የአንዲት ሴትን እርቃን ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋራው 14 ዓመት ተፈረደበት

ስልክ የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጋናዊው የሞባይል ስልክ ጠጋኝ የአንዲት ሊባኖሳዊትን እርቃን ፎቶ ያለ ፈቃዷ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማውጣቱ የ14 ዓመት እስር ተፈረደበት።

ሶሎሞን ዶጋ የተባለው የ22 ዓመቱ ስልክ ጠጋኝ፣ የሴቲቷን እርቃን ፎቶ ያለ ፈቃዷ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከለጠፈ በኋላ ነው ፍርድ ቤት እስሩን የበየነበት።

ጋና ዋና ከተማ አክራ በሚገኘው ፍርድ ቤት ግለሰቡ የቀረበው፣ በወሲባዊ ብዝበዛ እና የሰውን የግል ምሥል ያለ ፍቃድ ለሌላ ወገን በማጋራት ነው።

የዐቃቤ ሕግ ዋና መርማሪ ማክስዌል ላንዮ እንዳሉት፣ ሊባኖሳዊቷ ሴት ስልኳን እንዲከፍትላት ለጠጋኙ ሰጥታዋለች።

ከዚያም ከግለሰቧ ፈቃድ ሳያገኝ በሕገ ወጥ መንገድ ስልኳ ውስጥ ያሉትን የግል ምሥሎቿን ወስዷል።

ከዚያም በኋላ ገንዘብ የማትከፍለው ከሆነ እርቃኗን የተነሳቻቸውን ፎቶግራፎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስፈራርቷትም ነበር።

ገንዘቡን አልከፍልም ብላ ስልክ ቁጥሩን ካገደችው በኋላ፣ ስልክ ጠጋኙ የእርቃን ፎቶዎቿን በማኅበራዊ ሚዲያ ለቋል።

ይህንን ድርጊት ከፈጸመ በኋላ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ታይቶ የ14 ዓመታት እስር ተፈርዶበታል።

ጋና ከሁለት ዓመታት በፊት በከለሰችው የመረጃ መረብ ደኅንነት ሕግ መሠረት፣ የሰዎችን እርቃን ፎቶ ያለ ፈቃዳቸው ማጋራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው።

ሰዎች ላይ ጫና አሳድሮ ገንዘብ ለመቀበል አልያም ለበቀል ሲባልም እርቃን ፎቷቸውን ማጋራት ከአምስት እስከ 25 ዓመታት በእስር ያስቀጣል።

የቀድሞ የፍቅር አጋራቸውን ለመበቀል ወይም ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የሰዎችን የእርቃን ምሥል ያለ ፈቃድ የሚለጥፉ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ ረገድ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና አዲስ ምዕራፍ ከፍታለች።

የተለያዩ ጥቅሞችን ለማግኘት የግሰቦችን ግላዊ ፎቶዎችና መረጃዎችን መስረቅ እና በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ለሕዝብ ማጋራት የበርካቶችን ሕይወት እያመሳቀለ ያለ የዘመናችን ክስተት ነው።

አገራትም ይህንን የወንጀል ድርጊት ለመከላከል እና ፈጻሚዎቹን ለመቅጣት አዳዲስ ሕጎችን እያወጡ እንዲሁም ያሏቸውን እያሻሻሉ ነው።