በደቡብ አፍሪካው ንግግር መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎችን ላያግባቡ የሚችሉ ጉዳዮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት አንዴ ጋብ ሲል ሌላ ጊዜ ደግሞ የተፋፋመ ጦርነት እያስተናገደ ሁለት ዓመት ሊደፍን የጥቂት ቀናት ዕድሜ ነው የቀረው።
‘አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ’ ተብሎ በዙር የተከፋፈለው ጦርነት ለበርካቶች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል። እንደ ጦር ወንጀልና እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች ተፈጽመውበታል።
መሰረተ ልማቶችን አውድሟል። የአገሪቱን መዋዕለ ንዋይ አሟጧል እንዲሁም የምጣኔ ኃብት ቀውስ አስከትሏል።
ምናልባትም በአፍሪካ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ደም አፋሳሹ ጦርነት ሆኖ ሳይመዘገብ እንዳልቀረ በሚነገርለት ጦርነት፤ ከ600ሺህ እስከ 800ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ሳያጡ እንዳልቀረ ጦርነቱን በቅርበት የሚከታተሉት ተንታኞቹ አብዱራሕማን ሳይድ እና አሌክስ ዴ ዋል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
ከውጪ አገር ኃይል እስከ ኢ-መደበኛ የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም የሰው ሰራሽ አውሮፕላኖችን ላሳተፈው ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሔ ካልተሰጠው እልቂቱ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እና በረሃቡ የመሞቱ አደጋ የበርካቶች እጣ ፈንታ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው።
ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ከሚደረገው ጥረት ጋር ተያይዞም ከሰሞኑ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የሰላም ንግግር ተጀምሯል። የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ አመራሮች ልዑኮቻቸውን የላኩ ሲሆን አሜሪካና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በታዛቢነት ተገኝተዋል።
የመሬት ይገባኛል፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የሉዓላዊነት ጥያቄዎች የሚነሱበት የሰላም ንግግር እንደሚሆንም ያሉት ጉዳዮች አመላካቾች ናቸው።
በጦርነቱ በቀጥታ እየተሳተፉ ያሉት በአንድ ወገን የፌደራል መንግሥቱና አጋር ኃይሎቹ ኤርትራ፣ የአማራ ክልል እና የአፋር ክልል እንዲሁም በሌላ ጎራ የትግራይ ኃይሎች ሁሉም የየራሳቸው ፍላጎቶች አሏቸው።
ምንም እንኳ የደቡብ አፍሪካው ንግግር ጅማሮው ውጤታማ መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም፤ የድርድር መንገዱ ለዚህ ለተወሳሰበ ጦርነት ቀላል ላይሆን ይችላል።
ድርድር አመታት የሚወስድ ጉዳይ እንደመሆኑ በሁለቱ ወገኖች መካከል የመግባባትና የመተማመን መንፈስን ለማምጣት እንዲሁም ለቀጣይ ውይይት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ግጭት ማቆም ወሳኙ እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።
ለመሆኑ የኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት በንግግር እንዳይፈታ አከራካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
ምዕራብ ትግራይ ወይም ወልቃይት
ይህ ስፍራ ለትግራይ የኅልውና ለአማራው ደግሞ የማንነት ጉዳይ ነው።
የትግራይ ኃይሎች ‘ምዕራብ ትግራይ’ ብለው የሚጠሩት፤ የአማራ ኃይሎች ደግሞ ‘ወልቃይ ጠገዴ’ የሚሉት አካባቢ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ላቅ ያለ እንደሆነ ይነገራል።
ስፍራው ኢትዮጵያን፣ ሱዳንን እና ኤርትራን ያዋስናል።
ከትግራይ ባሻገር፤ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ልትዋሰን የምትችለው በዚህ ስፍራ በኩል ብቻ ነው።
