ሰባ በመቶ የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሰባ በመቶው የትግራይ አካባቢ በኢትዮጵያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ሆኖ እርዳታ እየቀረበ መሆኑ የፌደራሉ መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ገለጹ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እና የተደራዳሪ ቡድኑ አባል አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን ከትግራይ ቆዳ ስፋት 70 በመቶ ያህሉ በፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥር ሥር መሆኑ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ጨምረውም በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኙት የትግራይ አካባቢዎች የሰብዓዊ እርዳታ እና መድኃኒት እየቀረበ ነው ብለዋል።
“በአገር መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ባልሆኑ አካባቢዎች ጨምር፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ ከየትኛውም ጊዜ በላይ እርዳታ እየቀረበ ነው” ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን።
ነገር ግን የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ለፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት፣ ኤኤፍፒ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ያሉትን የሚቃረን ሃሳብ ሰንዝረዋል።
ኤኤፍፒ አቶ ጌታቸውን እንደጠቀሰው አምባሳደር ሬድዋን የተናገሩት “ተጨባጭ መረጃን መሠረት ያደረገ አይደለም” ማለታቸውን ዘግቧል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሐሙስ ዕለት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ግጭት ለማቆም ስምምነት ቢደረሰም ወደ ትግራይ ምግብም ሆነ መድኃኒት እየገባ አይደለም ብለው ነበር።
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳሉት፤ “ምንም ነገር እየገባ አይደለም። . . . የግጭት ማቆም ስምምነቱን ተከትሎ ወዲያውኑ ምግብ እና መድኃኒት ወደ ክልሉ ይገባል ብዬ እየጠበቅኩ ነበር። ይህ ሁኔታ ግን እየታየ አይደለም” ብለዋል።
ጨምረውም በትግራይ ክልል ውስጥ ሰዎች በረሃብ እና በህክምና ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች ምክንያት እየሞቱ ነው ብለዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው መድኃኒት እና ምግብ የጫኑ ተሸካርካሪዎች ሽረ ከተማ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
“ምግብ የጫኑ 35 እና መድኃኒት የጫኑ 3 ተሸከርካሪዎች ሽረ ከተማ ድርሰዋል። በረራዎች ተፈቅደዋል” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ከሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ በተጨማሪ የመሠረታዊ አገልግሎቶች ዳግም የማስጀመር ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።
“መሠረታዊ አገልግሎቶች እየተቀጠሉ ነው” ያሉት አምባሳደሩ የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት በዘላቂነት ግጭት ለማቆም የደረሱት ስምምነት አገልግሎቶችን እንዲጀመሩ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ከቀናት በፊት የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ለሁለት ዓመታት ተካሂዶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ያደረሰውን ጦርነት ለመቋጨት የሰላም ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚህ ስምምነት መሠረት ህወሓት ትጥቅ ለመፍታት የተስማማ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የሰብዓዊ እርዳታ የማድረስ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን የማስጀመር ኃላፊነት ተጥሎበታል።
ሁለቱ አካላት በስምምነታቸው መሠረት ህውሓት ትጥቅ የሚፈታበትን ሁኔታ ዝርዝር ለመነጋገር የአገር መከላከያ እና የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በኬንያ መዲና ናይሮቢ እየመከሩ ይገኛሉ።
ሁለቱ ወገኖች ባለፉት አምስት ቀናት ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ዛሬ አርብ ኅዳር 02/2105 ዓ.ም. ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለት ዓመት በሞላው ጦርነት በተለይ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው የእርዳታ አቅርቦት በተለያዩ ጊዜያት ሲጀመርና ሲቋረጥ መቆየቱ ይታወቃል።
በተጨማሪም የስልክ፣ የመብራት፣ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በክልሉ ውስጥ ከተቋረጡ ወራት ተቆጥረዋል።
በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ጦርነት በዘላቂነት ለማቆም ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ስምምነት ሲፈረም፣ ያልተገደበ የእርዳታ አቅርቦት ወደ ክልሉ እንዲቀርብና መሠረታዊ አገለግሎቶች በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምሩ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።












