ከባንክ አገልግሎት ወደ ተቆራረጠችው ትግራይ ገንዘብ ለመላክ የሚከፈለው ከባድ ዋጋ

ራያ ቆቦ ውስጥ ወደ ትግራይ ሊያልፍ ሲል በቅርቡ ተያዘ የተባለ ገንዘብ

የፎቶው ባለመብት, Social Media

ላለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ በቆየችው ትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ሕይወት ከባድ ሆኗል።

በርካቶች ከጦርነቱ በፊት የነበራቸውን ሕይወት እና ጓደኝነት፣ ትምህርት እና ሥራ፣ ከምንም በላይ ሰላምን ይናፍቃሉ።

የታመሙ ሮጥ ብለው የሚታከሙበት የሕክምና ተቋም ህንጻው ብቻ ቀርቷል።

ሮጥ ብለው ያገኙትን የሚሸምቱበት ሱቅ ባዶውን ያዛጋል።

ያለቻቸውን በውድ ዋጋ የሚሸጡ ነጋዴዎች ጋር ለመሄድ ደግሞ ገንዘብ ወሳኝ፤ ግን ከየት ይምጣ።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው አቶ አብርሃ ይሕደጎ፣ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የመዝገብ ቤት ሠራተኛ ነበር።

አሁን ላይ ግን የሚከፈለው ገንዘብ እንደሌለና ሥራውን እንዳቆመ ገልጿል።

“ጦርነቱ ያስጨንቀናል፤ የምንኖረው ሕይወትን እንኳ ምን ብዬ እንደምገልጸው አላውቅም - እየባሰበት ነው። እኔ፤ አልፎ አልፎ የሚላክልኝን ገንዘብ ጠብቄ ልጆቼን ለመቀለብ እየጣርኩ ነው። እዚህ ሁሉንም ነገር ስለተወደደ ገንዘቡ ጥቅም የለውም፤ ምንም ነገር መግዛት አይቻልም” ይላል።

በባሕር ማዶ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው ችግራቸውን ጠቅሰው የድጋፍ ተማጽኖ ድምጽ ያሰማሉ።

ገንዘብ ግን ወደ ትግራይ ለማስገባት ውጣ ውረዱ ከባድ ነው።

ለዚህም ነው የትግራይ ተወላጅ የሆኑት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ሳይቀር ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ ለመላክ መቸገራቸውን የተናገሩት።

ጦርነቱ ባንክን ጨምሮ የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ምክንያት በመሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠር የክልሉ ሕዝብ የባንክ አገልግሎት አያገኝም።

የፋይናንስ አገልግሎቶች መቋረጥ ደግሞ ወደ ክልሉ ገንዘብ መላክን እጅግ አስቸጋሪ እና ብዙ ወጪ የሚጠይቅ እንዲሆን አድርጎታል።

ይሄንን ተከትሎ አንዳንድ ቤተሰቦች ገንዘብ ለማግኘት ንብረታቸውንና ሌላ አለኝ የሚሉትን ነገር ሸጠዋል። አንዳንዶች ደግሞ በውጭ አገራት የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው እጅ ይጠባበቃሉ።

ሰላም ባለኸኝ በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ-ጾታ ባለሞያ ስትሆን፣ በትግራይ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ጥቂት ወራት ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝታ ነው ወደ ቤልጅም የሄደችው።

አሁን ግን በጦርነቱ ምክንያት ወደ ትግራይ መመለስ እንዳልቻለች ትናገራለች።

እንደ ሰላም ያሉ በውጭ አገር ሆነው ቤተሰቦቻቸውንና ጓደኞቻቸውን በገንዘብ እያገዙ የሚገኙ ሰዎች፣ ወደ ትግራይ ገንዘብ ለመላክ እጅግ የተወሳሰበና ዋስትና የሌላቸው መንገዶችን ይጠቀማሉ።

ሰላም “በሕይወት ለመቆየት፣ እንባ እየተናነቃቸው ገንዘብ ላኩልን ስለሚሉን፣ የምንልከው ገንዘብ ከግማሽ በላይ እየተወሰደብንም ቢሆን ሕጋዊ ያልሆነ መንገድ እንድንጠቀም ተገደናል” ትላለች።

እሷ፣ ከአንድ ዓመት በላይ ገንዘብ ለመላክ የተለያዩ መንገዶችን ስትጠቀም መቆየቷን ትናገራለች።

ገንዘብ ለመላክ ያሉ አማራጮች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመጀመሪያው አዲስ አበባ ያሉ ሰዎችን መጠቀም ነው።

አዲስ አበባ ያሉ አቀባባዮች መቀለ ከሚኖሩ ገንዘብ ካላቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት አላቸው።

አዲስ አበባ ለሚገኙት ሰዎች በስማቸው በባንክ አካውንታቸው ውስጥ ገንዘብ ካስገቡ በኋላ፣ ለማን እንደሚሰጥ እና የላኪ ስም በስልክ ይነገራቸዋል።