አፈሩም ለም ነው። ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልከው ቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘው ሰሊጥ መመረቻ ቦታው ምዕራብ ትግራይ ወይም ወልቃይት ነው።
የሁመራ ሰፋፊ የሰሊጥ የእርሻ መሬቶች በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ዳቦ እና እንጀራ ናቸው።
የትግራይ ኃይሎች ይህ አካባቢ ከጦርነቱ በፊት የትግራይ አካል እንደነበረ በመጥቀስ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ሁሉም ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት ቦታው መመለስ አለበት ብለው ሊሞግቱ ይችላሉ።
ለአማራ የሚከራከሩት ደግሞ፤ ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ስልጣን ይዞ አካባቢውን ወደ ትግራይ ከመጠቅለሉ በፊት የአማራ አካል መሆኑን ያነሳሉ።
በተጨማሪም ታሪካዊና የማንነት ዳራን በመጥቀስ ስፍራው ለአማራ እንደሚገባ በመጥቀስ ጥያቄውን ውድቅ ሊያደርጉት ይችላሉ።
ከትግራይ በኩል የሚነሳው መከራከሪያ ቋንቋን መሰረት ባደረገው የብሔር ፌደራሊዝም እንዲሁም ታሪክን በመጥቀስ የትግራይ አካል እንደሆነ ያነሳሉ።
ከኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ጥቅሙ ባሻገር የኅልውና እና የማንነት ጉዳይ የሆነው ምዕራብ ትግራይ/ወልቃይት ጉዳይ አንገብጋቢው የንግግር አጀንዳ ሊሆን ይችላል።
የደቡብ አፍሪካው ንግግር እየተካሄደ ያለው የፌደራሉ መንግሥትና የኤርትራ ጥምር ኃይሎች የተለያዩ ከተሞችን ተቆጣጥረው በሚገኙበት ወቅት ነው።
የመንግሥት ኃይሎች ሽረ፣ አክሱም፣ አላማጣ፣ ኮረምና አድዋን ተቆጣጥረው የሚገኙ ሲሆን የትግራይ ኃይሎች ከነዚህ ስፍራዎች ለቀው እንዲወጡ እየጠየቁ ሲሆን በዚህም ንግግር ውስጥ ከሚነሱ አጀንዳዎች አንዱ እንደሆነም የተለያዩ መግለጫዎች ያመለክታሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትጥቅ የማስፈታት ጥያቄ
በአሁኑ ወቅት በትግራይ አንዳንድ ከተሞችን የተቆጣጠረው የፌደራሉ መንግሥት፤ በዚህ ንግግር የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል።
የፌደራሉ መንግሥት ባለስልጣናት እና ደጋፊዎች፤ ‘በአንድ አገር ሁለት ጦር ሊኖር አይችልም’ በማለት የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት ቁልፍ ጉዳይ አድርገው ሃሳባቸውን ሲገልጹ ተሰምተዋል።
በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ኃይሎች ‘የትግራይ መከላከያ ኃይል’ በሚሉት ሠራዊት ውስጥ ምን ያህል ተዋጊዎችና የጦር መሳሪያዎች እንዳሉት ባይታወቅም፣ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ተቃርቦ የነበረው ኃይል ለፌደራል መንግሥቱ ስጋት ይሆነኛል ብሎ ሊያስብ ይችላል።
ስለዚህም ትግራይ አንድ የፌደራል መንግሥቱ አካል መሆኗን በማስታወስ፤ የፌደራሉ መንግሥት ተወካዮች የትግራይ ኃይሎች ‘ትጥቅ ይፍቱ ብለው ሊጠይቁ’ ይችላሉ።
በጀት ከተቋረጠ ጥቂት አመታትን ባስቆጠረችውና በፌዴራል ስርዓቱም ምንም ውክልና በሌለበት ሁኔታ ጦርነቱን በሰላም መቋጨት እንጂ ትጥቅ መፍታት መቼም አጀንዳ እንደማይሆን የትግራይ ኃይሎች ሲናገሩ ይሰማል።
“ጠላት” በሚሏቸው ኃይሎች በሰሜን፣ ምስራቅ እና ደቡብ ተከበናል የሚሉት የትግራይ ኃይሎች፤ ሰላም ለማውረድ ሲባል ትጥቅ መፍታት አማራጭ ላይሆን ይችላል።
‘ኅልውናችን አደጋ ላይ ነው’፣ ‘ከበባውን ለመስበር ሰላማዊም ይሁን ወታደራዊ መፍሄዎችን እንጠቀማለን’ እንዲሁም “ትግራይ የገባ እዚሁ ይቀበራል’ ለሚሉት የትግራይ ኃይሎች ‘የትጥቅ ፍቱ ጥያቄን’ የማይቀበሉት ጉዳይ እንደሆነ ሲያነሱ ይሰማሉ።
በተለይም ኤርትራን በመጋበዝ የትግራይ ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ወረራና ጥሰት ተፈጽሟል በማለትም የትግራይ ኃይሎች “ህዝባችንን መጠበቅ የምንችለው እኛ ነን” የሚል ምክንያትም ያቀርባሉ ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤርትራ ጉዳይ
ሌላኛው በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆነችው የኤርትራ ጉዳይ ነው።
ኤርትራ በዚህ የሰላም ንግግር ፍላጎቴ አልተጠበቀም ብላ የምታስብ ከሆነ፤ የሰላም ድርድሩ ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል።
ኤርትራ ፍላጎቷ ምን ቢሆን ነው እጇን ጦሯን ወደ ትግራይ የላከችው?
