በኢትዮጵያው የሰላም ንግግር አሜሪካ እና ተመድ በታዛቢነት እየተሳተፉ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, THINKSTOCK/Getty
በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ባለው የሰላም ንግግር አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት አስታወቀ።
የአፍሪካ ኅብረት ዛሬ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሁለቱ ድርጅቶች በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑን አስታውቋል።
በስፋት ሲጠበቅ የቆየው የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች የሰላም ንግግር ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 15 ጀምሮ እስከ እሁድ ጥቅምት 20/2015 ዓ.ም. ቀጥሎ እንደሚካሄድ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ቀደም ሲል ይፋ አድርገው ነበር።
የሰላም ንግግሩን በበላይነት የሚመራው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት፤ የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ለገቡበት ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ኅብረቱ የሚያደርገው ጥረት መጀመሩን በዚህ መግለጫ አስታውቀዋል።
ሊቀመንበሩ ጨምረው የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ለግጭቱ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት እያሳዩ ያሉት ቁርጠኝነት አዎንታዊ መሆኑን በመግለጫቸው ገልጸዋል።
የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች የሚያደርጉትን ድርድር የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ እንደሚያስተባብሩት በመግለጫው ተመላክቷል።
ሙሳ ፋኪ የተኩስ ድምጽ እንዳይሰማ፣ የተባበረች፣ የተረጋጋች እና ሰላማዊ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የአፍሪካ ኅብረት “በኢትዮጵያውን ባለቤትነት እና በአፍሪካ ኅብረት መሪነት” የሚካሄድ የሰላም ንግግር እንዲኖር ድጋፉን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ሙሳ ፋኪ ደቡብ አፍሪካ ይህን የሰላም ንግግር ለማስተናገድ በመፍቀዷ የአገሪቱን መንግሥት እና ፕሬዝዳንት ሲራል ራማፎሳን አመስግነዋል።
በዚህ በስፋት ሲጠበቅ በቆየው የሰላም ንግግር ላይ ለመሳተፍ የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ወኪሎች ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት በጠረጴዛ ዙሪያ የሚቀመጡት በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው።
ባለፉት ቀናት የፌደራሉ መንግሥት ጥምር ኃይሎች በርካታ ከተማዎችን እና የትግራይ አካባቢዎችን ከትግራይ ኃይሎች አስለቅቋል የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
የንግግር አጀንዳዎች
የአፍሪካ ኅብረት ተፋላሚ ኃይሎች ግጭት አቁመው ልዩነቶቻቸው በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሊደራደሩባቸው የሚችሏቸውን ጉዳዮች በይፋ ባይገልጹም፤ የአፍሪካ ኅብረት እና ምዕራባውያን ግን ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ፕሮፌሰር ክንደያ፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሚደረገው ውይይት የትግራይ ኃይሎች የሚያነሷቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ግጭት በአስቸኳይ ማስቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ማስወጣት የሚሉት መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የፌደራል መንግሥት ግን ከዚህ ቀደም "ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ" ለንግግር ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።












