የሰላም ድርድር ምን መምሰል አለበት? የአፍሪካ ሕብረትስ የኢትዮጵያን የርስ በርስ ጦርነት መፍታት ይችላል?

የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለሁለት ዓመታትየዘለቀው ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ የርስ በርስጦርነት መቋጫ በቅርብ ይታይ ይሆን?

የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎችን የሚወክሉ ልዑካን ቡድኖች የሠላም ውይይት ለማድረግ ደቡብ አፍሪካ ከትመዋል ከርመዋል።

የውይይቱ ዓላማም ደም አፋሳሽ ግጭቱ ቆሞ መፍትሔ ለማፈላለግና ሰላም ማስፈን ነው።

ይህ የርስ በርስ ጦርነት በሰላም እንዲፈታ ውይይት እንዲደረግ ግፊት ሲቀርብ የመጀመሪያው ባይሆንም የሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ተወካዮች ይፋዊ በሆነ መልኩ በጠረጴዛ ዙሪያ ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

ከዚህ ቀደም ከመገናኛ ብዙሃን ተደብቀው ከአንድም ሁለት ጊዜ እንደተገናኙ ቢነገርም ሁለቱም በይፋ ያሉት ያሉት ነገር ባይኖርም የትግራይ ኃይል አመራሮች በአንዳንድ መግለጫዎቻቸው ላይ መነጋገራቸውን ጠቅሰዋል።

የፌደራሉ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ለጥቂት ወራትበሰሜን ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላም ታይቶ ነበር።

ነገር ግን ባለፈው ነሐሴ ሁለቱ ኃይሎች ድጋሚ ወደ ጦርነት ገብተዋል።

ጦርነቱ ድጋሚ ከተቀሰቀሰ በኋላ የኢትዮጵያና አጋሩ የኤርትራ ኃይል የበላይነቱ እንደያዙና የተለያዩ የትግራይ ክልል ከተማዎች እንደተቆጣጠሩ ቢነገርም ከሁለቱም መንግሥታት ጦርነቱን በተመለከተ የሚሰጡ መግለጫዎች እጅጉን ቀንሰዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው ሁለቱ ወገኖች የሰላም ውይይት ለማድረግ ደቡብ አፍሪካ የሄዱት።

ይህ የሰላም ውይይት እጅግ በርካታ ጥያቄዎች ያጀቡት፤ የአፍሪካ ሕብረት በአወያይነት ምዕራባዊያንና አሜሪካ ደግሞ በተፅዕኖ አሳዳሪነት የሚሳተፉበት እንደሆነ ያነጋገርናቸው ተንታኞች ይገልጣሉ።

የሰላም ድርድሩ ምን ሊመስል ይችላለል? የመሳካት ዕድሉስ ምን ያህል ነው? የአፍሪካ ሕብረት ግጭትን የመፍታት አቅሙ ምን ያህል ነው?

ለመገናኛ ብዙኃን ከመግለጫ በቀር ትንፍሽ የማይባልበት የሰላም ውይይትናና ዕጣ ፈንታውን በተለመከተ ተንታኞቻችን ሐሳባቸውን ሰጥተውናል።

የሰላም ውይይት ምን መምሰል አለበት?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ያሬድ ኃይለማርያምየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማኅበር ኃላፊ ናቸው።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የሳቸውን ድርጅት ጨምሮ ሌሎች ለሰብዓዊ መብት የቆሙ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመስፋፋቱ በፊት ጦርነቱ በሰላም እንዲፈታ ሲጠይቁ ነበር።

ያሬድ፤ ከዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡ ጫና ስለመጣ አሊያም በጦርነቱ አቅም ማጣትና ሌሎች ወደ ድርድር ለመግባት ምክንያት ከሆኑ ይህ ድርድር «መሣሪያ ነው የሚሆነው እንጂ ግብ አይደለም» ይላሉ።

«ዋነኛው ነገር ድርድሩን በቅን ልቡና ከእውነት የመፈለግ ስሜት መኖር አለበት ።» ይላሉ

የፖለቲካ ምሑሩ መሐሪ ታደለ [ዶ/ር] ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሐሳብ አላቸው።