አሥመራ የህወሓት በቀጠናው መኖር ለደኅንነቴ ስጋት ነው ስትል ቆይታለች።
ለኤርትራ ወደዚህ ጦርነት መግባት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ተንታኞች ይናገራሉ።
አሥመራ ጦሯን ወደ ትግራይ የላከችበት ዋነው ምከንያት ኢሳያስ ከህወሓት ጋር ያላቸው ቁርሾ ነው ይላሉ ተንታኙ አብዱራሕማን ሳይድ።
ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ አለመቀጠሉ እንዲረጋገጥ ይፈልጋሉ።
በቅርቡ የነበረውን የኤርትራ የክተት ጥሪን ተከትሎ አፈሳዎች መቀጠላቸውን የተናገሩ ነዋሪዎችም ከባለስልጣናቱ ‘አሁን በመጨረሻው የኅልውና ደረጃ ላይ እንገኛለን፤ ወያኔ መቀበር አለበት፤ ልጆቻችሁን ካላመጣችሁ፣ በሚደርሰው መዘዝ ተጠያቂዎች ናችሁ’ እንደሚሏቸውም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሌላኛው የመሬት ጉዳይ ነው።
በሁለቱ ሃገራት የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 1996 ዓመተ ምህረት የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን አስተላለፈ፡፡
ሁለቱ ሀገራት ከተፋለሙባቸው ቦታዎች አንደኛዋ የነበረችው ባድመ የኤርትራ ግዛት እንድትሆን ተፈረደ፡፡ በኤርትራ አስተዳደር ስር የነበረው የጾረና አካባባቢ እንዲሁ ለኢትዮጵያ እንዲሆን ተወሰነ።
ኮሚሽኑ ውሳኔውን ሲያስተላልፍ የቅኝ ግዛት ህጎችን እና አለም አቀፍ ህግን ተመስርቶ ሲሆን በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት የድንበር ማካለሉ ካለ አንዳንድ ቅድመ- እሳቤዎች እንዲሁም ቢተገበር ችግር ይፈጠራል አለ። እናም በሁለቱ ሃገራት መካከል ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግም ተጠየቀ ይህንን ኤርትራ ሳትቀበለው ቀረች።
ኢህአዴግ ውሳኔውን ተቀብሎ ጦሩን ከባድመ ለማስወጣት ፈቃደኛ አልሆነም።
ይህንንም ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት ድንበር ለበርካታ ዓመታት ፍጥጫ ሰፍኖበት የነበረ ሲሆን ኤርትራ የአልጀርሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ስትጎተጉት ቆይታለች።
ኤርትራ ለአመታትም መሬቷን እንደተወሰደባትም በህወሃት መራሹ መንግሥትም ተከልክላ መቆየቷን ልትዘነጋው የማትችለው ጉዳይ እንደሆነ ለአመታት ስትናገር መቆየቷ ይታወቃል።
ሆኖም ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰኔ 11፣ 2010 ዓ.ም ባደረገው ጉባኤ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሁለቱን ሃገራት አፋጧቸው የቆየውን ጉዳይ መፍትሄ መስጠቱ ይታወሳል።
በዚህ ጉባኤ ኢህአዴግ የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ገልጿል። መገለጹ ይታወሳል።
የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎም የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ሰላም መምጣቱንም አብስረው የነበረ ሲሆን የባድመና ድንበር የማካለሉ ጉዳይ በዚህ ወቅትስ ለምን ተፈጻሚ አልሆነም የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ አሉ።
በትግራይ ጦርነት ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር በመሆን እየተዋጋ ያለችው ኤርትራ በአልጀርሱ ስምምነት ከተወሰነላት ባድመ በተጨማሪ በሽረና ሌሎች ከተሞች ጦሯ እንደሚገኝ የተለያዩ መንግሥታትና ተቋማት ሲገልጹ ይሰማል።
በቅርቡም አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአውሮፓ ህብረት የኤርትራ ጦር በተደጋጋሚ እንዲወጡ መጠየቁ ይታወሳል።
በተደጋጋሚ ጦሯ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ የተጠየቀችው ኤርትራ ከሰሰሞኑ " ኤርትራ የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ጦርነት አጥፊ ሚና እየተጫወተች ነው" በማለት ያቀረበውን ሪፖርት “ተበዳዩን የመውቀስና ወንጀለኛውን በሰብዓዊ መብት ሽፋን የማዳን ተግባር” ስትል ማጣጣሏ ይታወሳል።
ሁለቱ ወገኖች በምን ሊስማሙ ይችላሉ?
