በትግራይ ክልል ያሉ ነዋሪዎች ጥቃት ይደርስብናል የሚል ስጋት ላይ እንደሆኑ አምነስቲ ገለጸ

ትግራይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ለአምስት ወራት የቆየው የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ተጥሶ ጦርነቱ በተባባሰበት ሁኔታ የትግራይ ነዋሪዎች ጥቃቶች ይደርስብናል ብለው እንደሰጉ አምነስቲ አስታወቀ።

አምነስቲ ይህንን የገለጸው ተፋላሚ ወገኖች ሰላማዊ ዜጎችን ከጥቃት እንዲጠብቁ በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 14፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነው።

የትግራይ ነዋሪዎች ግድያ፣ መደፈርና ሌሎች መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶች ዳግም ይከሰታሉ የሚል ፍርሃት ላይ ናቸው ብሏል።

“የትግራይ ነዋሪዎች መከላከያ ሰራዊትና እና አጋር ኃይሎች እነዚህን አካባቢዎች ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት ተንሰራፍቶ የነበሩ ግድያዎች፣ ወሲባዊ ጥቃቶች እና ስልታዊ ጥቃቶች እንደገና ሊፈጸምብን ይችላል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው” ሲሉ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ሙሌያ ምዋንያንዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መጠለያ የሆነችውን የሽረ ከተማን ጨምሮ የኮረም እና አላማጣ ከተሞችን መቆጣጠሩን አስታውቋል።

 ከነዚህ ከተሞች በተጨማሪ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የአድዋ ከተማ በኢትዮጵያና በኤርትራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መሆኗን የዘገበ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት ባወጣው መግለጫ ሌሎች ከተሞችን እንደተቆጣጠረ ቢገልጽም የትኞቹን እንደሆነ አልጠቀሰም።

መንግሥት እነዚህን ከተሞች ሲቆጣጠር በከተሞች ውጊያ ሳይደረግ መሆኑን ጠቅሶ የዜጎችን ጉዳት ለመቀነስ እየጣረ መሆኑን ገልጿል።

ሆኖም ለተቋሙ የደረሱት ሪፖርቶች ይህ ተፈጻሚ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው ብሏል አምነስቲ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

 በነሐሴ እና መስከረም ወራት በመቀለ እና በአዲ ዳዕሮ በርካታ የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸውን የገለጸው አምነስቲ በዚህም ህፃናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል ብሏል።

 የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አጋር የሆነው የኤርትራ ጦር በሽራሮ ከተማ ከጳጉሜ 1፣ 2014 ዓ.ም- መስከረም 2/ 2015 ዓ.ም ባሉት ቀናት ኤርትራውያን ስደተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 40 ነዋሪዎችን ገድሏል ብሏል።

ወታደራዊም ይሁኑ ሲቪል ባለስልጣናት በጦር ኃይሎቻቸው የሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለህግ የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል ያለው አምነስቲ “ይህንን ተግባራዊ አለማድረግ የነዚህ ወንጀሎች ተባባሪ ያደርጋቸዋል ብሏል።

 በዚህ ጦርነት ላይ ጥሰት የፈጸሙ የጸጥታ ኃይሎችን ያለመቅጣት የበለጠ ወንጀሎችን እንዲፈጽሙ እንደሚያበረታታ አሳይቷል ያለው ተቋሙ አምነስቲ የመዘገባቸው የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ዳግም እንዲከሰቱ ፈጽሞ ሊፈቀድ እንደማይገባው አስታውቋል።

አምነስቲ በዚህ መግለጫው በሰብዓዊ መብት ረገጣ እና በጦር ወንጀሎች ተሳታፊ የሆኑትን የኤርትራ ጦር አባላትንና የአማራ ታጣቂዎችን ጨምሮ ከስራ ማገድ እንዲሁም በአስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ማረጋገጥ አለባቸው ብሏል።

አምነስቲ በተጨማሪም የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ያለምንም እንቅፋት እንዲገባ እንዲፈቅድ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጠይቋል።

የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ባስለቀቃቸው ከተሞች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሥራ እንደሚጀመር ሲገልጽ ቆይቷል።

ዛሬም በወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰብአዊ የእርዳታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እየሠራ ይገኛል ብሏል።

 ተቋሙ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረበት እስከ አሁን የተፈጸሙ ወንጀሎችን ገለልተኛ እና ተዓማኒነት ባለው መልኩ ምርመራ እንዲደረግ አለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶችን ስትራቴጂዎችም እንዲዘረጋ ጠይቋል።