በቻይና የሚደገፈው የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የደኅንነት ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን የሚያደርግና የአካባቢውን አገራት የሚያሳትፍ በቻይና የሚደገፍ ስብሰባ ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይጀመራል።
ይህ በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነ ስብሰባ የተሰናዳው በቻይና መንግሥት ድጋፍ እንደሆነ ተነግሯል።
ስብሰባው በቻይና መንግሥት ድጋፍ መደረጉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቻይና በአካባቢው ሁነኛ ተጽዕኖ እንዲኖራት መፈለጓ እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ቻይና የአካባቢው ድኅንነት ሁኔታ ያሳሰባትም በእነዚህ አገራት ከፍ ያለ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰሷ ነው የሚሉ አልጠፉም።
በዚህ የሁለት ቀናት ኮንፈረንስ ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት የሚወከሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
እነዚህ ብዙዎቹ አገራት በአህጉሪቱ ከፍተኛ የሚባል የቻይናን የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው።
የኮንፈረንሱ አሰናጅ ኢትዮጵያም ከቻይና መንግሥት ከፍተኛ የሚባል የገንዘብ ድጋፍ እና መዋዕለ ነዋይ የምታገኝ አገር ናት።
ይሁንና ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣው አለመረጋጋትና የእርስ በእርስ ጦርነት ቻይናን ሊያሳስብ የሚችል እንደሚሆን ተገምቷል።
በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መባቻ በኬንያ ጉብኝት ላይ የነበሩት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ለሰላም በሚደረገው ጥረት አገራቸው “ትልቅ ሚና” መጫወት እንደምትፈልግ ተናግረው ነበር።
ይህን ካሉ በኋላ ብዙም ሳይሰነብት ቤይጂንግ ባልተለመደ ሁኔታ ለአካባቢው ልዩ መልዕክተኛ መሰየሟ አይዘነጋም።
ምንም እንኳ ዛሬ የሚጀመረውን ኮንፈረንስ በቻይና ድጋፍ የሆነ ቢሆንም በኢትዮጵያ ተዋጊ ወገኖችን ለማደራደር ቻይና ያሳየችው ይፋዊ ፍላጎት የለም ።
ኮንፈረንሱ ቻይና በአካባቢው ያላትን የኢንቨስትመንትና የውጭ ፖሊሲ ፍላጎቶች እየጨመረ ስለመምጣቱ እንደ አንድ ማሳያ የወሰዱት አልጠፉም።
ቻይና ለአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሾመችው ባለፈው የካቲት ወር ነበር።
አንጋፋ ዲፕሎማት ናቸው የሚባሉት ዡ ቢንግ ለዚህ ሹመት ከመታጨታቸው በፊት በፓፓዎ ኒው ጊኒ አምባሳደር ሆነው ማገልገላቸው ተጠቅሷል።
ያም ብቻ ሳይሆን ግለሰቡ አገራቸውን ወክለው በአፍሪካ፣ በአሜሪካና በኦሽኒያ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የሠሩ ናቸው።
ቤይጂንግ በምሥራቅ አፍሪካ ሰፊ የሆነ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ያሏት ሲሆን
በጂቡቲ ያቋቋመችው ግዙፍ የባሕር ኃይል ሰፈርም የሚጠቀስ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጠናው ለሚገኙ አገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ከመስጠቷ በተጨማሪ በአገራቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ታከናውናለች።
በኢትዮጵያ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ አስተማማኝ መረጋጋት ሊሰፍን አለመቻሉ እንዲሁም አሁንም እልባት ያላገኘው የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ለቀጠናው ደኅንነት ፈተና የሆኑ ጉዳዮች ናቸው።
ከቻይና በተጨማሪ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ አገራት ጉዳይን በቅርበት የሚከታተሉ ልዩ መልዕክተኞች እንዳሏቸው ይታወቃል።












