የመንግሥት እና የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደረሱ

ስምምነት

ደቡብ አፍሪካ ላይ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ስምምነት ዝርዝር አተገባበርን በተመለከተ የመንግሥት እና የህወሓት ከፍተኛ የሠራዊት አዛዦች ዛሬ ቅዳሜ ኅዳር 03/2015 ዓ.ም. ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ ስምምነት ፈረሙ።

ስምምነቱን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ጄኔራል ታደሰ ወረደ የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች በተገኙበት ሲፈርሙ የፕሪቶሪያው ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ ስምምነት ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት መጠበቅ፣ የትጥቅ መፍታትንና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ጉልህ እርምጃ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ተናግረዋል

ይህ የዛሬው ፊርማ አስራ ሁለት ቁልፍ ጉዳዮችን ይዞ ፕሪቶሪያ ላይ ከአንድ ሳምንት በፊት ለተፈረመው ስምምነት ተግባራዊነት በር ከፋች ነው ተብሎ ይታመናል።

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቅዳሜ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ በመንግሥት እና በህወሓት የጦር አዛዦች መካከል በተፈረመው ስምምነት፣ የፈደራሉ ሠራዊት ወደ መቀለ በሚገባበት ዕቅድ ላይ ከስምምነት መደረሱን ገልጿል።

መንግሥት እንዳለው በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በተያዘው የጊዜ ገደብ ሁለቱ ወገኖች “ትጥቅ የሚፈታበትን እና የመከላከያ ሠራዊት ወደ መቀሌ በሚገባበት ዕቅድ ላይ ተስማምተዋል” ብሏል።

ከሰኞ ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ናይሮቢ ውስጥ በዝግ መካሄድ የጀመረው ንግግር ለሦስት ቀናት ይቆያል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ለተጨማሪ ሁለት ቀናት ተራዝሞ ዛሬ ቅዳሜ የደረሱበት ውጤት ይፋ ሆኗል።

ለአምስት ቀናት በተደረገው ንግግር ላይ የፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ በዋናነት ተሳትፈውበታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቅዳሜ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ የሰላም ስምምነቱ በታቀደለት መንገድ እንዲፈጸም መንግሥት እየሠራ መሆኑን ገልጾ፣ ለዚህም በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ስር ባሉ አብዛኞቹ የትግራይ አካባቢዎች እርዳታ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንና መሠረታዊ አገልግሎቶች ቀስ በቀስ ሥራ እየጀመሩ ነው ብሏል።

ሁለት ዓመት የሆነውን የሰሜን ኢትዮጵያውን የእርስ በርስ ጦርነት ለመቋጨት በመንግሥት እና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል ደቡብ አፍሪካ ላይ የተፈራረሙን ስምምነት ተከትሎ ነው ወታደራዊ አዛዦቹ የአፈጻጸም ሂደቱን በተመለከተ ከስምምነት የደረሱት።

ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማብቃት በዘላቂነት ግጭትን ማስቆም፣ የእርዳታ አቅርቦት እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች መጀመር እንዲሁም ትጥቅ መፍታትን የሚያካትት ነው።

ቅዳሜ ኅዳር 03/2015 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በሁለቱ ወታደራዊ አዛዦች መካከል በይፋ እንደሚፈረም የተነገረው ሰነድ ከሰዓታት በኋላ ምሽት 12፡30 ላይ የተፈረመ ሲሆን፣ አስተባባሪዎቹ ለመዘግየቱ ይቅርታ ከመጠየቅ ውጪ ምክንያቱን አልገለጹም።

ይህ ናይሮቢ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው የወታደራዊ አዛዢቹ ንግግር ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመው አጠቃላይ ስምምነት ተግባራዊ በሚደረግበት ዝርዝር ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

ሁለቱም ወገኖች ለስምምነቱ አተጋባበር የሚሆን የጋራ የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያውጡ፣ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ከሚቋቋመው የስምምነቱን አተገባበር ከሚቆጣጠር እና ከሚያረጋግጠው ቡድን ጋር እንደሚተባበሩ ተገልጿል።

ፊርማቸውን ያኖሩት የሁለቱም ወገን የጦር አዛዦች ናይሮቢ ላይ የተደረሰውን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግበራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህ መሠረት ዋነኛው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ሁለቱም ወገኖች በ24 ሰዓታት ውስጥ በከፍተኛ የጦር መሪዎቻቸው ንግግር እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን፣ በአምስት ቀናት ውስጥ ደግሞ ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት ተግባራዊ በሚሆንበት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር በወጣ መረሃ ግብር አማካይነት ነው ናይሮቢ ላይ ሲመክሩ የሰነበቱት።