በአዲሱ ዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ እሽቅድድም ዘመን ሠራዊቷን እያዘመነች ያለችው ቻይና

ቻይና በብርሃን ፍጥነት የጦር ኃይሏን እየገነባች ነው።
አገሪቱ በሚሳኤል ቴክኖሎጂ፣ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዕድገቷ በዓለም አቀፍ ወታደራዊ የኃይል ሚዛን ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣች ነው። ይህ ደግሞ በብዙ ምዕራባውያን ታዛቢዎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እአአ በ2035 የቻይና ጦር አሁን ካለበት የበለጠ እንዲዘምን ትዕዛዝ ሰጥተዋል። በ2049 "ጦርነትን መዋጋት እና ማሸነፍ የሚችል ዓለም አቀፍ" ወታደራዊ ኃይል መሆን አለበትም ብለዋል።
ትልቅ የቤት ሥራ ቢሆንም አገሪቱ ግን አላማዋን እያሳካች ነው።
ግዙፍ ወጪ
ቻይና ለመከላከያ የምታወጣውን ወጪ በተመለከተ "ግልጽነት የጎደለው" እና "ወጥ ያልሆነ መረጃ" ነው በመባል በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ትወቀሳለች።
ቤይጂንግ ይፋዊ ወታደራዊ ወጪዎቿን መረጃ ይፋ ታደርጋለች፤ ነገር ግን ቻይና ለጦር ኃይሏ የምታውለውን ገንዘብ በተመለከተ ከምትሰጠው መረጃ በተቃራኒ ምዕራባውያን የሚሰጡት ግምት ብዙ ጊዜ ከፍ ያለ ነው።
ከአሜሪካ በስተቀር ቻይና ለጦር ኃይሏ ከየትኛውም የዓለም አገር የበለጠ ወጪ እንደምታወጣ በሰፊው ይታመናል።
መቀመጫውን በዋሽንግተን ያደረገው የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል እንደሚለው የቻይና ወታደራዊ በጀት ዕድገት ከአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገቷ ቢያንስ ለአስር ዓመታት ብልጫ አለው።
የኒውክሌር ጦር ክምችት መጨመር
ከወር በፊት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ባደረገው ትንበያ ቻይና በ2030 የኒውክሌር ክምችቷን በአራት እጥፍ ለማሳደግ ተዘጋጅታለች። በተጠቀሰው ጊዜ ቻይና "ቢያንስ 1ሺህ የኒውክሌር ተወንጫፊ" እንዲኖራት አስባ እየሠራች ነው ብሏል።
የቻይና መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን ግምቱን "የማይመስል እና በቅዥት የተሞላ መላምት" በማለት የኒውክሌር መሣሪያዎች "በዝቅተኛ መጠን" እንዲኖራት ማድረጓን አክሎ ገልጿል።
በዓለም ቀፍ ደረጃ ያለውን የኒውክሌር ክምችት የሚያጠናውና በስቶክሆልም የሚገኘው ዓለም አቀፉ የሠላም ምርምር ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጦር መሣሪያዎቿን ቁጥር እየጨመረች መሆኗን ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ካላት 5,550 ኒውክሌር ጋር ለመድረስ ቻይና ብዙ ርቀት ይቀራታል። ሆኖም የኒውክሌር አረሩ መጨመር ለምዕራቡ ዓለም ወታደራዊ የበላይነት ትልቅ ስጋት ሆኖ ብቅ ብሏል።
በለንደን የሚገኘው የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ቬርል ኑዌንስ እንደሚሉት "የቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ዋነኛው ጉዳይ ነው።"
"በሁለቱም ወገኖች በኩል ትልቅ እምነት የማጣት ዝንባሌ አለ። ውይይት በሚያስፈልገው ደረጃ ላይ አልደረሰም። ትልቅ አደጋዎች ተደቅነዋል። አቅጣጫውን ለማየት አስቸጋሪ ነው" ብሏል።
የሃይፐርሶኒክ ዘመን
ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ከድምፅ ፍጥነት ከአምስት እጥፍ በላይ ይጓዛሉ።
እንደ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ግን ፈጣን አይደሉም። በጥቃት ወቅት ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ስለሆኑ አንዳንድ የአየር መከላከያዎችን ጥቅም አልባ ሊያደርጓቸው ይችላሉ።
የለንደኑ የኪንግስ ኮሌጅ ባልደረባ ዶ/ር ዘኖ ሊኦኒ እንደሚሉት ከሆነ "ቻይናውያን በጣም ረዥም ርቀት ወደ ኋላ እንደቀሩ ስለሚረዱ ከሌሎች ኃያላን ጋር ለመቀራረብ ትልቅ እርምጃ ለመውሰድ እየሞከሩ ነው።"
ይህን ለማድረግ ከሚሞክሩበት አንዱ መንገድ ደግሞ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን ማሳደግ እንደሆነ ገልጿል።
