በጊምቢ ለሰዓታት ከተፈጸመው ጥቃት የተረፉ የዐይን እማኞች ምስክርነት

በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙ መንደሮች ላይ ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ. ም. በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ንጹሀን ዜጎች እንደተገደሉ የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ገለጹ።
በዕለቱ ከጠዋቱ 3 ሰዓት አንስቶ እስከ ከሰዓት በኋላ ድረስ ታጣቂዎች የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በሰነዘሩት ጥቃት፣ ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በርካቶች እንደሞቱ የዐይን እማኞች ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ቤቶች እንደተቃጠሉባቸውና የቀንድ ከብቶችን ጨምሮ ሌላም ሀብት እና ንብረት እንደተዘረፈባቸውም ተናግረዋል።
በቶሌ ቀበሌ በሚገኙት ጉቱ፣ ጨቆርሳ፣ ስልሳው፣ በገኔ፣ ጫካ ሰፈር እና ሀያው በተባሉ መንደሮች (ጎጦች) የሚኖሩ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደተፈጸመ የዐይን እማኞቹ ገልጸዋል።
ትላንት ሰኔ 12 እና ዛሬ ሰኔ 13 በጥቃቱ ሳቢያ የተገደሉ ሰዎችን አስክሬን እየሰበሰቡና እየቀበሩ እንደዋሉና አሁን ላይ በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደተሰማሩ አክለዋል።
ከማል (ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ ተቀይሯል) የተባለ የዐይን እማኝ ወንድሙንና የወንድሙን ባለቤት በጥቃቱ ሳቢያ እንዳጣ ለቢቢሲ ተናግሯል።
“ጥቃቱ የጀመረው 3፡20 አካባቢ ነበር። እስከ 7፡00 [ታጣቂዎቹ] አልወጡም። ልዩ ኃይልና መከላከያ የገባልን 11፡00 ላይ ነው። እስከዚያ ድረስ ማንም ሊረዳን አልመጣም። የሚመለከተው አካልም አልረዳንም” ይላል።
በቶሌ ቀበሌ፣ ስልሳው የተባለው መንደር ውስጥ ተወልዶ ያደገው አርሶ አደር ከማል፣ እሱ በሚኖርበት አካባቢ “እስካሁን 250 ሰው ቀብረናል” ብሏል።
“ትላንት [እሁድ] ስንቀብር ዋልን። አሁን ደግሞ ሌሎችን ሊቀብሩ ሄደዋል” ያለው ከማል ገና አስከሬናቸው የሚነሳ ነዋሪዎች እንዳሉም ተናግሯል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ኦነግ-ሸኔ እንደሆኑና “ብሔር ለይተው፣ አማሮችን እንደጨፈጨፉ” አክሏል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች እንዲሁም መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመው ሸኔ በመባል የሚታወቀው ታጣቂው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደሆነ ሲገልጹ፣ ቡድኑ ግን ለጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥቃቱን በማስመልከት ሰኞ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ታጣቂዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙና የጊምቢው ጥቃትም መንግሥት አደራጅቶታል ባለው ኢ-መደበኛ ኃይል የተፈጸመ ነው ብሏል። ጨምሮም ይህ ክስተት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል።
በአሜሪካ የአማራ ማኅበር የአድቮኬሲ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሆነ ማንደፍሮ፣ ጥቃቱ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ መሆኑንና ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል የዓይን ምስክሮችን ጠቅሶ እንደዘገበው በጥቃቱ አብዛኞቹ የአማራ ብሔር ተወላጆች የሆኑ ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
