የትግራይ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ምን ሊመስል ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለት ዓመት የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነቱ በመንግሥት እና በህወሓት መካከል በተደረገው ንግግር ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ጦርነት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ የበርካቶችን ነብስ ቀጥፏል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓል።
ጦርነቱ በተካሄደባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል ውስጥ የሰብአዊ እርዳታ መቋረጥ፣ የመድኃኒት አቅርቦትና የህክምና አገልግሎቶች መደናቀፍ እንዲሁም የኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮሚዩኒኬሽን፣ ባንክ እና ሌሎች መሠረታዊ አግልግሎቶች መስተጓጎል በሕዝቡ ላይ ከባድ ፈተናን ደቅኖ ቆይቷል።
በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት ሁሉም ወገኖች ከባድ የመብት ጥሰቶችና ግድያዎችን መፈጸማቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ባወጧቸው ሪፖርቶች በተደጋጋሚ አመልክተዋል።
ከዚህም ባሻገር ጦርነቱ ካስከተላቸው ጥፋቶች መካከል አንደኛው በሕዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ማላላቱ እና ግንኙነቶችን ማሻከሩ እንደሆነ ከተለያዩ ወገኖች ይሰማል።
ይህን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት የሚያስችል ስምምነት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት ባለሥልጣናት መካከል ከሳምንት በፊት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ ውስጥ ተፈርሟል።
በዚህም የሰላም ስምምነትም ላይ ጦርነቱ ያስከተላቸው ቀውሶችን ለማስተካከል የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደረጉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በቀጣይነት በሚደረጉ ንግግሮች ላይም ይኸው ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጠው ይታመናል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ጦርነቱ ባስከተለው መቋሰልና ጉዳት ምክንያት ቀጣዩ የትግራይ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? የትግራይ ሕዝብስ ከጦርነቱ በፊት እና በኋላ ባለው ምልከታ ላይ ልዩነት ተፈጥሯል? የህወሓት እና መንግሥት ሚናስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት እየተነሱ ናቸው።
ከዚህ አንጻር ያሉትን ጉዳዮች ለመዳሰስ ፖለቲከኛ፣ጋዜጠኛ እና የትግራይ ተወላጆቸን ምልከታ ለመዳሰስ ሞክረናል።
የሰላም ስምምነት
ለአስር ቀናት ያህል በደቡብ አፍሪካዊቷ ከተማ ፕሪቶሪያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ድርድር ረቡዕ ጥቅምት 23/2015 የመጀሪያውን የብስራት ዜና አሰምቷል።
በዚህም ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት ዘላቂ የተኩስ አቁም ለማድረግ ሲስማሙ ህወሓት ትጥቅ እንዲፈታም ተስማምተዋል።
“የሰላም ድርድሩ ከምንም በላይ ጦርነቱን ማስቆም መቻል አለበት” ይላሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሔል ባፌ (ዶ/ር)።
አክለውም “ከጦርነቱ በፊት ወደ ድርድር እንዲመጡ ብዙ ጊዜ ቢጠየቁም ፈቃደኛ አልሆኑም። አሁን ይህ የሁለቱም የመጨረሻ አማራጭ ነው። ከዚህ በኋላ ሕዝብ ነው የሚወስነው” ብለዋል።
ሰብሳቢዋ በተነፃፃሪ በዚህ ጦርነት እጅግ የተጎዳው የትግራይ ሕዝብ “አረፍ ማለት እንዳለበት ይናገራሉ።
ስለዚህም የትግራይ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ በእጃቸው ነው ብለን እንድንተውላቸው፤ተፅዕኖው፣ጫናው፣ አፈናው ሊነሳላቸው እንደሚገባ ይጠቅሳሉ።