ከባንክ አገልግሎት ከራቀች ረዥም ወራትን ባስቆጠረችው መቀለ የሚኖሩ ባለሀብቶች ጋር ደውለው ምን ያህል ገንዘብ እንደተላከ፣ መቼ መውሰድ እንደሚቻል ይነጋገራሉ።

ከዚያም መልሰው ለገንዘቡ ላኪ መረጃውን በማስተላለፍ ኮሚሽናቸውን ተቀብለው ሥራቸውን ይጨርሳሉ።

እዚህ ላይ ገንዘብ ላኪ እና ተቀባይ መረጃ የመለዋወጥ ድርሻውን ራሳቸው ይወጣሉ።

ሌላኛው ገንዘብ መቀባበያ መንገድ ደግሞ በአፋር እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ እና ገንዘብ በማዘዋወር ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎችን መጠቀም ነው።

ይህ የገንዘብ ዝውውር ግን አንድ ስምምነት ይፈልጋል።

መጀመሪያ ላኪው ከገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሰረት ከ30 እስከ 50 በመቶ የድለላ ዋጋ [ኮሚሽን] እንዲከፍል ይስማማል።

ሁለቱም የሚያስማማቸው መጠን ላይ ከደረሱ በኋላ ተቀባዩ ቀሪው ገንዘብ ይደርሰዋል።

በአፋር ክልል ያለው እንቅስቃሴ የሚከፈለው ገንዘብ አዲስ አበባ ካለው ዝቅ ያለ ቢሆንም፣ ገንዘቡ ተቀባዩ ጋር እስኪ ደርስ እስከ ሦስት ወር ሊወስድ እንደሚችል ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።

ተራ በቃል የሚፈጸም ንግግር ብቸኛው ገንዘብ ላኪው ያለው መተማመኛ ሲሆን፣ አንዳንድ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ገንዘቡን ካደረሱ በኋላ የተቀባዩን ድምጽ ወይም ምስል ቀርጸው ላኪው ጋር በመላክ ድርሻቸውን እንደተወጡ ያረጋግጣሉ።

ሰላም እነዚህ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅማባቸዋለች።

አንድ ጊዜ “ወንድሜ ታሞ ስለነበረ፣ የሚታከምበት ገንዘብ ቶሎ ብላችሁ ላኩ ስለተባልን 67 ሺህ ብር ላኩኝ። ቤተሰቦቼ የደረሳቸው ግን 30 ሺህ ብር ብቻ ነበር። በዚህ በጣም ተበሳጭቻለሁ” ትላለች።

የዚህ ምክንያት የገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ መስመር ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ትግራይ የተዘረጋ ስለሆነ፣ የሚላከው ገንዘብ ተቀባዩ እጅ እስኪደርስ በርካታ የጥቅም ተካፋይ ሰዎች ስላሉ እንደሆነ ይነገራል።

ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ያነጋገረው በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ አንድ ግለሰብ “የምንወስደው ኮሚሽን ሁሉ ወደ ኪሳችን አይገባም። አንድ ገንዘብ ከባንክ ስናወጣ ለበርካታ ሰዎች የሚሆን ስለምናወጣ እነሱም የሻይ ይፈልጋሉ። በተጨማሪም ወደ ትግራይ ብዙ ገንዘብ ይዞ መግባት ከባድ እና መሰናክሎች የበዛበት ነው። እነዚህን በገንዘብ እየሸፈንን ነው የምንሄደው” ብሎ ነበር።

‘ስድስት ሺህ ዩሮ ተቀብሎኝ ጠፋ’

ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ 616 የባንክ ቅርንጫፎች በመዘጋታቸው ምክንያት ወደ ባንኮቹ ገንዘብ መላክም ሆነ፣ በትግራይ ክልል ከተከፈቱ የሂሳብ ቁጥሮች ገንዘብ ማንቀሳቀስ አይቻልም።

አሁን ያለው የገንዘብ ዝውውር ሰንሰለት እጅግ አደገኛ እና የከተማ አስተዳደሮች እና የፀጥታ አካላት ቁጥጥር የሚያደርጉበት ስለሆነ፣ በርካታ ሰዎች ገንዘባቸው በተለያየ መንገድ ጠፍቶ መቅረቱን ይናገራሉ።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የቆቦ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በኩል ሲያልፍ የነበረ ሦስት ሚሊዮን ብር በፀጥታ አካላት ቁጥጥር ላይ መዋሉን አስታውቆ ነበር።

በዚህ መሠረት የገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ መንገድ ላይ ፍተሻ ሲኖር የያዙት ገንዘብ እንደሚወረስባቸው ይናገራሉ።