እስካሁን ድረስ ስለተገዱ ሰዎች ቁጥር ይፋዊ መረጃ ባይሰጥም፣ ከዐይን እማኞች በተገኘው መረጃ መሠረት ከ200 በላይ ንጹሀን ዜጎች ሞተዋል።
ቢቢሲ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ጊምቢ ወረዳ እንዲሁም የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ ቢደውልም እስካሁን አልተሳካም። የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ግንኙነትን ምላሽ ለማካተት የተደረገው ጥረትም አልተሳካም።
“ቤተሰቦቻችን አልቀው እኛ አለን”
“እኔስ አንድ ወንድምና የወንድም እህት አጣሁ። ሙሉ ቤተሰቡን ያጣ ዘመዴ አለ። 21 ቤተሰብ የሞተበትም ሰው አለ እኮ። ልጆቹን፣ የልጅ ልጆቹን ያጣም አለ” ብሏል ከማል።
እሱ የሚኖርበት አካባቢ አቅራቢያ ባሉ ሦስት ጎጦች “250 ሰው እንደተቀበረ” እና ገና አስክሬናቸው ተፈልጎ የሚቀበሩ ሰዎች ስላሉ፣ የሟቾችን አጠቃላይ ቁጥር አሁን ላይ ለመናገር እንደሚከብድ ገልጿል።
“ቤተሰቦቻችን አልቀው እኛ አለን፣ ግማሹ ትላንት ተቀበረ። ግማሹ ዛሬ ይሰበሰባል። ትላንት ‘ይህን ሁሉ ሰው መቅበር አንችልም’ ብለው የተመለሱ አሉ” ሲል ከማል አክሏል።
ዛሬ ተጨማሪ የሰው ኃይል ለቀብር እንደሄደ ጠቅሶ “ምን ያህል ሰው እንደሞተ በዚህ መረዳት ይቻላል” ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቃቱን በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ዝርዝር ነገር ባያሰፍሩም፣ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚፈጸሙ እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን መንግሥታቸው እንደማይታገስ ገልጸዋል።
መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው እና እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሚለው ቡድን ታጣቂዎች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኦሮሚያ ክልል አመልክተዋል።
ከማል ጥቃቱ በሚፈጸምበት ወቅት ወደ እርሻ ሄዶ እንደነበርና ጥቃቱ መፈጸሙን እንደሰሙ ወደ መንደራቸው ሲመለሱ ሴቶችና ሕጻናት በብዛት ተገድለው እንደደረሱ ተናግሯል።
“ወረዳውን ‘ኧረ እባካችሁ እርዱን፣ ኧረ የመንግሥት ያለህ’ ብለን ስንደውልለት የሚረዳን ጠፋ። ኋላ ላይ በ11 ሰዓት ለይምሰል የሚረዳን መጣ። የተጠቃው አማራ ብቻ ነው። ብሔር ለይተው ‘እዚህ ምን ተደርጋላችሁ? በቃ ውጡ!’ ነው ያሉን። እዚህ ካደራችሁ መልሰን መጥተን እንጨፈጭፋችኋላን ብለውናል። የሦስት ቀን ሕጻን ሳይቀር ተጨፍጭፎብናል።”
ጥቃቱ እሱ የሚኖርበት መንደር ጋር ሲጀመር፣ ቤቶች ሲቃጠሉ ከሩቁ ተመልክቶ ወደ ቤቱ አቅራቢያ እንደሄደም እንዲህ ተናግሯል።
“እየገሰገስን ስንመጣ መንደሩ ተከቧል። እኛንም በጥይት አባረሩን። ቤት ውስጥ የነበሩ ሴቶችና ሕጻናት አለቁ። አርሶ አደሩን እያባረሩ በጥይት ገደሉ። ሸንኮራ ማሳ ውስጥ ተደብቀው ሲያለቅሱ የነበሩ ሕጻናት ሳይቀሩ ተገድለዋል።”
የነዋሪዎች ንብረት እንደተዘረፈና ከእንግዲህ በኋላም ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉም ከማል ተናግሯል።
“የቁም ከብት ቀርቶ ዶሮ የቀረው የለም። ተዘርፏል። የሞተው ሞቷል ለእኛ ለቀረው መፍትሄ እንዲሰጠን ነው የምንፈልገው። መንግሥት ካለ፣ ሕግ ካለ ከዚህ ያስወጣንና ወደ አገራችን ይመልሰን። እስካሁን ያዘነልን፣ ስህተት ነው ያለንም የመንግሥት አካል የለም” ብሏል።