“ውሳኔው የሕዝቡ መሆን አለበት”
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በተደረሰው ስምምነት በክልሉ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ የሽግግር አስተዳደር እንደሚመሰረት ተገልጿል።
ጦርነቱ ባስከተለው ቁስል ምክንያት በርካታ የትግራይ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ተፈጥሯል። ይህ ሁኔታ በእርቅ፣ በሽግግር ጊዜ ፍትሕ እና በካሳ የሚስተካከል ነው ብለው የሚያምኑ እንዳሉት ሁሉ፣ የማይጠገን ክፍተት ተፈጥሯል የሚሉም አሉ።
ጦርነቱ ክልሉ ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ጋር ያለውን ትስስር ጎድቶታል ከሚሉት መካከል በዬል ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ዶክትሬት ድግሪ ተመራማሪ የሆኑት ጎይቶም ገብረልዑል “ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና የመቀጠሏ ዕድል በጣም ጠባብ ነው” ይላሉ።
በሁለት ዓመቱ ጦርነት ወቅት ትግራይ ውስጥ የተፈጸመው ግፍ “ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ ቢመጣ እንኳ አንድ የትግራይ ሰው የዛሬ 10 ወይም 20 ዓመት ሌላ ጭፍጨፋ ላለመኖሩ ምን ዋስትና አለ ብሎ መጠየቁ አይቀርም” ይላሉ ጎይቶም።
“ስለዚህ ወደፊት ተመሳሳይ ግፍ እንዳይፈፀምብን የራሳችንን አገር ማቋቋም ይኖርብናል” የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው።
ለዚህም የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ለሕዝቦች የሰጠው መብት መሆኑን በመጥቀስ “ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ። ይህንን ፍላጎት መቃወም የኢትዮጵያን ሕገ-መንግሥት እንደመቃወም ነው” ይላሉ።
ይህ አይነቱ ፍላጎት በበርካታ የትግራይ ተወላጆች በተለይም በውጭ አገራት በሚኖሩት ዘንድ በስፋት ሲያንጸባረቅ የቆየ ሲሆን፣ ነዋሪነታቸው በውጭ የሆኑና ቢቢሲ ያነጋገራቸው የትግራይ ተወላጆች ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው።
ሌሎች ደግሞ አሁን ቀዳሚው ጉዳይ መሆን ያለበት የጦርነቱ መቆምና በችግር ውስጥ ያለው የክልሉ ሕዝብ ድጋፍ የሚያገኝበት እንዲሁም መልሶ የሚቋቋምበትን መንገድ መፈለግ ነው ይላሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢዋ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው “ህወሓት ሊወስን እንዳልቻለ እስከታየ ድረስ ሕዝቡ የሚወስንበት ዕድል ሊፈጠር ይገባል።”
ጋዜጠኛ እና የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጣ መሥራች የሆኑት ፀዳለ ለማም በተመሳሳይ ውሳኔው የሕዝቡ ሊሆን ይገባል የሚል አመለካከት አላቸው።
“ህወሓት በኢትዮጵያዊነት የሚያምን እና ፌደሬሽኑን የሚደግፍ ነው፤ ይሁንና ይህንን መወስን የሚችለው ፓርቲ ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ ነው” ይላሉ ጋዜጠኛዋ።
የትግራይ ሕዝብ ያሻውን የማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ መብት አለው የሚሉት ፀዳለ “ሪፈረንደም መጠየቅ ሕገ-መንግሥታዊ ነው። የትግራይ ሕዝብ ይህን ከፈለገ ህወሓት እንኳ ሊከለክለው አይችልም” ሲሉ ያስረዳሉ።
ራሔል (ዶ/ር) ህወሓት ጦርነቱን አቁሞ ከሦስት አስርታት በላይ ካስተዳደረው የክልል ሥልጣን ሊወርድ ይገባል የሚል እምነት አላቸው። መንግሥትም ሕዝቡ የፈለገውን ያደርግ ዘንድ ሊያመቻች ይገባልም ይላሉ።
“መንግሥት መሠረታዊ ነገሮችን አሟልቶ ኃላፊነቱን ለትግራይ ሕዝብ ሊተው እንደሚገባ አምናለሁ። ህወሓትም እጅ መስጠት ካቃተው አካባቢውን ለቆ ይውጣ” ሲሉ ያክላሉ።
ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል የሚያስረዱት ፖለቲከኛዋ “የትግራይ ሕዝብ ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ፤ የራሱን አካባቢ አስተዳድሮ፤ ምን ይበጀናል የሚለውን ውሳኔ እንዲሰጥ” መንግሥት ማመቻቸት እንዳለበት በመጥቀስ ነው።
