“ይድረስ ከተወለድሽ ላላየሁሽ ልጄ. . .” ወደ ትግራይ የተላኩ ደብዳቤዎች

ደብዳቤዎች

የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከቀጠፈው ሕይወት፣ ካጎደለው አካል፣ ካቆሰለው ሥነ ልቦና በተጨማሪ የትግራይን መሠረተ ልማት በዓመታት ወደኋላ መልሷል።

ከዚህም ባሻገር ስልክ፣ ኢንተርኔት እና ባንክ ከተቋረጡ ሁለት ዓመት ደፍነዋል።

የቤተሰብ፣ የወዳጅ ዘመድ፣ የጓደኛ ድምጽ መስማት ብርቅ ከሆነ ሰነባበተ። ስልክ ብድግ አድርጎ ወደሚወዱት ሰው መደወል ሩቅ ሆነ።

አምና የተሠራ አንድ ቪድዮ ላይ መቀለ ያሉ ወጣቶች “የስልክ ድምጽ ስትሰሙ ምን ይሰማችኋል?” ተብለው ሲጠየቁ፣ አብዛኞቹ “አላርም ነው ብዬ ነው የማስበው” ብለው ነበር የመለሱት።

ዕድለኛ የሆኑ ሰዎች፣ በዋነኛነት በእርዳታ ሠራተኞች አማካይነት ለቤተሰቦቻቸው የድምጽ መልዕክት፣ ፎቶ ወይም ቪድዮ ይልካሉ።

ታዲያ ይሄ መልዕክት የሚደርሰው ከሳምንታት ገፋ ሲልም ከወራት በኋላ ሊሆን ይችላል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ አመራሮች መካከል የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት በነበረባቸው አምስት ወራት፣ የትግራይ ተወላጆች ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች በመጓዝ ለቤተሰቦቻቸው ስልክ ይደውሉ ነበር።

በክልሉ ስልክ እና ኢንተርኔት ከተቋረጠ ወዲህ፣ እዚያው ትግራይ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ከተሞች ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ ከተማ ውስጥ ያሉ ሰዎችም እንደቀድሞው እንዳሻቸው አይገናኙም። እናም እንደ ጥንቱ ደብዳቤ ለመጻጻፍ ተገደዋል።

ቢቢሲ የእርስ በእርስ ጦርነቱን ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያ አስታኮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን ትግራይ ወዳሉ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው ደብዳቤ እንዲጽፉ ጠይቋል።

በዚህ ዘገባ ከተካተቱት ደብዳቤዎች የተወሰኑት ቀደም ሲል የተጻፉ ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ ከዚህ ዘገባ ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ባቀረበው ጥያቄ የተጻፉ ናቸው።

ቀድሞ ጽፈው የላኳቸውን ደብዳቤዎች በድጋሚ ጽፈው የላኩልንም አሉ። ከአንድ ደብዳቤ በስተቀር የተቀሩት ደብዳቤዎች በፀሐፊዎቹ በራሳቸው የእጅ ጽሑፍ ነው የተቀመጡት።

የትግራይ ደብዳቤዎች

“በሐሳብ እንጂ በአካል የማላውቃት ልጄስ እንዴት ናት?”

ሃፍቶም የሚኖረው ደቡብ አፍሪካ ነው። ትግራይ ካለች ባለቤቱ እንዲሁም ከበኩር ልጁም ጋር ከተገናኘ ይኸው ሁለት ዓመት ደፈነ።

ጦርነቱ ሲነሳ ባለቤቱ ነፍሰ ጡር ነበረች። ሁለተኛ ልጁ ስትወለድ ከባለቤቱ አጠገብ አልነበረም። ልጁንም ከተወለደች ጀምሮ አላያትም።

“ምግብ ልበላ እንደቀረብኩኝ፣ እናንተ ትታዩኝ እና ወንጀለኝነት ይሰማኛል። ከዚያ ሳልበላ አድራለሁ” ይላል ሃፍቶም።

በዐይኑ ሊያያት ስላልቻለው ልጁ “በሐሳብ እንጂ በአካል የማላውቃት ልጄስ እንዴት ናት? ስሟን ማን እንዳልሻት ባላውቅም እኔ ግን ‘ናፍቆት’ ብያታለሁ” ሲል በደብዳቤው ይገልጻል።

