የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች የሰላም ንግግር ተጀመረ

የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች የሚያደርጉት የሰላም ንግግር ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ተጀመረ።
በስፋት ሲጠበቅ የቆየው የሰላም ንግግር ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 15 ጀምሮ እስከ እሁድ ጥቅምት 20/2015 ዓ.ም. ቀጥሎ እንደሚካሄድ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ቪንሰንት ማግዌኛ በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት እየተፋለሙ ያሉት ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የኅብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ እንደሚያስተባብሩት ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ የሰላም ንግግሩ ፍሬ እንዲያፈራ ለአስተባባሪዎቹ መልካም ምኞታቸውን ገልጸው፤ “የድርድሩ ውጤት ለመላው ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ ደቡብ አፍሪካ ምኞቷን ትገልጻለች” ብለዋል።
በዚህ በስፋት ሲጠበቅ በቆየው የሰላም ንግግር ላይ ለመሳተፍ የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ወኪሎች ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው ይታወሳል።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት፣ በአፍሪካ ኅብረት በሚመራው የሰላም ንግግር ላይ የሚሳተፈው የትግራይ ልዑክ ቡድን ደቡብ አፍሪካ ደርሷል ሲሉ ከትናንት በስቲያ እሁድ ጥቅምት 13 ምሽት ላይ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ረፋድ ጥቅምት 14/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በሰላም ንግግሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ አምርቷል ብሏል።
ሁለቱ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት በጠረጴዛ ዙሪያ የሚቀመጡት በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው።
ባለፉት ቀናት የፌደራሉ መንግሥት ጥምር ኃይሎች በርካታ ከተማዎችን እና የትግራይ አካባቢዎችን ከትግራይ ኃይሎች አስለቅቋል የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
ተደራዳሪዎቹ እነማን ናቸው?
በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት በተሰራጨው ደብዳቤ መሠረት የትግራይ ኃይሎች ከሚወከሉባቸው ተደራዳሪዎች መካከል የህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የፓርቲው ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ አንዱ ናቸው።
ሁለተኛው ደግሞ የትግራይ ኃይሎችን ከሚመሩት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መካከል አንዱ የሆኑት ጀኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ናቸው። ከሁለቱ ግለሰቦች በተጨማሪ አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው፣ ፍሰሃ ሃፍተጺዮን (ዶ/ር)፣ ተወልደ ገ/ትንሳይ፣ ካሳ ገ/ዮሐንስ እና አሰፋ አብረሃ የትግራይ ኃይሎችን የሚወክሉት ናቸው።
የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚነጋገሩ አባላት ከዚህ ቀደም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ይህ ተደራዳሪ ቡድን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራ ሲሆን ሰባት አባላትን ያካተተ ነው።
ከአቶ ደመቀ በተጨማሪ የፌደራል መንግሥቱን የሚወክሉት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንት ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የመከላከያ ሠራዊት የመረጃ ደኅንነት ኃላፊ ሌ/ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር) እና በብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ማዕከል ዘርፍ ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት እየሰሩ የሚገኙት አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር ናቸው።
የንግግር አጀንዳዎች
የአፍሪካ ኅብረት ተፋላሚ ኃይሎች ግጭት አቁመው ልዩነቶቻቸው በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሊደራደሩባቸው የሚችሏቸውን ጉዳዮች በይፋ ባይገልጹም፤ የአፍሪካ ኅብረት እና ምዕራባውያን ግን ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ፕሮፌሰር ክንደያ፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሚደረገው ውይይት የትግራይ ኃይሎች የሚያነሷቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ግጭት በአስቸኳይ ማስቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ማስወጣት የሚሉት መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የፌደራል መንግሥት ግን ከዚህ ቀደም "ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ" ለንግግር ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።












