መነጋገራቸውን ገለጹ።

ውይይቱን በሚመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤትም ሆነ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫም የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ እንዲሁም ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ፣ በተጨማሪም መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለማድረግ እያከናወነ ላለው ሥራ ብሊንከን እውቅና ሰጥተዋል ብሏል።

አንቶኒ ብሊንከን “ሁሉም የውጭ ኃይሎች ከአገሪቱ እንዲወጡ እና የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት በአንድ ላይ እንዲከናወን” ማድረግን ጨምሮ የተደረሰው ስምምነት በቶሎ ተግባራዊ የመደረግን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል ብሏል።

ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና የፌደራል መንግሥቱ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ኅዳር 14/2015 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ አመራሮች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት የትግራይ ኃይሎች ተሰልፈውባቸው ከቆዩባቸው ግንባሮች የማስወጣት ሂደት እንደሚጀመር የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ።

ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ለታጣቂዎቻቸው የማስረዳት ሥራዎች እየተገባደዱ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ይሄንን ተከትሎ አሁን ከተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች መውጣት እንደሚጀምሩ አመልክተዋል።

“ስምምነት ተደርጓል፤ ከዚያ በኋላ ‘ዲስኢንጌጅ’ ማድረግ፣ ሠራዊቱ ተጓጉዞ ወደ ትክክለኛው ቦታ እንዲገባ የማድረግ ሥራዎች በሁለት እና ሦስት ቀናት ውስጥ ይጀመራል” ብለዋል።

“አንድ ተጨባጭ ለውጥ የተኩስ ልውውጥ መቆሙ ነው። በዚህ ደግሞ ሕዝቡ ደስተኛ ነው . . . ሠራዊቱም ደስተኛ ነው። ሲታኮስ የነበረው ሠራዊት በአንዳንድ አካባቢዎች በአካል ተገናኝቶ ሀሳብ የሚለዋወጥበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉም ጄኔራሉ ተናግረዋል።

ኅዳር 15/2015 ዓ.ም.

በጦርነት ሳቢያ ተቋርጦ የቆየውን ወደ ትግራይ የሚደርገውን በረራ መልሶ ለመጀመር የሚያስችለውን ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቢቢሲ ገለጸ።

የሠላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ አየር መንገዱ የንግድ በረራዎችን መልሶ ለመጀመር ሙሉ ዝግጀቱን እንዳጠናቀቀ የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያደቻ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በክልሉ ሥራውን የሚያከናውነበት “ሁኔታ እየተስተካከለ መምጣቱን” ጠቅሰው በረራዎችን ለመጀመር የፀጥታ አካላትና የሲቪል አቪዬሽንን የመጨረሻ ፍቃድ እየተጠበቀ ነው ብለዋል።

ኅዳር 15/2015 ዓ.ም.

በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦቦሳንጆ የተመራው የአፍሪካ ኅብረት ልዑካን ሐሙስ ኅዳር 15/2015 ዓ.ም. ባደረጉት የመቀለ ጉብኝት ከህወሓት አመራሮች ጋር ተነጋገሩ።

የሰላም ስምምነቱ ትልቅና ውስብስብ እንደመሆኑ መጠን የማኅበረሰቡም ስምምነት ስለሚያስፈልገው ሕዝቡን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የትግራይ ኃይል አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ለልዑካኑ ማስረዳታቸውን አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው ገልጸዋል።

በዚህ የሰላም ስምምነት ዋነኛ እክል የኤርትራ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው ቦታዎች ላይ በትግራይ ተወላጆች ላይ እየፈጸሙት ያለው መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰት መሆኑንም ለልዐካኑ አስረድተናል ብለዋል።

የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በበኩላቸው “የትኛውም አገር የውጭ አገር በመሬቱ ላይ መኖሩን መቀበል የለበትም” ብለዋል።

ኅዳር 21/2015 ዓ.ም.

በትግራይ ክልል ተቋርጠው የቆዩትን የቴሌኮም አገልግሎቶችን መልሶ ለማስጀመር የጥገና ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም ለቢቢሲ አስታወቀ።

ቀደም ሲልም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የጥገና ሥራዎችን በማከናወን በተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አቅርቦት መልሶ መጀመሩን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ የኃይል አቅርቦትን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ረገልጿል።

ኅዳር 22/2015 ዓ.ም.

የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱበትን ዝርዝር ዕቅድ የሚሠራ የሁለቱ ወገኖች የባለሞያዎች የጋራ ኮሚቴ ሽረ ላይ እየመከረ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ውይይሩ ከረቡዕ ኅዳር 21 ጀምሮ ከፌዴራል መንግሥት እና ከትግራይ ታጣቂዎች የተውጣጣው የባለሞያዎች የጋራ ኮሚቴ በቀናት ውስጥ ሥራውን ያጠናቅቃል ተብሏል።

በዚህም የጋራ ኮሚቴው የሚያወጣው ዝርዝር ዕቅድ ትጥቅ የማስፈታት፣ ታጣቂዎችን ወደ ካምፕ የማስገባት እና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመልስ ይሆናል ተብሏል።