የኤሎን መስክ 'ኤክስ' ሴቶችን አራቁተው ከሚያሳዩ የኤአይ ምሥሎች ጋር በተያያዘ ውግዘት ደረሰበት

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images via Getty
"ግሮክ" የተባለው የባለሀብቱ ኤሎን መስክ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቻትቦት፤ ተጠቃሚዎቹ የሰዎችን ፎቶ ወሲባዊ በሆነ መልኩ እንዲቀይሩ መፍቀዱ ከአውሮፓ እና እስያ ባለሥልጣናት ውግዘት አስነሳበት።
የዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያ ባለሥልጣናት ጉዳዩን በተመለከተ ምርመራ እንደጀመሩ አስታውቀዋል። የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሸን እና ሕንድ በበኩላቸው ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለቀድሞው ትዊተር የአሁኑ "ኤክስ" ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ማሌዢያ እና ኢንዶኔዢያ ደግሞ ግሮክ አገራቸው ውስጥ እንዳይሠራ አግደዋል።
'ኤክስኤአይ' በተባለው የኤሎን መስክ ኩባንያ የተሠራው 'ግሮክ' የተባለው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቻትቦት በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘትን የተነሳበት ለኤክስ ተጠቃሚዎች ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ነው።
በአሌሎን መስክ ከተገዛው የቀድሞው ትዊተር ጋር የተሳሰረው ግሮክ፤ ተጠቃሚዎች በኤአይ የሰዎችን ምሥል ቀይረው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲለጥፉ አስችሏል። የኤክስ ተጠቃሚዎች 'ግሮክን' ተጠቅመው የሴቶች ፎቶ ወደ እርቃን ምሥል ሲቀይሩ እና ገጾቻቸው ላይ ሲለጥፉ ተስተውሏል።
ቢቢሲ፤ የተለያዩ ሴቶች ያለፈቃዳቸው በኤአይ አማካኝነት ፎቷቸው ላይ እርቃናቸውን እንዲሆኑ ወይም ወሲባዊ አኳኋን እንዲያሳዩ መደረጉን ተመልክቷል። አንዲት ሴት እርሷን ወሲባዊ በሆነ መልኩ የሚያሳዩ ከ100 በላይ ምሥሎች እንደተሠሩ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የዩናይትድ ኪንግደም የቴሌኮሚዩኒኬሽን ተቆጣጣሪ ተቋም የሆነው "ኦፍኮም" ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ የኤአይ ቻትቦቱ እርቃናቸውን የተደረጉ ሰዎችን ምሥል ለመፍጠር እና ለማጋራት ጥቅም ላይ መዋሉ እንዳሳሰበው ገልጿል።
"ወሲባዊ የሆኑ የሕጻናት ምሥሎች" ጭምር ባለቤትነቱ የኤሎን መስክ በሆነው ኤክስ ኤአይ አማካኝነት መሠራታቸውን የሚገልጽ ሪፖርት እንደደረሰው አስታውቋል።
ከዚህም በመነሳት ኤክስ ላይ ምርመራ መጀመሩን የዩናይትድ ኪንግደሙ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። በዚህ ምርመራ ኤክስ ጥፋተኛ ሆኖ የሚገኝ ከሆነ ኩባንያው በመላው ከሚያገኘው ገቢ 10 በመቶውን ወይም 18 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲከፍል ቅጣት ሊጣልበት ይችላል።
ይህንን ዓይነቱን እርምጃ የወሰደችው ዩናይትድ ኪንግደም ብቻ አይደለችም። ባለፉት ቀናት የተለያዩ የአውሮፓ እና የእስያ አገራት ምርመራ ጀምረዋል ወይም በባለሥልጣናቶቻቸው በኩል ውግዘትን አሰምተዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽን በሰሞነኛው ቅሬታ የተነሳ ከዚህ ቀደም ለኤክስ ሰጥቶ የነበረውን ከግሮክ ጋር የተያያዙ ውስጣዊ ሰነዶች እንዲጠበቁ እና እንዳይጠፉ የሚያደርግ ትዕዛዝ የቆይታ ጊዜ እስከ 2026 መጨረሻ ድረስ አራዝሟል።
ሕንድ በበኩሏ በግሮክ አማካኝ ከተሠሩ ወሲባዊ ምሥሎች ጋር በተያያዘ ለኤክስ ይፋዊ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች። ሕንድ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ባወጣችው ማስጠንቀቂያ ምሥሎቹ እንዲወርዱ እንዲደረጉ እና እርምጃ ስለመወሰዱ በ72 ሰዓት ውስጥ ሪፖርት እንዲደረግላት ጠይቃለች።
ኢንዶኔዢያ በበኩሏ የአገሯ ዜጎች ግሮክን እንዳይጠቀሙ አግዳለች። ይህ እርምጃ የተወሰደው ሴቶች እና ሕጻናትን በኤአይ ከተሠሩ ሐሰተኛ የፖርኖግራፊክ ይዘት ያላቸው ልጥፎች ለመጠበቅ እንደሆነ አስታውቃለች።
ማሌዢያም በተመሳሳይ ግሮክ የሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ "ያለፈቃድ የተቀነባበሩ ወሲባዊ፣ ጸያፍ፣ እና እጅግ አስነዋሪ ምሥሎችን" ለመፍጠር "ተደጋጋሚ አላግባብ ጥቅም ላይ መዋሉን" በመግለጽ ጊዜያዊ እገዳ ጥላለች።
የአውስትራሊያ የበይነ መረብ ደኅንነት ተቆጣጣሪ ተቋምም ግሮክ ላይ ምርመራ መጀመሩን ገልጿል። የጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ጣልያን ደግሞ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
ኤክስ የደረሰበትን ትችት ተከትሎ የኤአይ ቻትቦቱ ባለቤት የሆነው ኤክስአይ፤ ግሮክን ተጠቅመው ምሥል መፍጠር የሚችሉ ሰዎችን ብዛት ገድቧል።በአዲሱ አሠራር በግሮክ ምሥል መፍጠር የሚችሉት ክፍያ ፈጽመው ኤክስ የሚጠቀሙ ደምበኞች ብቻ ናቸው።
ኤክስ የቀረበበትን ትችት በተመለከተ በሰጠው ምላሽ "ግሮክን ሕገ ወጥ ይዘቶችን ለማመንጨት የሚጠቀም ወይም ትዕዛዝ የሚሰጥ ማንኛውም ሰው፤ ልክ ሕገ ወጥ ይዘቶችን ወደ ድረ ገጽ እንደጫነ ሁሉ ተመሳሳይ ቅጣት ይጠብቀዋል" ብሏል።















