በርካቶችን ያስደነገጠው የጋምቤላው ቪዲዮ እና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መግለጫ

የፎቶው ባለመብት, social media
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም በጋምቤላ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ ግድያን ጨምሮ የመብት ጥሰቶችን ስለመፈጸማቸው መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን ገለጸ።
ኮሚሽኑ በጋምቤላ በክልሉ ልዩ ኃይል እና መደበኛ ፖሊስ ከሕግ አግባብ ውጭ የተፈጸሙ የኃይል እርምጃዎች በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ ነዋሪዎች ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተጋለጡ መሆናቸውንና ከሕግ ውጪ ግድያ መፈጸሙን መረጃዎች እየደረሱት እንደሆነ አመልክቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከቀናት በፊት በጋምቤላ ከተማ ውስጥ የተፈጸመውን የአማጺያን ጥቃትን ተከትሎ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ እየተዘዋወረ ያለው ቪዲዮ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።
በቪዲዮው ላይ እጁን ወደ ኋላ የታሰረ ግለሰብ፣ የደንብ ልብስ በለበሱ ታጠቂዎች በተደጋጋሚ በጥይት ተደብድቦ ሲወድቅ ይታያል።
ቢቢሲ ቪዲዮው የት እና መቼ እንደተቀረጸ እንዲሁም ስለትክክለኛነቱ መረጋገጫ ባያገኝም፣ ጋምቤላ ውስጥ የተከሰተ ሳይሆን እንደማይቀር በርካቶች እየተናገሩ ነው።
የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም አርብ ሰኔ 10/2014 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ባወጣው በዚሁ መግለጫው ላይ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ ግድያ ስለመፈጸማቸው መረጃ እንደደረሰው ገልጿል።
አማጺያን በጋምቤላ ከተማ የፈጸሙት ጥቃት በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ "በተለይ በጥቃቱ ተሳትፈዋል ወይም ተባብረዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ቤት ለቤት በመሄድ ጭምር ግድያዎች እንደተፈጸሙ" ኢሰመኮ ከተለያዩ ምንጮች ካሰባሰበው መረጃዎች እንደተረዳ አመልክቷል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለም (ዶ/ር) በፀጥታ ኃይሎች የሚወሰዱ እርምጃዎች በሙሉ የሰብአዊ መብቶችን መርሆችን ሊከተሉ እንደሚገባ አሳስበው፤ በተለይም ሕይወት ሊያጠፋ ከሚችል ተመጣጣኝ ካልሆነ የኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡና በፀጥታ ኃይሎች የተወሰዱ ሕገ ወጥ ተግባራት ላይ በአስቸኳይ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስበዋል።
ባለፈው ማክሰኞ በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ ላይ መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመው ቢያንስ አርባ ሰዎች መገደላቸውና በርካቶች መቁሰላቸው ተዘግቧል።
በአማጺያኑ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተዘዋወረ ያለውን ቪዲዮ በመጥቀስ ከጥቃት ጋር በተያያዘም የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ እርምጃ እየወሰዱ ነው የሚል ክስ እየቀረበ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች ባልታጠቁ ሰዎች ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ ጥቃቶችና ግድያዎችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በተደጋጋሚ መጋራታቸው፣ በሕግ ተጠያቂ በመሆን ጉዳይ ላይ በስፋት ጥያቄ አስነስቷል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ በትዊተር ገጻቸው የፀጥታ ኃይሎች “ማንኛውንም ኦሮሞ ነው ብለው በጠረጠሩት ግለሰብ ላይ ግድያዎችን እየፈጸሙ” ነው በማለት ከስሰዋል።
የጋምቤላ ክልል መስተዳደር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ኡጋቶ አዲንግ ቢቢሲ ጉዳዩን አስመልክቶ ላቀረበላቸው ጥያቄ “ፕሮፓጋንዳ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።
እስካሁን በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ላይ ጋምቤላ ውስጥ የተከሰተ ነው በሚል እየተዘዋወረ ያለውን ቪዲዮ በተመለከተ ክልሉ በይፋ ያለው ነገር የለም።
ማክሰኞ ሰኔ 07/2014 ዓ.ም ማለዳ ላይ አማጺያኑ በጋምቤላ ከተማ ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ ከተማዋ ለቀናት ከተለመደ እንቅስቃሴዋ ውጪ ሆና ቆይታለች።
አማጺያኑ ለተወሰኑ ሰዓታት በርካታ የከተማዋን ከፍሎች ተቆጣጥረው የነበረ ሲሆን፣ የክልሉ ፀጥታ ኃይል በወሰደው እርምጃ ከተማዋን ከታጣቂዎቹ ማስለቀቁን አሳውቋል።
ከማክሰኞው ጥቃት በኋላ ረቡዕ ዕለትም የጋምቤላ መደበኛ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ ቆይቶ፣ ሐሙስ ዕለት ነዋሪው ወደ ተለመደ ሥራው እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የክልሉ ቃል አቀባይ ትናንት አመሻሽ ላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጨምረውም አሁንም የፀጥታ ኃይሉ ከጥቃቱ በኋላ በሕዝቡ ውስጥ ተደብቀዋል ያላቸውን የታጣቂ ቡድኑ አባላትን አድነው በመያዝ ላይ ናቸው ብለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ ላይም የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ በታጣቂዎቹ ላይ “ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን፣ በወገን ጦር ላይም መጠነኛ ጉዳት መድረሱን” ተናግረዋል።
የከተማው ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩትና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጩ ምስሎች እንዳሳዩት በርካታ የታጠቂው ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ አስከሬኖች በጋምቤላ ከተማ መንገዶች ላይ ታይተዋል።
መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው እና ሸኔ በሚል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ የሕዝብ ግንኙነት እንደሆነ የሚነገረው ኦዳ ተርቢ፣ የቡድኑ ታጣቂዎች ከጋምቤላ ነጻነት ግንባር ጋር የተሳካ የመቀናጅት ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጾ ነበር።
ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰነው የምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሆነው የጋምቤላ ክልል ታጣቂዎች ከሚንቀሳቀሱባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ እና የከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጋር ይዋሰናል።