ደብዳቤ

“ሁሉም ነገር፣ መኖርን ጨምሮ ትርጉም ያጣብኛል”

ስሜ አይጠቀስ ብሎ ቀጣዩን ደብዳቤ የላከልን የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው። ትግራይ ካሉ ቤተሰቦቹ ጋር ከተነጋገረ ሁለት ዓመት ተቆጥሯል።

በደብዳቤው “በሕይወት ካላችሁ፣ ውድ ቤተሰቦቼ እንደምን አላችሁ?” ሲል ይጠይቃል። ያለፈውን ሁለት ዓመት ሲገልጽም “የበረታ ሐዘን፣ ጭንቀት፣ ድባቴ፣ መከራ የነገሠበት፤ አጥንት ስር ድረስ ዘልቆ የሚገባ ናፍቆትና መብሰክሰክ ያየለበት ነው” ይላል።

ደብዳቤ
የምስሉ መግለጫ, ገጽ 1
ደብዳቤ
የምስሉ መግለጫ, ገጽ 2

“ልጄ በሕይወት አለ? የትም ባልደርስም፣ ንገሪኝ”

ይህን ደብዳቤ የላከችልን ከኢትዮጵያ ውጭ የምትኖርና ከልጇ ጋር ሁለት ዓመት ገደማ ለማውራት ያልቻለች እናት ናት።

ቀድሞ እናቷን እና ልጇን ገንዘብ እየላከች ታስተዳድር ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት ይህን ማድረግ አልቻለችም።

በመድኃኒት ማጣት አስም ታማሚ ልጇ እንደሚሰቃይና ከወራት በፊት የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ በሰው በሰው አግኝታ ኢንሄለር እንደላከች ነግራናለች።

በትግርኛ የጻፈችው ደብዳቤ የአማርኛ ትርጉም እንዲህ ይቀርባል።

ለውድ እናቴ ሓዳስ እቁባይ፡

ሓዳስዬ እንዴት ነሽ? አመል ሆኖብኝ ነው እንጂ ያለሽበትን ሁኔታ እንኳን ለጠላትም አይስጠው።

ሓዳስዬ፣ የልጄን ሁኔታ እውነቱን እንድትነግሪኝ ነው ይሄን ደብዳቤ የምጽፍልሽ። የአስም በሽታው እንዴት ሆነ? ከመድኃኒት ውጪ አንዲት ሌሊት ማሳለፍ እንደማይችል አውቃለው።

እስትንፋስ አጥሮት እህ. . . እህ. . . እህ. . . ሲል ይታየኛል። ሓዳስዬ ልጄ በሕይወት አለ? የትም ባልደርስም ንገሪኝ። አሳድገሽዋልና ላንቺ ይቀርባል። ስለዚህ አደራሽን እውነቱን ንገሪኝ።

በሕይወት ከቆየልኝ ግን ይህ ሰው አንዱን ኢንሄለር ላድርስልሽ ብሎኛል እና ልኬልሻለሁ።

ሓዳስዬ፣ እስከዚያው ለምታምኚው ጸሎት አድርጊ።

ቻው

በሰላም ያገናኘን

ሳራ

ደብዳቤ

“ትግራይ መምጣት ወደ ሕዋ እንደመምጠቅ ከባድ ሆኗል”

በአዲስ አበባ የምትኖረው የዚህ ደብዳቤ ፀሐፊ በጦርነቱ ሳቢያ ቤተሰቦቿን መጠየቅ፣ ከእነሱ መስማትም እንዳልቻለች ትናገራለች።

ለእናቷ እና እህቶቿ የላከችውን ደብዳቤ “የተወደድሽው እማዬና ቤተሰቦቼ፣ እናንተን ለማየት የትግራይን መሬት ከረገጥኩ ሁለት ዓመት ሊሆነኝ ነው” ብላ ነው የምትጀምረው።