ሁለት ዓመት ባስቆጠረው የሰሜኑ ጦርነት የትግራይ ሕዝብ ስለወደፊቱ ዕጣ ፈንታው በተመለከተ የአመለካከት ለውጥ አድሮበት ይሆን? ተብለው የተጠየቁት ጋዜጠኛ ፀዳለ ሊካድ የማይችል ሐቅ እንዳለ ይናገራሉ።
“የኤርትራ ሠራዊት ገብቶ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን በማየት ማንም እንደሌላቸው ወይም እንደተተዉ ሊሰማቸው ይችላል። ስለዚህ የኢትዮጵያ አገረ-መንግሥት ላይ ያላቸው አቋምና አመኔታ ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበረው ሊሆን አይችልም።”
በታሪክም በእምነትም ኢትዮጵያን ያለ ትግራይ ማሰብ እንደማይቻል የሚናገሩት ፀዳለ፤ “ለኢትዮጵያ ያላቸው ሚና ይታወቃል። ለኢትዮጵያ በታሪክ፣ በባሕል እና በሌሎችም መስኮች ያላቸው ሚና የትየለሌ ነው። ነገር ግን ይህንን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ከሠራው ጋር እንደገና መገምገም ያስፈልጋል” ሲሉ ያክላሉ።
የኤርትራ ጦር ተሳትፎ
ጦርነቱን አብዝተው በመቃወም የሚታወቀቱ ፀዳለ የትግራይ ሕዝብ “እንደተተወ ቢሰማው ተፈጥሮአዊ ነው። ሕዝቡ ተረስቷል፤ መረሳት ብቻም ሳይሆን ለጎረቤት በቀለኛ አገዛዝ ተላልፈው ተሰጥተዋል” ይላሉ።
ጋዜጠኛዋም ሆኑ ፖለቲከኛዋ የኤርትራ ጦር በዚህ ጦርነት መሳተፉ ነገሮችን የበለጠ አወሳስቧል በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ።
“የኤርትራ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ለትግራይ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ሁኔታዎችን አወሳስቦብናል። ይህ የሉዓላዊነት ጥያቄ ነው። ለዚህ ተጠያቂው የፌዴራል መንግሥቱ ነው” ይላሉ ራሔል።
ፀዳለ ደግሞ፤ “የትግራይ ሕዝብ ደኅንነት ለውጭ ወራሪ ኃይል ተላልፎ በተሰጠበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ መለየት እንፈልጋለን ቢሉ የሚገርም አይሆንም” ይላሉ።
ፖለቲከኛዋ አስቀድመን የራሳችንን ችግር መፍታት አለመቻላችን ነው የኤርትራ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያደረገው ሲሉ ይከራከራሉ።
“እኔ በግሌ መጀመሪያ የአገር ውስጡን ችግር መንግሥትና ህወሓት ከፈቱት የኤርትራ መንግሥት ጉዳይ ብዙ ችግር ይሆናል ብዬ አላስብም። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ከውስጣችን ችግር የተነሳ ነው። መጀመሪያ እሱን ቀድመን መፍታት ይኖርብናል።”
ጋዜጠኛዋ በበኩላቸው የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤርትራን ተሳትፎ አለማውገዙ ሁኔታው እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል የሚል እምነት አላቸው።
“ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ቡድኖች የኤርትራ ኃይሎች እንዲወጡ የጠየቀ አለን? እውነት እንነጋገር ከተባለ የኤርትራ ኃይሎች እንዲወጡ ጥሪ ያደረገ የለም። በዚህ ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ ምን እንዲሰማው ይጠበቃል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰብሳቢዋ ራሔል (ዶ/ር) በበኩላቸው ተወደደም ተጠላም የህወሓት የሥልጣን ዘመን እየከሰመ መጥቷል ብለው ያምናሉ።
“ህወሓት ሳይፈልግ ጊዜው አብቅቷል። አንድ ነገር አድጎ መክሰሙ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ለምን በእነሱ የተሳሳተ አካሄድና ወቅቱን ባላገናዘበ ፖለቲካ ሕዝብ ይጎዳል?”
ጋዜጠኛዋ ፀዳለ ለማ፣ፖለቲከኛዋ ዶ/ር ራሔል ባፌ፣ ጎይቶም ገብረልዑልም ሆኑ ሌሎች የትግራይ ተወላጆች እንደሚሉት የትግራይ ሕዝብ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በእራሱ በሕዝቡ መወሰን እንደሚኖሩበት አጽንኦት ይሰጣሉ።
-------
*ማስታወሻ፡ ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ቃለ ምልልስ የተደረገው በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ስምምነት ከመደረጉ በፊት ነው።