ምዕራብ ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት ታጣቂ ቡድኑ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙ መንደሮች “ሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወት፣ በአካል እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት” ደርሷል ሲል ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጦ፣ በዚህም ጥቃት በንጹሃን ሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "በንጹሃን ዜጎች ላይ በሕገ ወጥ እና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት እና መተዳደሪያን ማውደም ተቀባይነት የለውም” በማለት፣ “በቤኒንሻንጉል እና በኦሮሚያ ክልሎች፣ ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር በሆነ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ሕይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም” ብለዋል።
“በጥቃቱ ልጄን አጥቻለሁ”
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አቶ ዓሊ (ስማቸው ተቀይሯል) በጊምቢ ወረዳ፣ በስልሳው ቀበሌ ትኖር የነበረች ልጃቸውን በጥቃቱ እንዳጡ ተናገረዋል።
ሁለት ልጆቻቸው እና የቀድሞ ባለቤታቸው አርጆ በምትባለው ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን ገልጸው፣ መንገዱ ከ8 ወራት በላይ ዝግ በመሆኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሳይገናኙ መቅረታቸውን እና አሁን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየኖሩ እንደሆ ገልጸዋል።
በቅዳሜው ጥቃት የ16 ዓመት ልጃቸው እንደተገደለችም ተናግረዋል።
“ቅዳሜ ረፋድ ሦስት ሰዓት አካባቢ ደውለው ጦርነት ተነሳ አሉን። ማነው? ስንል ኦነግ ሸኔ ገባብን አሉን። ሁሉም ሱቅ ተዘጋጋ። እንደ አጋጣሚ ወደ እርሻ የሄዱ ነበሩ፣ እነሱ ናቸው ደውለው ያናገሩን. . . የአንድ ሰው ስልክ ነበረኝ እና እሱ ጋ ስደውል ተኩስ አለ አለኝ። ቃጣሎም አለ አለኝ። እሺ አልኩኝና ትንሽ ቆይቼ ስሞክር ሬሳ በሬሳ ነው ማንም የሚደርስላቸው የለም። ምሽት ላይ ነው እነሱም ወደ ሰፈር የገቡት” ሲሉ ስለ ሁኔታው አስረድተዋል።
አቶ ዓሊ፣ አካባቢው በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ጥቃቱ ከጠዋት እስከ ማምሻው 11 ሰዓት አካባቢ መቆየቱንም ተናግረዋል።
“አሁን የተረፉት አሉ። ሬሳው ግን በአብዛኛው አልተነሳም። ገጠር ውስጥ ገባ ገባ ያሉ አሉ። እዚያ አካባቢ አሁንም አልተነሳም እያሉ ነው” በማለት አሁን ስላለው ሁኔታ የተናገሩት ነዋሪው፣ ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት የፌደራልም ይሁን የክልል የፀጥታ አካል እንዳልነበረ ተናግረዋል።
ከጥቃቱ በኋላ ግን የፀጥታ አካላት ወደ አካባቢው እንደገቡ አክለዋል።
“ባለቤቴ፣ የልጄ እናት እዚያ ነው ያለቸው። ‘እየራበን ነው። ትላንት ጠዋት ራሱ እህል ያልቀመስን ሰዎች አለን። ትነሳላችሁ ብለው ሰብሰበውናል ግን ያገኘነው ነገር የለም’ ነው ያለችን” ብለዋል።
እሳቸው አሁን በሚኖሩበት፣ ጥቃቱ ከተፈፀመበት ብዙም በማይርቅ እና ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚዋሰነው የቤንሸንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ ነዋሪዎች ስጋት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
“ቤቴ ተርፏል፣ ሱቄ ተዘርፏል”
ሌላው የዐይን እማኝ ሰይድ (ስሙ ተቀይሯል) ጥቃቱ ቅዳሜ ዕለት ከጠዋቱ 3፡00 እስከ 9፡00 ሲፈጸም እንደቆየና መንገድ ተዘጋግቶ ስለነበር እስከ 7፡00 ድረስ የፀጥታ ኃይል እንዳልገባ ይናገራል።
