በምዕራብ ወለጋ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 200 ሰዎች ተገደሉ

ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ መንደሮች ላይ ታጣቂዎች ባለፈው ቅዳሜ በፈጸሙት ጥቃት እጅግ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚኖሩባቸው መንደሮች በተፈጸመው ጥቃት በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና ሺዎች ደግሞ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል የዓይን ምስክሮችን ጠቅሶ እንደዘገበው በጥቃቱ አብዛኞቹ የአማራ ብሔር ተወላጆች የሆኑ ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቃቱን በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ዝርዝር ነገር ባያሰፍሩም በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚፈጸሙ እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን መንግሥታቸው እንደማይታገስ ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ እና መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመው ሸኔ በመባል የሚታወቀው ታጣቂው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንደሆነ ሲገልጹ፣ ቡድኑ ግን ለጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጓል።
በአሜሪካ የአማራ ማኅበር የአድቮኬሲ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሆነ ማንደፍሮ ጥቃቱ የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ መሆኑንና ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው መንግሥት ኦነግ ሸኔ ሲል በአሸባሪነት በፈረጀውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚል በሚጠራው ታጣቂ ቡድን ነው ያሉት አቶ ሆነ፣ ከአካባቢው አሰባስበናል ባሉት መረጃ “ታጣቂው ቡድን የአማራ ተወላጆች የሚኖሩባቸውን 5 መንደሮችን ኢላማ በማድረግ ግድያውን መፈጸሙን” ገልጸዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ የመንግሥት ሠራዊት በአካባቢው መሠማራቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም የተገደሉ ሰዎች አስከሬኖች እየተሰበሰበ መሆኑንና እሁድ ዕለትም በርካቶች በተዘጋጁ የጅምላ መቃብሮች አንድ ላይ መቀበራቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ስለጥቃቱ የተባለው
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው እና እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሚለው ቡድን ታጣቂዎች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የኦሮሚያ ክልል አመልክተዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት ታጣቂ ቡድኑ ቅዳሜ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም. የአካባቢው ነዋሪ በሆኑ “ሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወት፣ በአካል እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት” መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ዛሬ ሰኞ "በንጹሃን ዜጎች ላይ በሕገወጥ እና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት እና መተዳደሪያን ማውደም ተቀባይነት የለውም” በማለት “በቤኒንሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር በሆነ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም” ብለዋል።
ጨምረውም ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላም እና ደኅንነትን መመለስ መንግሥታቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጦ፣ በዚህም ጥቃት በንጹሃን ሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጥቃቱን አስመለክተው ባወጡት መግለጫ ላይ ጥቃቱ ኢላማ ያደረጋቸው ሰላማዊ ሰዎችን በተመለከተ በዝርዝር ምንም ያሉት ነገር የለም።
የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም የክልሉ መንግሥት፣ በጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ተፈጸመ በተባለውና ዝርዝሩ በይፋ ላልተገለጸው ጥቃት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተጠያቂ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን “በንጹሃን ላይ የተፈጸመ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት” ሲል ገልጾታል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለቡድኑ ጥቃት ምክንያቱ በፌደራል እና በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እየተወሰደበት ያለው እርምጃ መሆኑን ገልጾ፣ “ይህንን እርምጃ መቋቋም ሲያቅተው በንጹሃን ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ፈጽሟል” ብሏል።
ይህንን በምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ከፌደራል መንግሥቱ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ነዋሪዎች አሁንም ስጋት ላይ ናቸው
መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተባለው ቡድን ላይ ተከታታይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት አሳውቋል።
ቅዳሜ ዕለት የተፈጸመው ጥቃትም ከዚሁ መንግሥት እየወሰደ ካለው እርምጃ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ኮሚሽኑ በጥቃቱ በሰዎች እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን፣ አሁንም በአካባቢው ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት እንዳለ እና ነዋሪዎች ከመንግሥት በአፋጣኝ ድጋፍ እንዲደርስላቸው እየጠየቁ መሆናቸውን ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጥቃቱን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ ላይ ጥቃቱ ኢላማ ያደረጋቸው ሰላማዊ ሰዎችን በተመለከተ በዝርዝር ምንም ያሉት ነገር ባይኖርም የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ነው።
በተለይም የጥቃቱ ዋነኛ ሰለባ የሆኑት በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የአማራ ብሔር አባላት እንደሆኑና በጥቃቱ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር በተለያየ መጠን እያስቀመጡ ይገኛሉ።
ከዚህ ቀደምም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በፈጸማቸው ተመሳሳይ ጥቃቶች በተለይ የአማራ ብሔር አባላትን ኢላማ አድርጓል ተብሎ ክስ ሲቀርብበት እና ሲያስተባብል መቆየቱ ይታወሳል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተሰየመው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚንቀሳቀስባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ እየወሰዱ ሲሆን፣ በቡድኑ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ይህንን ባለፈው ቅዳሜ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ቡድኑ በነዋሪዎች ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎም የፌደራል እና የክልሉ የፀጥታ አካላት በታጣቂው ቡድን ላይ የሚወስዱትን እርምጃ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኦሮሚያ ክልል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ከዚሁ ጥቃት ጋር በተያያዘ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የመከላከል እርምጃዎችን እንዲወስድ ለመንግሥት ጥሪ አቅርበዋል።
ጨምረውም መንግሥት “በማንኛውም ሁኔታ ሲቪል ሰዎች የጥቃት ዒላማ እንዳይደረጉ ተገቢ የሆነ ጥንቃቄና ጥበቃ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ” አሳስበዋል።
ቅዳሜ ዕለት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ ቀደም ብሎ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንቅስቃሴን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚገልጸውና ሕዝብ ግንኙነት ሥራን የሚያከናውነው ኦዳ ተርቢ በትዊተር ገፁ ላይ ታጣቂዎቹ በደምቢዶሎ እና በጊምቢ ወታደራዊ ዘመቻ እያደረጉ መሆናቸውን አስፍሮ ነበር።
በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ሲንቀሳቀስና ጥቃት ሲፈጽም የቆየው አማጺው፣ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ግድም የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ከሚባል ቡድን ጋር በመሆን በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ እንደነበር የጋምቤላ ባለሥልጣናትና ቡድኑ አስታውቀው ነበር።
በጋምቤላ ከተማ ላይ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ የታጣቂው ቡድን አባላት መገደላቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት የገለጹ ሲሆን፣ አማጺው ግን ያቀደውን ወታደራዊ እርምጃ በስኬት ፈጽሞ መውጣቱን ገልጾ ነበር።
የታጣቂው ቡድን ጥቃት
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተለይ በምዕራብና በደቡብ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ የሚነገር ሲሆን፣ በነዋሪዎች፣ በመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሠራተኞች እንዲሁም በመንግሥታዊና በግል ተቋማት ላይ መፈጸሙ ሲዘገብ ነበር።
ታጣቂ ቡድኑ ከቀናት በፊት ጥቃት የፈጸመበት የምዕራብ ወለጋ ዞንን ጨምሮ በምሥራቅ ወለጋ እና በምዕራብ ሸዋ ውስጥ ሲንቀሳቀስና ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።
በተለያዩ ጊዜያት በቡድኑ ተፈጸሙ በተባሉ ጥቃቶች በተቋማት ላይ ከሚደርሱ ጉዳቶች ባሻገር በርካታ በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውና ለጉዳት መዳረጋቸው ሲነገር ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ቡድኖች ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ አዎንታዊ ምላሽ ከሰጡት ኃይሎች መካከል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አንዱ እንደነበር ይታወሳል።
ይህ መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንድ አካል የነበረ እና በወቅቱ ትጥቅ መፍታትን በመቃወም ከኦነግ ተለይቶ የወጣ ቡድን ሲሆን፣ ታጣቂው በተደጋጋሚ ከፈጸማቸው ጥቃቶች በኋላ በአገሪቱ ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ ተፈርጇል።