የሰብዓዊ እርዳታ የመሠረተ ልማት አቅርቦት
ማክሰኞ ጥቅምት 15፣ 2015ዓ.ም የተጀመረው የሰላም ንግግር እሁድ ሲጠናቀቅ ሁለቱ ወገኖች ተስማምተውባቸዋል ሊባሉ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል የሰብዓዊ እርዳታ እና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ጅማሮዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ይህ የትግራይ ፍላጎት ብቻ ስለሆነ ሳይሆን የምዕራባውያን ቀዳሚ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ነው።
የፌደራል መንግሥቱም ቢሆን በትግራይ ላሉ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ‘ድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ነው ብሎ ነበር።
ምንም እንኳን መንግሥት ይህንን ይበል እንጂ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ እገዳ እንደጣለባትና በክልሉም ረኃብን እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ አውሏል በሚል የተለያዩ ሪፖርቶች ቀርበዋል።
ከትግራይ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረ ሕይወት የትግራይ ኃይሎች ልዑካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው ይፋ ባደረጉበት የትዊተር ጽሑፋቸው የትግራይ ኃይሎች የሚያነሷቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ግጭት በአስቸኳይ ማስቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ማስወጣት የሚሉት መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በድርድሩ ላይ የታዛቢነት ሚና እንደሚኖራት የገለጸችው አሜሪካም ብትሆነ በውጪ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል ግጭት አቁሞ ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት ብላለች።
ብሊንከን የሰላም ንግግሩ በተጀመረበት ዕለት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር ግጭቱ በአስቸኳይ ማቆም ቅድሚያ ተሰጥቶት፤ ተደራዳሪዎቹ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ፣ የሰላማዊ ሰዎች ደኅንነት ለመጠበቅ እርምጃ እንዲወስዱ እንዲሁም የኤርትራ ኃይሎች ከሰሜን ኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ከስምምነት እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ በትጋት እየሠራ ነው ብሏል።
በዚህ ንግግር መንግሥት ተቆጣጥሮ በያዛቸው የትግራይ አካባቢዎች መሠረተ ልማቶችን ለማስጀመር እና የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭትን በመቆጣጠር የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ሊስማማ ይችላል።
የጦር ወንጀለኞችን በሕግ መጠየቅ
በሁለቱም ወገን ያሉት ተዋጊ ኃይሎች በተለያየ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች አጋልጠዋል
የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደሆኑም የሚቆጠሩ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች፣ መድፈር፣ ማሰቃየት፣ እስር፣ ዘረፋ፣ የግል እና መሰረተ ልማቶችን ማውደም . . . በዚህ ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው።
በኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ምርመራ የሚያካሂድ ቡድን አቋቁሞ እየሰራ መሆኑንና በደሎችን ፈጽመዋል የተባሉ የሠራዊቱን አባላት ለፍርድ ማቅረቡን በመጥቀስ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ይገልጻል።
ከትግራይ በኩል ደግሞ የሚቀርበው ጥያቄ ነጻና ገለልተኛ የሆነ አካል ምርመራ እንዲያደርግና ጥፋተኞች በዚያ መሰረት እንዲቀጡ ወስኗል።
ለምሳሌም ያህል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶች በሚያጣራው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን የሪፖርት ግኝት ከትግራይ በኩል ድጋፍ ሲያገኝ የኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታ ይሰማል።
በዚህ ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ሪፖርቱ ገልጿል። ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሆን ተብለው የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች እንደ ጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው ምክንያታዊ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ ብሏል።
ሪፖርቱ “ያልተሟላ፣ ተያያዥነት የሌለው እና በመረጃ ያልተደገፈ” በማለት አገሪቱን በመጥፎ መልኩ ለማቅረብ የታለመ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት አጣጥሎታል።
የሠራዊት አባላት ለፈጸሟቸው በደሎች እንዴት በሕግ ሊጠየቁ ይችላሉ? ማን ጉዳዩን ይመረምራል? ማን ይዳኛቸዋል? ቅጣታቸውንስ እንዴት ተፈጻሚ ይሆናል? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ባይኖርም ሁለቱም ወገኖች በመርህ ደረጃ ጥፋተኞችን ከሕግ ፊት ለማቅረብ ተስማምተው ተፈጻሚነቱ ግን ሊጓተት የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።












