ከሰሞኑ የጋምቤላ ጥቃት ጀርባ ያለው ቡድን ማን ነው?

ጋምቤላ ክልልን የሚያሳይ ካርታ

ማክሰኞ ሰኔ 07/2014 ዓ.ም ማለዳ ላይ የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት-ሸኔ በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ ላይ ጥቃት በመክፈት ከተማዋ ለቀናት ከተለመደ እንቅስቃሴዋ ውጪ ሆና ቆይታለች።

የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጋትሉክ ቡኦም ፓል ጥቃታቸው የጀመረው ከከተማው 4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደምቢዶሎ መውጫ ላይ ከሚገኝ ጫካ በመነሳት እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለተወሰኑ ሰዓታት በርካታ የከተማዋን ክፍሎች ተቆጣጥረው እንደነበር የሚናገሩት ሊቀመንበሩ የመንግሥት ኃይሎች ወደ ከተማው በማፈግፈግ ውጊያው “በሕዝብ መካከል” ስለነበር፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና እርሳቸው በመነጋገር ከከተማው መውጣታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በወቅቱ የክልሉ መስተዳደርም ታጣቂዎቹ የተወሰነውን የከተማዋን ክፍል ተቆጣጥረው እንደነበርና ፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ጠንካራ እርምጃ አማጺያኑን በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ከተማዋ ማስወጣት መቻሉን አሳውቋል።

አቶ ጋትሉክ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ዕቅዳቸውን አሳክተው በወታደራዊ ካምፕ ላይ ጉዳት አድርሰው በርካታ መሣርያም መማረካቸውን ቢናገሩም፤ የክልሉ ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ግን በርካታ የታጣቂዎቹ ቡድን አባላት በከተማዋ ውስጥ መገደላቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከማክሰኞው ጥቃት በኋላ ረቡዕ ዕለትም የጋምቤላ መደበኛ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ ቆይቶ፣ ሐሙስ ዕለት ነዋሪው ወደ ተለመደ ሥራው እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እና ፀጥታ ኃይሉም ከጥቃቱ በኋላ በሕዝቡ ውስጥ ተደብቀዋል ያላቸውን የታጣቂ ቡድኑ አባላትን አድነው በመያዝ ላይ ናቸውን የክልሉ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር በኮንፌዴሬሽን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያ ለመመስረት እንደሚታገሉና አሁን የፈጸሙት ጥቃት ዓላማ ከተማዋን መቆጣጣር እንደነበር አቶ ጋትሉክ ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ ላይ የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ በታጣቂዎቹ ላይ “ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን፣ በወገን ጦር ላይም መጠነኛ ጉዳት መድረሱን” ተናግረው ነበር።

የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር በበኩላቸው ትልቅ ኪሳራ የደረሰው በመንግሥት ወገን ላይ እንደሆነና ከእነርሱ ወገን ሦስት ተዋጊዎቻቸው ሲሞቱ፣ ሌሎች ቁጥራቸውን ያልገለጿቸው ደግሞ መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል።

የከተማው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩትና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጩ ምስሎች እንዳሳዩት በርካታ የታጠቂው ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ አስከሬኖች በጋምቤላ ከተማ መንገዶች ላይ ታይተዋል።

መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው እና ሸኔ በሚል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ የሕዝብ ግንኙነት እንደሆነ የሚነገረው ኦዳ ተርቢ፣ የቡድኑ ታጣቂዎች ከጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጋር የተሳካ የመቀናጅት ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጾ ነበር።

በክልሉ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑ እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ግለሰብ ይህን ጥቃት የፈፀሙት ከውጪ የመጡ አካላት ብቻቸውን ሳይሆን በሕዝቡ እና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ እገዛ አድርገዋል ሲሉ ይወነጅላሉ።

የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር ከከተማው በቅርብ ርቀት፣ አንፊሎ እና ድንበር አካባቢ መሽገው ይገኛሉ ያሉት ግለሰቡ፣ ከደቡብ ሱዳን የመጡ ተፈናቃዮች ጋርም በመቀላቀል እገዛ እንደሚያገኙ ይናገራሉ።

በጋምቤላ ከተማ ማክሰኞ ዕለት በነበረው ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ከተለያዩ ምንጮች አጣርቷል።

የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጋትሉክ ቡኦም ፓል

የፎቶው ባለመብት, Gatluk/FB

የምስሉ መግለጫ, የጋምቤላሕዝብ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጋትሉክ ቡኦም ፓል

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ከተደረገው ብሔራዊ ምርጫ በኋላ መመስረቱ የሚነገረው የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) በሺዎች የሚቆጠሩ አባላትና ታጣቂዎች እንዳሉት ይናገራል።

የድርጅቱ ሊቀ መንበርና ምክትል፣ የኢህአዴግ አጋር ድርጅት በመሆን ክልሉን ሲያስተዳድር የነበረው የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባል ሆነው በክልሉ በተለያየ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ አገልግለዋል።

በዚህም ሊቀ መንበሩ በተለያዩ የክልሉ መንግሥት ቢሮዎች ከምክትል ኃላፊነት እስከ የክልሉ ኮሌጅ ዲንነት ድረስ መስራታቸውንም ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ኃላፊነቶች ውስጥ ያገለገሉት አቶ ጋልዋክ፣ በባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፣ በከተማና ልማት፣ በትምህርት ቢሮዎች ውስጥ በምክትል ኃላፊነቶች እንዲሁም በክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ እና ጥቃቅን እና አነስተኛ በከፍተኛ አመራርነት መስራታቸውን ይናገራሉ።

