‘ለሕዝቡ ያልተገለጸው’ የኤርትራ ተሳትፎ እና የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለት ዓመታት የፈጀው የኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያበቃ ያደርጋል የተባለው የሰላም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ተፈርሟል።
ስምምነቱን ተከትሎም የኢትዮጵያ እና የህወሓት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ስለ ትጥቅ መፍታት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ለመነጋገር በኬንያ ናይሮቢ ተገናኝተው እየተወያዩ ነው።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ጦርነት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፏል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓል።
የኤርትራ ጦር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በመወገን ክልሉን ከሚቆጣጠረው ህወሓት ጋር ጦርነት ላይ መሆኑን የተለያዩ ወገኖች ሲገልፁ ቆይቷል።
ከዚህ በፊት በአገሪቱ ውስጥ ትልልቅ ጉዳዮች ሲኖሩ የማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ለሕዝቡ ይፋ የሚያደርጉ ቢሆንም ወደዚህ ጦርነት ሲገባ ግን ይህ አልታየም።
በዚህም የተነሳ መንግሥት የበርካቶችን ሕይወት በቀጠፈው በዚህ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች እንዲገቡ የተወሰነበት ምክንያትን አልገለጸም።
ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ ኤርትራውያን
ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው ሄለን ብርሃኔ የምትኖረው ኔዘርላንድስ ነው።
አባቷ የስምንተኛ ዙር ብሔራዊ አገልግሎት አባል እንደሆኑ የምትናገረው ሄለን፣ አሁንም በሠራዊቱ ውስጥ እያገለገሉ መሆኑን ለቢቢሲ ትናገራለች።
ከአባቷ በተጨማሪ ታናሽ ወንድሟ የ31ኛው ዙር ብሔራዊ አገልግሎት አባል እንደሆነ፣ ነገር ግን ቤተሰቡ ከሐምሌ 2013 ላይ ስለሱ ከሰማ በኋላ እስካሁን ድረስ ‘ይሙት ይኑር’ እንደማያውቁ ታስረዳለች።
“የታናሼ ታናሽ ደግሞ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ድንበር ሲከፈት ወደ ኢትዮጵያ ገብታለች። የእርስ በርስ ጦርነቱ ሲጀመር ትግራይ ውስጥ ነበረች። በኅዳር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ድምጿን ከሰማሁ ወዲያ ስለሷ ምንም መረጃ የለንም።”
አባቷ በግንቦት ወር 2014 ለእረፍት ወደ ቤት መጥተው እንደነበረ እናቷ እንደነገሯት የምትገልፀው ሄለን፣ “በሰኔ ወር ወደ ክፍሉ ከተመለሰ በኋላ በመስከረም መጀመሪያ ላይ አንድ ጊዜ 'ሚስድ ኮል' ስላደረገልኝ ደወልኩለት እና ‘ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀስን ነው’ አለኝ። ነገር ግን ወዴት እንደሚሄዱ ስለማያውቅ አልነገረኝም” ትላለች።
ስደተኛ ካምፕ ውስጥ አለች ብላ እያሰበች ስለጠፋችው እህቷ እየተጨነቀች ባለችበት ወቅት የወንድሟ እና የአባቷ ደኅንነትን አለመስማቷ ተጨማሪ ጭንቀት እንደፈጠረባት ትናገራለች።
ለቤተሰቦቹ ደኅንነት ሲል ስሙን እንዳንጠቅሰው የጠየቀን ሌላ ኤርትራዊ በበኩሉ፣ ከቤተሰቦቹ አባላት መካከል አምስቱ የብሔራዊ ወታደራዊ አገልግሎት አባላት መሆናቸውን ያስረዳል።
“በአገራዊ አገልግሎቱ ውስጥ የተሳተፉት ወንድሞቼ ከአንዱ በስተቀር ሁሉም በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል። አሁን በባሕር ኃይል ውስጥ ካለው የመጨረሻ ታናሽ ወንድሜ በቀር ስለ ሦስቱ ወንድሞቼ ምንም መረጃ የለኝም። በተለይም አንዱ ስላለበት ሁኔታ ምንም መረጃ ሳናገኝ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ሆኖናል” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኤርትራ ለምን በኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ተሳተፈች?
የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ለምን እንደተቀላቀለ በይፋ ባይገለጽም፣ በግብፅ የሚገኙት ኤርትራዊ ጋዜጠኛ እና ፀሐፊ ማህሙድ አቡበከር በአልጀርሱ ውሳኔ ለኤርትራ የተሰጠው መሬት ለ18 ዓመታት ያህል በህወሓት የበላይነት በተያዘው መንግሥት እምቢተኝነት ምክንያት ሳይፈጸም መቆየቱ እንደ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
“መንግሥት መሬቱን መመለስ እንደሚፈልግ እና ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ህወሓት ወደ ኤርትራ ሚሳኤል መተኮሱ እንደምክንያት ሊጠቀሱ እንደሚችሉ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ይጠቁማል።”
የአፍሪካ ቀንድ እና የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አብዱልራህማን አቡሃሺም “በህወሓት እና በኤርትራ መሪዎች መካከል ሰላም አለመኖሩ፤ ከድንበር ጦርነቱም በኋላ ተፈጥሮ የቆየው ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታን” ኤርትራ በጦርነቱ እንድትሳተፍ በመድረግ እንደምክንያት ይጠቅሳሉ።
ጋዜጠኛ ማህሙድ በበኩሉ ከጦርነቱ በኋላ የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ እንዲፈታ በአልጀርስ የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ገዢው ህወሓት ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ መሆኑን በመግለፅ፤ “ስለዚህ ግንኙነቱን ወደ ኋላ መለስ ብለን መመልከቱ ቢያንስ በኤርትራ በኩል የሚቀርበውን ክርክር እንድንረዳ ያግዘናል” ይላል።
“ይህ ግን ትስስሮቹን ለማብራራት እንጂ፣ ይህን ጦርነት ምክንያታዊ መሆኑን ለማስረዳት አይደለም” በማለትም ከጦርነቱ ይልቅ እየጠነከረ የመጣው ጥላቻና ቂም ይበልጥ እንደሚያሳስበው ይናገራል።
“የአልጀርሱ ስምምነት በመካከላቸው የቆየውን የእርስ በርስ ጠላትነት የሚደመስስ አልነበረም፣ ጠላትነቱ ከከባድ ጦርነት ወደ ቀዝቃዛ ጦርነት ብቻ ነው የተሸጋገረው” ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ አብዱራህማን በበኩላቸው።
ተጠያቂው ማነው?
በእንግሊዝ ሳውዝ ባንክ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ እና የሕግ ክፍል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ጋይም ክብረአብ ሕዝብ በአፈሳ መልክ እንዲሁም ይፋዊ ባልሆነ የክተት ጥሪ ከነልጆቹ እንዲዘምትና እንዲያዘምት ብቻ ነው የሚጠየቀው ይላሉ።
አክለውም “በትግራይ ውስጥ ስለተካሄደው ልጆቹ የተሳተፉበት ደም አፋሳሽ ጦርነት በሚመለከት በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንኳን ተነግሮት አያውቅም። ስለተፈጠረው ነገር እና እየከፈለው ስላለ ዋጋ ማንም አይነግረውም” በማለት ያብራራሉ።
በየትኛውም አገር፣ በብዙ አምባገነን መንግሥታት በሚመሯቸው አገሮችም ጭምር፣ ለጦርነት የሚያስገድድ ሁኔታ ካለ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚወስን የሚያስረዱት ፕሮፌሰር ጋይም፣ በኤርትራ ግን ይህ ተፈጽሞ እንደማያውቅ በምሳሌ ያስቀምጣሉ።
