በኦሮሞ ነጻነት ጦር ታጣቂዎች የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በርካቶች ተገደሉ

አምቦ ከተማ የምዕራብ ሸዋ ዞን መቀመጫ ናት
የምስሉ መግለጫ, አምቦ ከተማ የምዕራብ ሸዋ ዞን መቀመጫ ናት

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሽዋ ዞን ተገደው የወጡ ሰላማዊ ዜጎች በተገኙበት የታጣቂዎች የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በምዕራብ ሸዋ በዞን በምትገኘው ጮቢ ወረዳ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን ያሰለጠናቸውን ታጣቂዎች እያስመረቀ ሳለ ነበር የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መፈጸሙ የተነገረው።

ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሰማው የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ሰላማዊ ዜጎች በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዲገኙ አስገድዶ የምርቃት ስነ-ስርዓቱ እየተካሄደ በሚገኝበት ወቅት ነው።

በዚህ ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን እና የታጣቂ ቡድኑ አባላትን ጨምሮ እስከ 70 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ120 ያላነሱ መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት የፌደራሉ መንግሥት ታጣቂ ቡድኑ ላይ ያነጣጠር የአየር ጥቃቶችን በምዕራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ሲፈጽም ቆይቷል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ትናንት በትዊተር ገጻቸው ላይ ከጥቅምት 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ቢያንስ 6 የሰው አልባ አውሮፕለን ጥቃቶች ተፈጽመዋል ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሜታ ወልቂጤ እና ጮቢ ወረዳዎች የተገደሉ 'ሰላማዊ ሰዎች ከ150 በላይ ናቸው' ይላሉ።

ኦዳ ተርቢ በጮቢ ጨምሮ 150 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ይበሉ እንጂ በወረዳው የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው የታጣቂ ቡድኑ የምርቃት ስነ-ስርዓት እየተካሄደ ሳለ ስለመሆኑም ይሁን በእነዚህ የአየር ጥቃቶች የተገደሉ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ስለመኖራቸው ያሉት ነገር የለም።

የአየር ጥቃቶቹን በተመለከተ ቢቢሲ የጮቢ ወረዳ አስተዳዳሪን ጨምሮ የአካባቢው ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ መረጃ ካለው ተጠይቆ ተፈጽመዋል የተባሉ የአየር ጥቃቶችን በተመለከተ ምርመራ እያደረገ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።

ሰላማዊ ሰዎች ሰላባ የሆኑባቸው የአየር ጥቃቶች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በምዕራብ ሸዋ ጮቢ ወረዳ ከተፈመው የአየር ጥቃት በኋላ የነበረን ሁኔታ የሚያሳይ ነው የተባለ ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት በማሕብራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲዘዋወር ቆይቷል።

ቢቢሲ የዚህን ተንቀሳቃሽ ምስል ትክክለኛነት ባያረጋግጥም፤ በምስሉ ላይ ተመሳሳይ የሆነ የደንብ ልብስ የለበሱ በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ይታያሉ።

የአከባቢው ነዋሪዎች ባለፉት ቀናት በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በተፈጸሙት የአየር ጥቃቶች ዒላማ የተደረጉት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ይሁን እንጂ ሰላማዊ ሰዎችም ሰለባ ስለመሆናቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወልቂጤ ወረዳ በነበረ ሌላ የአየር ጥቃት ሦስት ወንድሞቹን ያጣው ነዋሪ ለታጣቂዎች የሚሰነዘሩት የአየር ጥቃቶች የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ እንደሆነ ይናገራል።

ነዋሪው እንደሚለው በአየር ጥቃቱ የተገደሉት ሦስቱ ወንድሞቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነበሩ።

“ባለፈው ዕሮብ (ጥቅምት 9) ጎሮ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት ነው የተገደሉት። . . . ጉዳት የደረሰባቸው ተዋጊዎች ቁጥራቸው ሲበዛ በቤት ውስጥ ተሸሽገው የነበሩ ተማሪዎችን 'ቁስለኞችን ያዙልን' በማለት ከቤት ማስወጣት ጀመሩ። ወንድሞቼ ልክ ከቤት እንደወጡ አየር መጣና ወንድሞቼን ጨረሰ” በማለት የነበረው ሁኔታ ያስረዳል።

“ጫካ ያለው ኃይል ሕዝብ ውስጥ በዝቶ ስላለ ከአየር ላይ ሆነው እንዴት ለይተው ይመታሉ? በአንድ ላይ ነው የሚመቱት። ወንድሞቼ ብቻ አይደሉም። በርካታ ሕዝብ ነው ያለቀው።”

ከምዕራብ ሸዋ ዞን ወረዳዎችን በተጨማሪ ባለፉት ቀናት የአየር ጥቃት ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች መካከል ሌላኛው በምስራቅ ወለጋ ዞን ኑኑ ቁምባ ወረዳ አዳሬ ከተማ ነው።

በከተማዋ አርብ እና እሁድ የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸውን አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በሁለቱ ቀናት በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች መንግሥት ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት በተጨማሪ ከብቶች ሲያግዱ የነበሩ ታዳጊዎች መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

‘ሸኔ’ ወይም 'የኦሮሞ ነጻነት ጦር'

መንግሥት 'ሸኔ' የሚለውን እና እራሱን 'የኦሮሞ ነጻነት ጦር' ብሎ የሚጠራው ቡድን በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ በስፋት በመንቀሳቀስ ለክልሉ እና ለፌደራል መንግሥት ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

ታጣቂ ቡድኑ የሚንቀሳቀስባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች የደኅንነት እጦት ያለባቸው ሆነዋል። ይህ ቡድን ለበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ጥፋተኛ ሲደረግ ቆይቷል።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው ቡድን በጀምላ ግድያ፣ ዘረፋ፣ በንጹሃን እና በመንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ፣ መንገድ በመዝጋት፣ የሕዝብ እና የመንግሥት ንብረት በማውደም፣ ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ እና በሌሎች ወንጀሎችም ይከሰሳል።

ይሁን እንጂ ታጣቂ ቡድኑ የሚቀርብበትን ክስ ሲያስተባብል ቆይቷል።

የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት ይህን ቡድን ለማጥፋት ቁርጠኛ መሆናቸውን እና በተለያዩ ጊዜ ዘመቻ መጀመራቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።