በምዕራብ ኦሮሚያ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

መንዲ ካርታ

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ተቆጣጥሮ ይገኝበታል በተባለችው መንዲ ከተማ በተፈጸም የአየር ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ጥቅምት 30/2015 ዓ.ም. እኩለ ቀን ከ7-8 ሰዓት በነበረው የአየር ጥቃት አንዱ ዒላማ የነበረው የታጣቂዎች ተሸከርካሪ ቢሆንም በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡት ግን አብዛኛዎቹ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልዋል።

በምዕራብ ወለጋ የምትገኘው መንዲ ከተማ ባለፉት ቀናት በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር የቆየች ሲሆን አሁን ላይ የመንግሥት ጦር ወደ ከተማዋ ዘልቆ መግባቱን የሚገልጹ ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።

ረቡዕ ዕለት የአየር ጥቃቶች ሲፈጸሙ መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራቸው የታጣቂ ቡድኑ አባላት በከተማዋ ነበሩ ተብሏል።

ከትናንት በስቲያ በነበሩት ጥቃቶች ወደ 20 የሚጠጉ ሰላማዊ ሰዎች ሳይሞቱ እንደማይቀር ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ ግን የሟቾች ቁጥር ከ100 በላይ ነው ብሏል።

የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ከትናንት በስቲያ መንዲ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች የሞቱት 30 ሰዎች መሆናቸውን እና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል። ቃል አቀባዩ ኦዳ ተርቢ በታጣቂ ቡድን አባላቶች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ያሉት ነገር የለም።

የአየር ጥቃቱን በተመለከተ እስከአሁን ከመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም። የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ከቢቢሲ ለሚነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

የአየር ጥቃት በሚፈጸምባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች በተደጋጋሚ የሚሉት የአየር ጥቃቱ ዒላማ ታጣቂ ቡድኑ ይሁን እንጂ ሕይወታቸውን እያጡ ያሉት ሰላማዊ ሰዎች ናቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተመሳሳይ ከትናንት በስቲያ መንዲ ከተማ ሁለት ስፍራዎች የደረሱት የአየር ጥቃቶች ዒላማ ያደረጉት ታጣቂ ቡድኑን ይሁን እንጂ አብዛኛው ተጎጂ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው።

በዚህ ጥቃት ሕይወታቸውን ካጡት መካከል ታሪኩ ዋና የተባሉ ወንጌላዊ እንደሚገኙበት ጓደኛቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል። “ታጣቂዎቹ የሚይዙት መኪና መንገድ ላይ ቆሞ ነበር። ድሮን መኪናውን ሲመታ ፍንዳታ አጋጥሞ ቤት ስር ተቀምጠው የነበሩ ሰላማዊ ሰዎችን ገደለ፤ እግራቸው የተቆረጠም አሉ” ብለዋል።

“የተገደሉት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ብዙ አይደሉም። አብዛኛው የተጎዳው ሰላማዊ ሰው ነው”

ይህንኑ ጥቃት በተለመለከተ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ የሰጡት ሌላ ነዋሪ፤ “እዚህ መኪና ላይ የነበሩት ታጣቂ ቡድን አባላት ብዙ አይደሉም። ቢበዛ አምስት ወይም ስድስት ቢሆኑ ነው። በሁለት መኪኖች መሃል ይህን መኪና ለይታ ነው የመታችው (ሰው አልባ አውሮፕላን)። መኪናው እዛው ጋየ። የተጎዳው የኅብረተሰብ ክፍል ግን ብዙ ነው” ብለዋል።

“ጥቃቱ እንደተፈጸመ እዛው የሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር 7 ወይም 8 ናቸው። 13 ሰዎች ደግሞ ሆስፒታል ገብተዋል” ሲሉ እኚህ ነዋሪ ጨምረው ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በምዕራብ ኦሮሚያ የአየር ላይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን እና የወለጋ ዞኖች የአየር ጥቃት ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ከቀናት በፊት ምዕራብ ወለጋ ቦጂ ዲርማጂ በተፈጸም የአየር ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች ስለመገደላቸው ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

በምዕራብ ሽዋ ዞን ተገደው የወጡ ሰላማዊ ዜጎች በተገኙበት የታጣቂዎች የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

በዚህ ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን እና የታጣቂ ቡድኑ አባላትን ጨምሮ እስከ 70 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ120 ያላነሱ መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

'ሸኔ' ወይም የኦሮሞ ነጻነት ጦር

መንግሥት 'ሸኔ' የሚለውን እና እራሱን 'የኦሮሞ ነጻነት ጦር' ብሎ የሚጠራው ቡድን በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ በስፋት በመንቀሳቀስ ለክልሉ እና ለፌደራል መንግሥት ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

ታጣቂ ቡድኑ የሚንቀሳቀስባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች የደኅንነት እጦት ያለባቸው ሆነዋል። ይህ ቡድን ለበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ጥፋተኛ ሲደረግ ቆይቷል።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው ቡድን በጀምላ ግድያ፣ ዘረፋ፣ በንጹሃን እና በመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ፣ መንገድ በመዝጋት፣ የሕዝብ እና የመንግሥት ንብረት በማውደም፣ ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ እና በሌሎች ወንጀሎችም ይከሰሳል።

ይሁን እንጂ ታጣቂ ቡድኑ የሚቀርብበትን ክስ ሲያስተባብል ቆይቷል።

የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት ይህን ቡድን ለማጥፋት ቁርጠኛ መሆናቸውን እና በተለያዩ ጊዜ ዘመቻ መጀመራቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።