በ1992 የተቋቋመው እና 150 አባላት የነበሩት የኤርትራ ብሔራዊ ምክር ቤት ይህን አላደረገም የሚሉት ፕሮፌሰር ጋይም፣ ከጥር 2002 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለሃያ ዓመታት ያህል ተሰብስቦ እንደማያውቅ ይገልጻሉ።
አክለውም ገሚሶቹ የምክር ቤቱ አባላት መታሰራቸውን፤ አንዳንዶቹ መሰወራቸውን፣ አንዳንዶቹ በበሽታ መሞታቸውንና በርካቶችም በእርጅና ምክንያት ከሥራ እንደተስተጓጎሉ ይገልጻሉ።
ፖለቲከኛ አቶ ሰንጋል ወልደትንሳኤ በበኩላቸው፣ የኤርትራ ካቢኔም ቢሆን ከ2018ቱ [እ.ኤ.አ] የኢትዮ-ኤርትራ ዕርቅና ሰላም በኋላ አንድ ቀን ለግማሽ ሰዓት ያህል ከመሰብሰቡ ውጪ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “ሊቆጣጠሩትና ሊቋቋሙት ባልቻሉት በውስጣቸው መፈጠሩ በተነገረ ልዩነት” ምክንያት ዳግም ተገናኝቶ እንደማያውቅ ይናገራሉ።
ከዚህም በላይ 19 አባላት ያሉት የሕዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲና ለፍትህ አመራሮች ለስደት፣ ለሕመም፣ ለአካል ጉዳተኝነት እና ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ የተቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ሹማምንትም ተገናኝተው ውሳኔዎችን ማስተላለፋቸው የሚያሳውቅ መግለጫ ተሰጥቶ እንደማያውቅ ፖለቲከኛው ያስረዳሉ።
በአሁኑ ጦርነትም ኢሳያስ እና ከእርሳቸው ጋር አብረው ሲሰሩ የነበሩ ከፍተኛ የደኅንነት እና የሠራዊት ባለሥልጣናት ዋና ተጠያቂዎች ናቸው በማለት ይከሳሉ።
“በኤርትራ ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት ሁሉ ኢሳያስ ብቻውን ተጠያቂ ሊያደርገው አይችልም። ለግል ጥቅማቸው አልያም ለራሳቸው እምነትና ዓላማ ሲሉ የእሱን ውጥኖች የሚያስፈጽሙ እንዲሁም ወጣቶችን እና ሽማግሌዎችን አፍሰው ወደ ጦርነት እንዲገቡ በማድረግ በሕግና በሕሊና በየደረጃው የሚጠየቁ ሰዎች አሉ።”
አብዱራህማን በበኩላቸው “በኤርትራውያን ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ተጠያቂ ነው። የትኛውም ለሕዝብ ተቆርቋሪ የሆነ መንግሥት ጦርነትን እንደ መጀመሪያ ምርጫ አይወስድም። ይህ ወጣት ወደ ጦርነት እንዲሄድ ማነው እያዘዘው ያለው? በአሥመራ በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ እስከሆነ ድረስ ተጠያቂ ነው” ይላሉ።
በማናቸውም ሁኔታ ተጠያቂነት ካለ የሚጠይቅ ሰው መኖር እንዳለበት የሚገልፁት ፖለቲከኛ አቶ ሰንጋል፣ ተጠያቂነት አይቀርም በማለት “ሕዝብ ድምፁ ባልሰጠበት ጦርነት ውስጥ ወጣቶችን አስገድዶ በማስገባት የኢሳይያስ አገዛዝም ውሎ አድሮ በሕግ እና በታሪክ የሚጠየቅበት ጊዜ ሩቅ አይደለም” ይላሉ።
ጋዜጠኛ እና ፀሐፊ ማህሙድ አቡበከር በበኩላቸው የአንድ አገር ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው በሰላም እና በዲሞክራሲ መሆኑን በመጥቀስ፣ አሁን ኢትዮጵያውያን [የጦርነቱ ተሳታፊዎች] ደቡብ አፍሪካ ላይ ስለተስማሙ የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የድንበር ጉዳይ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር መፍታት እንዳለበት ያስረዳሉ።