ጋነግ “በዲሞክራሲ እና በፍትሕ የሚያምን፣ ለጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት የሚታገል ድርጅት ነው” እንደሆነ የሚገልጽ ሲሆን፣ ፓርቲው ከሌሎች በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር አጋርነት በመፍጠር የፌደራሊስት ኃይሎች ግንባር ተሳታፊ ነበር።

ይህ የፌደራሊስት ኃይሎች የተባለው ስብስብ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በተደጋጋሚ ወደ መቀለ በመመላለስ ከህወሓት ጋር ሲመክር እንደነበር ሊቀመንበሩ ያስታውሳሉ።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ጦርነቱ ሲቀሰቀስ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩት የግንባሩ ሊቀመንበር ጋትሉክ “ከሦስት ወራት በላይ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ጋር አለህ በሚል” ታስረው መቆየታቸውን ይናገራሉ።

ሊቀመንበሩ “የተጭበረበረ ነው” በሚሉት በ2013 ሰኔ ወር ላይ በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ላይ መሳተፋቸውንና፣ “ከዚያ በኋላ ሊያስሩኝ ሲሞክሩ ወደ በረሃ ገባሁ” የሚሉት ጋልቶክ ለጋምቤላ ሕዝብ እኩልነት ትግል መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር ከቀናት በፊት በጋራ ሆኖ ጥቃት ከሰነዘረው የኦሮሞ የነጻነት ሠራዊት የመሣርያ እና ሥልጠና ድጋፍ እንደሚያገኝ ሊቀመንበሩ አረጋግጠዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ የሆነው ኩምሳ ድሪባም (ጃል መሮ) ለቢቢሲ ከግንባሩ አመራሮች ጋር የረዥም ጊዜ ትውውቅ እንዳላቸውና ለታጣቂዎቻቸውም ስልጠና ሲሰጡ እንደነበርም ገልጿል።

ሊቀመንበሩ የሌላ አገር ዜግነት እንዳላቸውና በጋምቤላ ክልል ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ በሰሩባቸው ጊዜያት የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉ ክስ የሚቀርብባቸው ሲሆን፣ ይህ ጉዳይ እንደማይመለከታቸው ይናገራሉ።

ሁለቱም ክሶች ከሊቀመንበሩ ጋር በተመሳሳይ ስም የሚታወቁት ምክትላቸውን የሚመለከት መሆኑንና ግለሰቡ የአሜሪካ ዜግነት እንዳለው አምነው፣ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ፈጽመዋል መባሉን “መሠረተ ቢስ ውንጀላ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ጋትሉክ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን፣ ሊቀመንበሩ ጋትሉክ ቡኦም ፓል ምክትላቸው ደግሞ ጋትሉክ ፓልቴርጋር ይባላሉ።

የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር እንጂ በቀጥታ ከህወሓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለው ሊቀ መንበሩ ጠቅሰው ነገር ግን “ከህወሓት ጋር ያለን የዓላማ አንድነት ነው” በማለት ተናግረዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግሥት ሸኔ የሚለውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን እና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) በሽብርተኛነት በመፈረጅ ሕገ ወጥ ቡድኖች ማድረጉ ይታወሳል።

የጋምቤላ ከተማን በሚያቋርጠው ወንዝ ላይ በጀልባ የሚጓዙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, GAMBELLA TOURISM

ጥቂት ስለ ጋምቤላ

በምዕራብኢትዮጵያ የሚገኘው የጋምቤላ ክልል ዋና ከተማው ጋምቤላ ሲሆን ከደቡብ ሱዳን፣ ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ክልል ሕዝቦች ጋር ይዋሰናል።

አኝዋክ፣ኮሞ፣መዠንገር፣ኑዌር እና ኦፖ የሚባሉ አምስት ብሔረሰቦች አሉት።

በተጨማሪም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የተወጣጡ ሌሎች ብሔረሰቦችም የሚኖሩበት ክልልነው። ከዚህ ቀደም ባለው መረጃ የክልሉ ሕዝብ ብዛት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሲሆን በኢትዮጵያ ትንሽ ሕዝብ ከሚኖርባቸው ክልሎች አንዱ ነው።

ለእርሻተስማሚ ለም መሬት ያለው የጋምቤላ ክልል፣ በተጨማሪም ከዓመት ዓመት የሚፈሱ ሁለት ግዙፍ ወንዞች ባለቤት ነው።

ክልሉ በተለያዩ ጊዜያት ብሔርን መሠረት ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ግጭቶች ያጋጠሙት ሲሆን፣ በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን ሰርገው የሚገቡ ታጣቂዎችም ጥቃት ይፈጽሙበታል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት መረጃ ከሆነ ክልሉ ከ480 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መኖርያ ነው።

ክልሉን የሚመራው የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕዴን) የተለያዩትን የክልሉ ብሔሮች ይወክሉ የነበሩ ቡድኖችን በማዋሃድ የተመሰረተ ነው።

ጋሕዴን ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ አጋር ድርጅት የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ አባል ነው።