ሰላም ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በአፋር ክልል በኩል ያለውን የገንዘብ ዝውውር ተጠቅማ ወደ ትግራይ የላከቸው ስድስት ሺህ ዩሮ፣ ገንዘቡን እንዲያደርስ የተቀበለው ግለሰብ እጅ ላይ መቅረቱን ትናገራለች። ይህ የበርካታ ሰዎች ላይ ደርሷል።

“ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ላይ አስተማሪ ነው፤ አንዱ ጓደኛችን በእሱ በኩል የላከው አንድ ሺህ ዩሮ በሦስት ቀን መቀለ ደረሰ። የሚያስከፍለው ኮሚሽን 22 በመቶ ስለነበረ፣ የሚቀንስልን በማግኘታችን ደስ አለን። ‘በርከት አድርጋችሁ የምትልኩ ከሆነ ለእናንተም የምትከፍሉት ይቀንስላችኋል፣ እኔም አልመላለስም’ ስላለን የተለያዩ ሰዎች ጠይቄ 6 ሺህ ዩሮ ላኩለት” ትላለች።

ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 3 ሺህ ዩሮ የራሷ ሲሆን ቀሪውን የጓደኞቿ ነበር። ገንዘቡ በወቅቱ በነበረው የባንክ ምንዛሪ ከ327 ሺህ ብር በላይ ይገመታል።

“ባንኮች ቢሰሩ እንዲህ ላለ ችግር አንዳረግም ነበር፤ ግን ደግሞ ቤተሰቦቻችን በሕይወት እንዲቆዩልን ስለምንፈልግ የጭንቅ አማራጮች እንድንወስድ ተገደናል” ስትል ትናገራለች።

ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀሩት ጦርነት እንዲያበቃ በተለያዩ ወገኖች ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በክልሉ ተቋርጠው የሚገኙት ባንክን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ የሚደረገው ግፊት ይጠቀሳል።

‘ሁሉም ሰው ገንዘብና መድኃኒት ይጠይቃል’

በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ እንደ ሳተላይት ስልክ ያሉ መሣሪያዎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የእርዳታ ተቋማት የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎች ሆነው ቆይተዋል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር እነዚህ የሳተላይት ስልኮችን ተጠቅሞ ነዋሪዎች ከክልሉ ውጪ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው ጋር ለማገናኘት ሲሰራ ቆይቷል።

እስከ አሁን ማኅበሩ “በጦርነት እና ግጭት የተለያዩ” ሰዎች 115 ሺህ የሚጠጉ የስልክ ጥሪዎች እና መልዕክቶች እንዲያስተላልፉ ማድረጉን ይገልጻል።

ወደ ክልሉ እርዳታ የጫነ መኪና ሲያመላልስ የነበረ ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈቀደ አሽከርካሪ የፌደራል ኃይሎች በትግራይ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ሦስተኛው ዙር ጦርነት እስከተነሳበት ወቅት በነበሩ የተለያዩ ግዜያት እርዳታ ሲያደርስ ነበር።

“መንገድ ላይ ብዙ ነገሮች አሉ፤ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰው ውድመት በየቦታ ይታያል። የተቃጠሉ መኪኖች፣ የወደሙ መኖሪያ ቤቶች በርካታ ናቸው። ጦርነቱ መንገድ ላይ የሚታይ ነው የሚመስለው” ይላል።

በክልሉ በተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች ያጋጠመ ሰፊ ማኅበራዊ ቀውስ መኖሩን የሚናገረው አሽከርካሪው፣ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከአዲስ አበባ ሲነሱ ገንዘብ አድርሱልን ከሚሉ ሰዎች ገንዘብ ተቀብለው እንደሚሄዱ ይገልጻል።

“በትግራይ ሁለንታዊ ችግር አለ፤ መንገድ ላይ ‘እባክህን ገንዘብ ወይ መድኃኒት አምጣልን’ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ብዙ ነው፤ በተለይ የካንሰር ህሙማን። ከእዚያው ለመግዛትም አቅም የላቸውም፤ ሁሉም ሰው ግን ገንዘብ ይጠይቃል።”

የጦርነቱን ዳግም ማገርሸት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ወደ ትግራይ ሲያደርሰው የነበረው ሰብአዊ እርዳታን እንዳቆመ ባለፈው የነሐሴ ወር አስታውቆ ነበር። በዚህ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ይገልጻል።

“እንዲህ አይነት ጦርነት ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም፤ በዚህ ዘመን እናትህ በሕይወት እያለች ለአንድ ቀንም ቢሆን ድምጿ በስልክ አለመስማት ከባድ ነው። በየቀኑ ሰዎች ሞቱ፣ የአየር ጥቃት ተፈጸመ፣ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ ነው የሚሉ ዜናዎች ስሰማ ይጨንቀኛል” የምትለው ሰላም ጦርነቱ የሚቆምበትን ጊዜ በጉጉት እየጠበቀች መሆኗን ትናገራለች።