 የሰላም ውይይት ስኬት በአብዛኛው የሚለካው፡ መሬት ላይ ባለው ወታደራዊ እውነታ፤ በተፋላሚ ወገኖች የፖለቲካ ፍላጎት እና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ቁርጠኝነት ላይ መሆኑን ተንታኙ ይናገራሉ።

ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ግን ከሁሉም የሚልቀው ቅንነት ነው።

«ሕዝብ እያለቀ ነው፤ ሃገር እየተጎዳ ነው፤ ለሃገር ጥቅም ሲባል መቆም አለበት ብለው ከሆነ የገቡት [እንደዛ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ] ድርድሩ ቀላል ባይሆንም ረዥም ርቀት ይጓዛል። ግጭቱ እንዲቆም ምክንያት ሊሆንም ይችላል።»

ያሬድ እንደሚሉት ድርድር መስጠትና መቀበልን ያቀፈ ስለሆነ ተደራዳሪዎች ለዚህ ተዘጋጅተው መሄድ አለባቸው።

«ድርድሩን ለጊዜ መግዣ እንደ ስትራቴጂ ከሆነ የወሰዱት ጦርነቱም አይቆምም፤ በሕዝብ ሃብትና ጊዜ መቀለድ ነው የሚሆነው።» ይላሉ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ስለቅንነት ደግመው ደጋግመው ያነሳሉ።

«ግጭት ‘ናቹራል’ ነው፤ ይከሰታል። ነገር ግን እርቅ የሚኖረው ቅንነት ሲኖር ነው። የሃገርን ጥቅም፤ ግጭቱ የሚያደርሰውን ጉዳት በማመዛዘን፤ የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸውን፤ የግል ‘ኢጓቸውን’ ወደ ጎን በመተው ለሕዝብ የሚጠቅመውን ማሰብ። ለሕዝብ የሚጠቅመው ደግሞ ግልፅ ነው። ሰላም ነው።»

ያሬድ፤ የሰላም ውይይት በሌሎችም ክፍለ ዓለማት ይካሄዳል፤ ነገር ግን ብዙ የማይፀናው ‘ቅንነት’ ስለማይኖርና ተደራዳሪዎች ‘ድብቅ አጀንዳ’ ይዘው ወደ ጠረጴዛው ስለሚመጡ ነው ይላሉ።

የጀብደኝነት ስሜት ሁለቱ ኃይሎች በቅን ልቡና ወደ ድርድርድ ሜዳ እንዳይመጡ ያደርጋቸዋል ሲሉም ይሞግታሉ።

«ብዙ ጊዜ የኛ ሃገር ችግር ጦርነቶች እስከ መጨረሻ ድረስ ሄደው፤ ሕዝብ ጨርሰው፤ የሃገር ንብረት አውድመው፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ወጣት አልቆ፤ ተፋላሚዎች ሲዝሉ ነው ወደ ሰላም የምንመጣው። ይህ ከባሕላችንም ጋር የተያያዘ ነገር አለው። ፖለቲከኞች ያሰለፉት ወጣትና የያዙት ጥይት እስኪሟጠጥ፤ አቅማቸው እስኪዝል ድረስ ይፋለማሉ።»

ጦርነቱ የጀመረ ሰሞን በግላቸው እንዲሁም በድርጅታቸው በኩል የሰላም ጥሪ ሲያቀርቡ ትችት ገጥሟቸው እንደነበር የሚያወሱት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ቢዘገይም ለሰላም ዕድል ሊሰጥ ይገባል ባይ ናቸው።

«አሁን ሕዝብ ካለቀ በኋላ፤ በጣም በርካታ ሕዝብ ተጎድቶ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከደቀቀ በኋላ፤ በርካታ ሴቶች ከተደፈሩ በኋላ ወደ ሰላም ድርድር እየመጣን ያለነው። ታሪክ ራሱን እየደገመ ነው። ከጀብድ ጋር የተያያዘው ባሕላችንና የፖለቲካ ልዩነቶችን በሠለጠኑ መንገድ የመፍታት ባሕላችን በጣም ደካማ መሆኑ ዋጋ እያስከፈለን ነው።»

በሠለጠን መንገድ ሲሉ ምን ማለት ነው? ስንል የጠይቅናቸው የመብት ተሟጋቹ በሚኖሩበት የአውሮፓ ክፍል የተፈጠረው በምሳሌነት አንስተው ያስረዳሉ።