እስከ ሰኞ ሰኔ 13 ረፋድ ባለው መረጃ መሠረት “በጉቱ 8 ቤታቸው ውስጥ ሳሉ የተቃጠሉ ሰዎችን ጨምሮ 35 ሰዎች ተቀብረዋል።በጨቆርሳ 102 ሰዎች ተቀብረዋል። በስልሳው 102 ሰዎች ተቀብረዋል። በገኔ ገና አስክሬን ባይነሳም እስካሁን 95 ሰዎች ሞተዋል። በሀያው እስካሁን አስክሬን አልተነሳም” ብሏል።
ጥቃቱ ከኦሮሚያ ክልል ተሻግሮ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ሁለት መንደሮች እንደቀጠለም ሰይድ ገልጿል። አሁን በአካባቢው ልዩ ኃይል እና መከላከያ ሠራዊት እንደገባም አክሏል።
“እኛ ወደ እርሻ ማሳ እንደሄድን የታጠቀው ኦነግ-ሸኔ በቡድን በቡድን ሆኖ መጣ። መጡ፣ ገቡ፣ ዝም ብሎ መግደል ብቻ ነበር። አማርኛ ተናጋሪው ቤት እየገቡ ገደሉ” ሲል ያየውን ተናግሯል።
ቤቶች እንደተቃጠሉ፣ ንብረት እንደተዘረፈ፣ የቀንድ ከብቶችም እንደተዘረፉ ሰይድ ተናግሯል።
“አንድ ቦታ 8፣ አንድ ቦታ 2፣ ጉቱ መንደር 12 ደግሞ ሰዎች ከነሕይወታቸው መቃጠላቸውን ሰምተናል። እዚያ ያለው እኮ ገበሬ ነው። የታጠቀ ኃይል አይደለም” ብሏል።
አሁን ላይ በአካባቢው እንቅስቃሴ እንደሌለም የዐይን እማኙ ገልጿል።
“ትላንት ወረዳው መጥቶ አይቶን ሄደ እንጂ ምንም አላደረገልንም። ሕዝቡ ንብረቱ ተዘርፏል፣ ቤቱ ተጥሏል የያዘው ነገር የለው። በረሃብ ማለቁ ነው።”
ከአካባቢው ታግተው የተወሰዱ ሰዎች እንደነበሩ ጠቅሶ፣ “ጫካ ሲደርሱ ግን ገድለዋቸዋል። ጫካ ውስጥ አንድ ቦታ 50 አስክሬን ተገኝቷል” ብሏል።
ጥቃቱ ሲጀመር አርጎ ጉደቱ ወደሚባል አካባቢ በሞተር እየሄደ እንደነበርና ተመልሶ “ተራራ ላይ [ተደብቆ] እንደዋለ” ተናግሯል።
መከላከያ ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ ወደ ቤቱ እንደተመለሰ የተናገረው ሰኢድ “ወንድሞቼ እስከ 7 እና 8 ቤተሰብ አልቆባቸዋል” ብሏል።
ታጣቂዎቹ “መትረየስ ይዘው” ወደ አካባቢው እንደገቡና ጥቃቱ “ብሔር የለየ” እንደሆነ አክሏል።
ሰኢድ ቤቱ ቢተርፍም የሸቀጥ ሱቁ እንደተዘረፈ ተናግሯል።
አሁን ላይ ቤት ንብረቱን ያጣው የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲሁ መንገድ ላይ እንዳለ እና ስጋት እንደሸበባቸው አክሏል።
“እኛ በሰላም አገራችን ኢትዮጵያ ናት ተብለን ተቀምጠን ነበር። የሚመለከተው አካል ከዚህ ቢያነሳን እንመርጣለን። ዛሬ እንዲህ ከሆነ ነገስ ቢመጡ?” ሲል አሁንም ስጋት ውስጥ እንዳሉ ገልጿል።
“ድረሱልን”
አቶ ሙባረክ (ስሙ ተቀይሯል) የተባሉ ነዋሪ ደግሞ ጥቃቱ ቅዳሜ ጠዋት 2፡15 አካባቢ መጀመሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በጥቃቱ ምክንያት በእሳቸውም ይሁን በቤተሰቦቻቸው ላይ የደረሰ አካላዊ ጉዳት አለመኖሩን ያስረዱት ነዋሪው፣ በሚያወቋቸው በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።
ነዋሪው አንዳንድ ቤተሰቦች “ከ15 እና 20 የሚደርሱ ሰዎች” መቅበራቸውን መመልከታቸውን ገልጸው፣ እሳቸው የሚያውቋቸው ከ80 ዓመት አዛውንት እስከ 2 ወር ጨቅላ መገደላቸውን ተናግረዋል።
በስጋት ምክንያት እስካሁን ድረስ ያልተነሱ “ከዚህ በላይ የሚገመቱ” አስክሬኖች እንዳሉ ገልጸዋል።
አሁን የኦሮሚያ ፖሊስ እና መከላከያ ሠራዊት “ጥበቃ እያደረጉልን ነው” ያሉት ነዋሪው፣ አሁን “የተሻለ” የሚባል ሁኔታ ላይ ነን ብለዋል።
“ከጥቃቱ በኋላ የተደረገልን ድጋፍ በሕይወት እንድንቆይ መጠበቅ ብቻ ነው። ሌላ የተደረገለን ድጋፍ የለም” ብለዋል።
“ጥቃቱን ለመግልጽ ይከብዳል። ለሰው ልጅ ተቆርቋሪ፣ አሳቢ አለሁ ካለ ይሄንን ቦታ መጥቶ መጎብኘት በጣም አስፈላጊ ነው። ድረሱልን” ሲሉ አቶ ሙባረክ አክለዋል።
*በዚህ ዘገባ ውስጥ የተካተቱት ሰዎች ካለባቸው የደኅንነት ስጋት አንጻር ስማቸው እንዳይገለጽ ያደረገው ቢቢሲ ነው።












