የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል በፌደራል ፖሊስ አባል በተተኮሰ ጥይት ተገደሉ

ጅግጅጋ ገራድ ዊልዋል አየር ማረፊያ
የምስሉ መግለጫ, ጅግጅጋ ገራድ ዊልዋል አየር ማረፊያ

ዛሬ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባሏ ጅግጅጋ አየር ማረፊያ ውስጥ በፌደራል ፖሊስ አባል በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ሕይወታቸው አለፈ።

በፖሊስ አባላቱ የተገደሉት ከዶሎ ዞን ተመርጠው ክልል ምክር ቤት አባል መሆን ችለው የነበሩት ጁዋሪያ መሀመድ ኢብራሂም ሰለመሆናቸው የቢቢሲ ሶማሊኛ ሪፖርተር ዘግቧል።

ብልጽግና ፓርቲም የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል እና የብልፅግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባሏ በአየር ማረፊያው ከአንድ የፀጥታ ኃይል አባል በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸው ማለፉን አረጋግጧል።

ፓርቲው ጉዳዩ በህግ አግባብ ተይዞ እየተጣራ መሆኑን ገልጾ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባሏ ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።

ከክልል ምክር ቤት አባሏ በተጨማሪ በፖሊስ አባሉ በተተኮሱ ጥይቶች 5 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በጅግጅጋ ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ በጅግጅጋ ያለው ሪፖርተር ዘግቧል።

በጥይት ተመትተው ሆስፒታል ከገቡት መካከል አንዱ የክልሉ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት መሀመድ አብዱረሺድ መሐመድ ኡመር መሆናቸው ተገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ አባሉ ዛሬ ከሰዓት 9 ሰዓት አከባቢ ከጅግጅጋ ለመጓዝ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኙ ሰዎች ላይ በከፈተው ተኩስ ነው የሞት እና የመቁሰል አደጋ የደረሰው።

የፖሊስ አባሉ ይህን ድርጊት ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ግን የፌደራል ፖሊስ አባሉ ከሌሎች የአየር ማረፊያው ጥበቃ አባላት ጋር ንትርክ ውስጥ ከገባ በኋላ ተኩስ ከፍቷል ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ቢቢሲ የፌደራል ፖሊስ አስተያየትን የጠየቀ ሲሆን፤ የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጉዳዩን አጣርተው ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ከተኩስ እሩምታው በኋላ የፌደራል ፖሊስ አባሉ በሌሎች የፌደራል ፖሊስ አባላት፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል እና በአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተዘግቧል።

ዛሬ ከሰዓት አለመረጋገት ሰፍኖበት የነበረው የጅግጅጋ አየር ማረፊያ አገልግሎት መሰጠት አቁሞ ነበር።