አክላም “ከስጋት ነጻ ሕይወት ሕልም በሚመስልበት ሁኔታ ውስጥ መኖር እንዴት እያደረጋችሁ ነው? ሕጻናቱስ የድብደባውን ድምጽ ለመዱት?” ትላለች።

ደብዳቤ

“ሁለቱ ዓመታት በዚች ምድር የኖርኩትን ያህል ረዘሙብኝ”

የዚህ ደብዳቤ ፀሐፊ ሰለሞን ኡጋንዳ ነው የሚኖረው። ከቤተሰቦቹ መስማትም ይሁን በችግራቸው ጊዜ መድረስ አለመቻሉን በደብዳቤው ይገልጻል።

“አባቴ መታመምህን ሰምቼ ልደርስልህ ባለመቻሌ ከእንባዬ ውጪ ሌላ አቅምና አማራጭ አላገኘሁም” ይላል።

አክሎም “እናቴ ሲያሰቃይሽ ለነበረው በሽታሽ መድኃኒት በማጣትሽ ቀኑ ያለፈበት መድኃኒት ስትወስጂ መክረምሽን ስሰማ መፈጠሬን እስክጠላ አዘንኩ” ይላል ሰለሞን።

ደብዳቤ

“መልዕክትሽ ሲደርሰኝ ፊቴ እንዴት በርቶ እንደሚውል”

ሌላው ቢቢሲ የደረሰው የፍቅር ደብዳቤ ነው። ስሜም ያለሁበትም አይጠቀስ ያለን ፀሐፊ፣ ትግራይ ከምትኖር ፍቅረኛው ጋር በአብዛኛው በደብዳቤ ነው የሚያወሩት።

እሱም ደብዳቤውን የሚያደርስ ሰው ከተገኘ። አልፎ አልፎ ኢንተርኔት ያለበት ቦታ መሄድ ከቻለች የድምጽ መልዕክት ትልካለች።

ጦርነቱ ባይነሳ ኖሮ ጥንዶቹ አምና ለመሞሸር አቅደው ነበር።

ፀሐፊው ደብዳቤውን በኮምፒውተር ጽሑፍ ከላከልን በኋላ ቢቢሲ ቀንጭቦ በሦስተኛ ወገን እጅ ጹሑፍ አዘጋጅቶታል።

በትግርኛ የጻፈው ደብዳቤ የአማርኛ ትርጉም እንዲህ ይቀርባል።

ደብዳቤ

የእኔ ማር እንዴት ነሽ? ደኅና ነሽ? እንዴት እያለፍሽው ነው? እንዲሁ ነው እንጂ፣ የኔ ጣፋጭ፣ ጠንካራ እንደሆንሽ፣ የሚመጣውን ተቋቁመሽ የነገን ተስፋ ይዘሽ እንደምትኖሪ አልጠፋብኝም።

እኔ ደኅና ነኝ፤ [አንድ ሰው] መሄዴ ስለሆነ መልዕክት ካለህ ብሎኝ እየተቻኮልኩ፣ ካፌ ውስጥ ምሳ እየበላሁ ስለነበረ ኤርፎን አድርጌ ድምጼን ስለቀዳሁት እንጂ ደኅና ነኝ። ሰላም ነኝ። የሚገርምሽ ጨጓራዬን እንኳን አሞኝ አያውቅም።

መልዕክትሽ ሲደርሰኝ ፌቴ እንዴት በርቶ እንደሚውል እና እያንዳንዱ መልዕክትሽን እንዴት እንደማጣጥመው፣ ይሄ አልፎ እናወራው ይሆናል።

ምን እንደሚያስደስተኝ ታውቂያለሽ? እያንዳንዱ ቃላቶችሽ ይገርሙኛል። እያንዳንዱን ቃላቶችሽን እያነሳሁ ጓደኖቼን ስጎርርባቸው ነው የምውለው።

ላንቺ የምኖር፣ የምወድሽ ነኝ።

እንገናኛለን!

አደራ እንዳትጨነቂብኝ። የምትፈልጊው ጠይቂኝ፤ ሁሉንም እሆንልሻለው።

Love you