ከመኪና እየወረዱ በጅምላ ሲገደሉ የሚያሳየው ቪዲዮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መፈጸሙን ኢሰመኮ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA SCREEN GRAB
በትናንትናው ዕለት በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ሲዘዋወር የነበረው በርካታ ግለሰቦች ከመኪና እየወረዱ ሲደበደቡና በጅምላ ሲገደሉ የሚያሳየው ቪዲዮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተፈጸመ መሆኑን ኢሰመኮ አስታወቀ።
ቪዲዮውን በርካቶችን ያሳዘነና ያስደነገጠ ሲሆን እነዚህ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተገደሉ የተባሉትም ግለሰቦች ቁጥራቸው ወደ 30 መሆኑን ኢሰመኮ በትናንትናውዕለት ሰኔ 11፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
ድርጊቱ የተፈጸመው በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ ልዩ ቦታው እንቶሊ በሚባል ስፍራ መሆኑንና በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም መሆኑም ተገልጿል።
ቪዲዮውን የመረመረው ኢሰመኮ፣ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ባወጣው “በኢትዮጵያ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች እና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ምርመራ” በሚል መጋቢት 2፣ 2014 ዓ.ም ያወጣው ሪፖርት ከተካተቱ ከህግ ውጭ የተፈጸመ የግድያ ድርጊት ክስተቶች አንዱ መሆኑን ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተሟላ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነትም እንዲረጋገጥ በድጋሚ አሳስቧል።
በዚሁ ሪፖርት ላይ ኢሰመኮ ከምስክሮች እና በስፍራው በመገኘት በመስክ ምልከታ ያሰባሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግ ድርጊቱ የተፈጸመበትን ስፍራ ጠቅሶ ወቅቱም በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት ቀኑ በትክክል ያልታወቀ መሆኑንም አስፍሯል።
የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በሁለት የጭነት መኪኖች ያመጡዋቸውን እና ወደ 30 የሚጠጉ የኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው ያሏቸውን ሰዎች በጅምላ በጥይት ደብድበው መግደላቸውን ገልጿል።
ኢሰመኮ ቪዲዮውን ላይ ተጨማሪ ማጣራትና የቴክኒክ ምርመራ ካደረገ በኋላ ከዚህ ቀደም በመስክ ምርመራ በለየው ስፍራና በቪዲዮው ላይ ያለውን ስፍራ ማነጻጸሩን አስታውቋል።
ምስሉ የተቀረጸበት ቦታ ለማነጻጸርና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የቴክኒክ ምርመራዎችን ማድረጉን ገልጾ ቪዲዮው ላይ ያለው ከፍርድ ውጭ የተፈጸመው የጅምላ ግድያ ከዚህ ቀደም ኢሰመኮ በሪፖርቱ ያካተተው ስለመሆኑ በአሳማኝ ደረጃ ማስረጃ ማግኘቱንና ማረጋገጡን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በበኩሉ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ መንግሥት ንጹሃንን የመጠበቅ ኃላፊነቱ በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ብሏል።
ከሰሞኑ በተጨማሪ በጋምቤላ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ ግድያን ፈፅመዋል የሚሉ መረጃዎች እየደረሱት እንደሆነ ኢሰመኮ አስታውቋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር የነበረ ቪዲዮ ላይ እጁን ወደ ኋላ የታሰረ ግለሰብ፣ የደንብ ልብስ በለበሱ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በጥይት ተመትቶ ሲወድቅ የሚያሳይ ነው።
ኢሰመጉም በበኩሉ ሰኔ 11 2014 ዓ.ም በተሰራጨ ቪዲዮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የታጠቁ እና የጸጥታ አካል መለዮ የለበሱ ሰዎች በመኪና ላይ ተጭነው የነበሩ ሰዎን ሲደበድቡ እና እየወረዱ ሲረሽኑ ታይቷል ብሏል።
ድርጊቱ በማን፣ የት እንደተፈጸመ ኢሰመጉ እንዳላወቀ ገልጾ ከህግ አግባብ ውጭ የሆነ ግድያ መሆኑን በመጥቀስ። ኢሰመጉ ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ ግድያ እየተባባሰ መምጣቱን ጠቅሷል።
በተጨማሪም በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7፣ 2014 ዓ.፥ም አንድ ወጣት የጸጥታ አካላት መለዮ በለበሱ ሰዎች እጁን ታስሮ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በጥይት ተደብድቦ ከህግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ተገድለዋል ብሏል።
በዚሁ ዕለትም በተደራጁ ቡድኖች በርከት ያሉ ነዋሪዎች ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል እንዲሁም ማንነትን መሰረት ያደረገ በሚመስል ጥቃት በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበው መገደላቸውንና ከዚህም ውስጥ አባት እና ልጅ ይገኙበታል በማለት ኢሰመጉ በመግለጫው አስፍሯል።
ኢሰመኮ አርብ ባወጣው መግለጫ አማጺያን በጋምቤላ ከተማ የፈጸሙት ጥቃት በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ "በተለይ በጥቃቱ ተሳትፈዋል ወይም ተባብረዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ቤት ለቤት በመሄድ ጭምር ግድያዎች እንደተፈጸሙ" ኢሰመኮ ከተለያዩ ምንጮች ካሰባሰበው መረጃዎች እንደተረዳ አመልክቷል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለም (ዶ/ር) በፀጥታ ኃይሎች የሚወሰዱ እርምጃዎች በሙሉ የሰብአዊ መብቶችን መርሆችን ሊከተሉ እንደሚገባ አሳስበው፤ በተለይም ሕይወት ሊያጠፋ ከሚችል ተመጣጣኝ ካልሆነ የኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡና በፀጥታ ኃይሎች የተወሰዱ ሕገ ወጥ ተግባራት ላይ በአስቸኳይ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስበዋል።