«ቤልጂዬም የዛሬ አምስት/ስድስት ዓመት መንግሥት ማቋቋም አቃትት። ፖርቲዎች በዘርም በምንም የተከፋፈሉ ነበሩ። ነገር ግን ቁጭ ብለው ውይይት ያደርጉ ነበር። እንኳን ጥይት ወንበርና ብርጭቆ መወራወርም አልነበረም። ለችግራቸው ጊዜ ሰጡት። አስታመሙት። ከሁሉም ጋር መከሩ። በስተመጨረሻ ተመልሰው መጥተው ማዕከላዊ መንግሥት አቋቋሙ። መሠልጠን ማለት ይሄ ነው።»

የፖለቲካ ምሑሩ መሐሪ ከላይ ከጠቀሱት በተጨማሪ የሽምግልና ስኬት በአስታራቂዎች እና በስትራቴጂዎቻቸው ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የውይይቱ ሂደት፣ አወቃቀሩን እና አጀንዳውን፣ አከራካሪ ጉዳዮች እንዴት ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው እና ሌሎች ለድርድር የሚቀርቡ ዋና ዋና ነገሮችን መለየትን ይወስናል ይላሉ።

“የአፍሪካ ሕብረት እንደ ዋና አስታራቂ ከሌሎች ልዑካን ጋር በመመካከር እስካሁን ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ አላወጣም” ይላሉ ምሑሩ።

«ይሄ አደገኛ ሊሆን ይችላል» የሚል አቋም ያላቸው ተንታኙ፡፤ «ግልጽነት የሌለው ሽምግልና ውዥንብር ስለሚፈጥር ለሰላም ድርድር እጅግ አስፈላጊ የሆነውን እምነት ያጠፋል» ይላሉ።

መጋቢት 2014 ከተደረሰው የተኩስ አቁም በኋላ ጦርነቱ ጋብ ማለቱን ተከትሎ ሁለቱን ኃይሎች ለማስፋፋት እየሞከሩ እንደሆነ የተነገራላቸው የቀድሞው የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ‘ወገንተኝነት’ አሳይተዋል ተብለዋል።

የትግራይ አመራሮች በአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ሲያነሱ ይደመጣል።

«ድርጅቱ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሌሎች ሸምጋዮችን መሾም ነበረበት» የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ

«ምክንያቱም ገለልተኛነት የሽምግልና የማዕዘን ድንጋይ ነው» የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በተገኙበት መንበራቸውም ለተኪያቸው በሰላም ያስረከቡት የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በዚህ የሰላም ድርድር እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል።

የአፍሪካ ህብረት ተፋላሚ ወገኖችን ወደ ሰላም ማምጣት ይቻለው ይሆን?

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፤ ‘ፎሬይን አክተርስ’ [የውጭ ኃይሎች] ድርድሩ እንዲሳካ ምክንያት አሊያም እንዳይሳካ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ።

በርካቶች ለአፍሪካ ሕብረት እያሳዩ ያሉት ድጋፍ መልካም ቢሆንም ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ቢኖር ጥቅማችንን እናጣለን’ ብለው የሚያስቡ ሊኖሩ ይችላሉ የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

«ለኤርትራ መንግሥት የሕወሓት መኖር ሁልጊዜም ስጋት ነው። ድርድር አለ ማለት ደግሞ ሕወሓት ሊቀጥል ይችላል ማለት ነው። ስለዚህ የኤርትራ መንግሥት ለዚህ ውይይት እንቅፋት ሊሆን ይችላል።»

ይሁን እንጂ ዶ/ር መሓሪ ኤርትራ በድርድሩ የምትሳተፍበት ህጋዊ ሂደት የለም ይላሉ።

"ይህ የውስጥ ጉዳይ ነው። ኤርትራን ወደ ድርድር ማምጣት ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ ኣድርጎ የሰላም ድርድሩን የበለጠ ሊያወሳስበው ይችላል። ይህን ለማድረግ የሚያስችል ዓለም አቀፍ የሕግ ሂደት የለም፤›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ውይይት ሐሳብ መነሳት ከጀመረ አንስቶ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት አሸማጋይነት እንዲከናወን ፍላጎት እንዳለው ሲገልጥ ቆይቷል። 

