የካሜሮኑ ኮከብ ሳሙኤል ኢቶ 3.2 ሚሊዮን ፓውንድ ግብር ማጭበርበሩን አመነ

ሳሙኤል ኢቶ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች ሳሙኤል ኢቶ

የቀድሞው የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን አጥቂና የባርሴሎና ሁነኛ ተጨዋች የነበረው ሳሙኤል ኢቶ 3.2 ሚሊዮን ፓውንድ የግብር ማጭበርበር ውስጥ እጁ እንዳለበት አመነ።

የአራት ጊዜ የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች የተባለው ኢቶ ትናንት ሰኞ በስፔን ፍርድ ቤት ቀርቦ የ22 ወራት በእግድ የሚቆይ ፍርድ ተፈርዶበታል።

ይሁንና ያጭበረበረውን ገንዘብ እና ተጨማሪ 1.55 ሚሊዮን ፓውንድ ቅጣት ጋር ደምሮ መመለስ ይኖርበታል።

አቃቢ ሕግ ሳሙኤል ኢቶ ከማስታወቂያ ጋር በተያያዘ ያገኘው የነበረውን ገቢ ደብቆ ቆይቷል ሲል ነው የከሰሰው።

ይህም በፈረንጆቹ ከ2006 እስከ 2009 ድረስ የቆየ የማጭበርበር ድርጊት ነው።

ኢቶ በተመሳሳይ ክስ ሲከሰስ ከውጭ ተጫዋቾች የመጀመርያው አይደለም።

ላለፉት ዓመታት በተመሳሳይ ከግብርና ገቢ ስወራ ጋር በተያያዘ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ሊዮነል ሜሲ፣ ጆሴ ሞሪንሆ እና ኔይማር ተመሳሳይ ክስ ውስጥ አልፈዋል።

የ41 ዓመቱ ሳሙኤል ኢቶ አሁን የካሜሮን ብሔራዊ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሲሆን ባርሴሎናን የተቀላቀለው በ23 ዓመቱ፣ በ2004 ነበር።

ኢቶ ከባርሴሎና ሌላ ለሪያል ማድሪድ፣ ለኢንተር ሚላን፣ ለቼልሲ እና ኤቨርተን ቡድኖች ተጫውቷል።

ኢቶ ከምሥል ጋር የተያያዘውን መብቱን ሐንጋሪ አገር ለሚገኝ አንድ ኩባንያ ያስተላለፈ ሲሆን ይህንን ያደረገው ግን በዚያ አገር የግብር ተመኑ ከሁሉም የአውሮጳ አገር ዝቅተኛ በመሆኑ ነበር።

ሳሙኤል ኢቶ ለፍርድ ቤት ማጭበርበሩን ካመነ በኋላ ባደረገው የክስ ማቅለያ ንግግር፣ “የተከበረውን ፍርድ ቤት መረዳት ያለበት ያን ጊዜ ልጅ ነበርኩ፤ ሁሉንም ነገር አደርግ የነበረው በተወካዬ ማሪያ ማሳሌስ አማካኝነት ነበር” ብሏል።