የትግራይ አመራሮች ደግሞ በአፍሪካ ሕብረት ተወካዮች ላይ ያላቸውን እምነት ማጣት ማንጸባረቃቸው የሚታወስ ነው።

ለዚህም ጦርነቱ በተፋፋመበትና ጥሰቶች ሪፖርት እየተደረገ በነበረበት ወቅት የአፍሪካ ሕብረት “መንግሥትበአገር ውስጥ የሚያደርገው ህግ የማስከበር ዘመቻ ነው” በሚል ድጋፍ በመስጠቱ ገለልተኛ አቋም የለውም ሲሉም ይወቅሳሉ።

የፌዴራሉ መንግሥት ‘የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት’ በሚለው የሕብረቱ መርህ እንደሚመራና ከዚህ ውጭ የሚደረግን ድርድር እንደማይቀበለው ገልጧል።

‘የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት’ የሚለው መርህ የመጣው ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት [አይሲሲ] ጋር ተያይዞ ነው የሚሉት ያሬድ እዚህ ችሎት ላይ ብዙ ጊዜ የሚቀርቡት አፍሪካዊያን መሆናቸውን ተከትሎ ምዕራባዊያን ይህን ዓለም አቀፍ ተቋም አፍሪካን ለማጥቂያ እየተጠቀሙበት ነው የሚል ሐሳብ እንዳለ ያስረዳሉ።

«በአንድ ወገን ትክክለኛ የሆነ ምልከታ አለው ብለው ልታስብ ትችላለህ ምክንያቱም ምዕራባዊያኑ ይህን ተቋም ስለሚጠቀሙበት። በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ አምባገነኖች ከተጠያቂነት ማምለጫ ስልት አድርገው ይጠቀሙበታል ማለት ያስችላል።» ይላሉ

ባለፈው ዓመት ሐምሌ መቀለን የጎበኙት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ተወካይ ማይክ ሃመርን ጨምሮ ሌሎች ዓለም ዓቀፍ ተወካዮች በትግራይ ክልል መሠረታዊ አገልግሎት በአስቸኳይ እንዲጀመር መጠየቃቸው ይታወሳል።

የፖለቲካ ተንታኙ መሐሪ ታደለ ልዩ መልዕክተኛው ኦባሳንጆ «ይህን እንኳን በአጀንዳነት ማንሳት አልቻሉም» ሲሉ ይወቅሳሉ።

አልፎም የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል እንዲወጣ አለመጠየቃቸው የተዓማኒነት ጥያቄ ያስነሳባቸዋል ይላሉ ምሑሩ።

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ወደ ድርድሩ መምጣታቸውን ደግፈዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፤ የአፍሪካ ሕብረት ያሸማግል ቢባልም «ከጀርባ ቅርፅ በማስያዝና ድጋፍ በመስጠት ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ያሉት ምዕራባዊያንና አሜሪካ ናቸው» የሚል እምነት አላቸው።

«እውነት ለመናገር የአፍሪካ ሕብረት ሰላምን በማስከበር ረገድ ያልተሳካለት ተቋም ነው። ኮንጎ ብትሄድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዳርፉር፣ ሶማሊያ፣ ሴራሊዮን. . . ምዕራባዊያን እጃቸውን እያስገቡ ቀጣናውን ሲያተራምሱ ይህ ሕብረት ደካማ ነበር» ሲሉ ሕብረቱን ይወቅሳሉ።

ዋና መሥሪያ ቤቱ አዲስ አበባ የቆመው የአፍሪካ ሕብረት በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል ያለውን ድርድር ማሸማገል ይችል ይሆን ?የሚለው ጥያቄ መነጋገሪያነቱ እንደቀጠለ ነው።

«በየቤታቸው የራሳቸው ችግር ያለባቸው መንግሥታት የተሰባሰቡበት ሕብረት ስለሆነ ሰላም በማምጣትም ሆነ ዲሞክራሲ በማስፈን ይህ ነው የሚባል ታሪክ ያለው ተቋም አይደለም። ነገር ግን ይህ ድርድር ከተሳካለት ትልቅ ነገር ነው» ይላሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ።

ሁለቱ ኃይሎች ከደቡብ አፍሪካ ሶስት መዲናዎች አንዷ በሆነችው ፕሪቶሪያ ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው።

ውይይቱ ገና እንጭጭ ቢሆንም ብዙዎች ተስፋ የሰነቁበት ነው።