ቻይና ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን መሞከሯን ታስተባብላለች። ባለፈው ክረምት ያስወነጨፈቻቸው ሁለት ሮኬቶች ጦሯ እነዚህን ሚሳኤሎች ለማግኘት መቃረቡን ያሳያሉ ሲሉ የምዕራባውያን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ቻይና ምን ዓይነት የሚሳኤል ሥርዓቶችን እየገነባች እንደሆነ በትክክል ግልጽ ባይሆንም ሁለት ዋና ዋና ሥርዓቶች አሉ። እነዚህም
- የሃይፐርሶኒክ ተንሳፋፊ ሚሳኤሎች አንዱ ሲሆን በምድር ከባቢ አየር ውስጥ ይቆያሉ።
- ፍራክሺናል ኦርቢታል ቦምባርድመንት ሲስተም (ኤፍኦቢኤስ) የሚባለው ደግሞ ወደ ኢላማ ከማቅናቱ በፊት በዝቅተኛ ምህዋር ይጓዛል።
ቻይና ሁለቱን የሚሳኤል ሥርዓቶች በማጣመር ከተሳካላት ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን ከኤፍኦቢኤስ ሊንቀሳቀስ ከሚችለው የጠፈር መንኮራኩር ለመተኮስ ይቻላታል።
እንደ ዶ/ር ሊዮኒ ከሆነ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች በራሳቸው ማርሽ ቀያሪ ባይሆኑም አንዳንድ ዒላማዎችን በጣም ተጋላጭ ያደርጋሉ ብለዋል።
"ሃይፐርሲኒክ ሚሳኤሎች በተለይም የአውሮፕላን ተሸካሚዎችን ለመከላከል በጣም አስቸጋሪ ያደርጋሉ" ሲሉም ተናግረዋል።
"ስጋቱ እውነት ነው፤ ነገር ግን ይህ የተጋነነም ሊሆን ይችላል" ሲሉም ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርተፊሻል ኢንተለጀንስ እና የሳይበር ጥቃቶች
ቻይና አሁን ሙሉ በሙሉ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመሩ የጦር መሣሪያዎችን ለማምረት ቁርጠኛ ሆናለች። ይህንን ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር የገለጸው ጉዳይ ነው።
የቻይና ወታደራዊ ሳይንስ አካዳሚ ይህ "በሲቪል-ወታደራዊ ውህደት" በኩል የማረጋገጥ ሥልጣን ተሰጥቶታል። በሌላ አነጋገር የቻይናን የግል ዘርፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ከአገሪቱ የመከላከያ ኢንዱስትሪዎች ጋር ማቀናጀት ማለት ነው።
ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ቻይና ቀደም ሲል ጀምሮ በወታደራዊ ሮቦቲክስ እና በሚሳኤል ሥርዓቶቿ፣ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በሰው አልባ የባሕር ኃይል መርከቦቿ ውስጥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን እየተጠቀመች ሊሆን ይችላል።
በቅርቡ በተደረገ የባለሙያዎች ግምገማ መሠረት ቻይና ቀደም ሲል መጠነ ሰፊ የሳይበር ዘመቻ ሥራዎችን በውጭ አገራት አከናውናለች።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ቻይና የማይክሮሶፍት የመረጃ ቋቶች ላይ ያነጣጠረ ዋና የሳይበር ጥቃት ፈጽማለች ሲሉ ከሰዋል።
ጥቃቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢያንስ 30,000 ድርጅቶችን እንደጎዳ ይታመናል። ዓላማውም የግል መረጃን እና የአዕምሯዊ ንብረትን ጨምሮ መጠነ ሰፊ የስለላ ሥራዎችን ለመሥራት ያለመ ነው ተብሎም ይታመናል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የዓለማችን ትልቁ ግን ኃያል ያልሆነው የባሕር ኃይል
ቻይና በዓለም ላይ ትልቁ የባሕር ኃይል ባለቤትነትን ከአሜሪካ ነጥቃለች። የመርከብ ቁጥሮችን በማነጻጸር የባሕር ኃይልን አቅምን መገምገም ሌሎች የማነጻጸሪያ መስፈርቶችን እንደሚያስቀር ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በአጠቃላይ ያሉትን አዝማሚያዎችን መመርመር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ሲሉም ያክላሉ።
ለጊዜው አሜሪካ በብዙ መመዘኛዎች ጠንካራ የባሕር ኃይል አቅም በመያዝ መሪነቷን አስጠብቃለች። አሜሪካ 11 አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ሲኖራት ቻይና ሁለቱ አላት። በኒውክሌር ተሸካሚ የባሕር ሰርጓጅ መርከቦች፣ ክሩዘር እና ትላልቅ የጦር መርከቦችም ቀዳሚ ናት።
ቻይና የባሕር ኃይሏን የበለጠ እንደምታስፋፋ ግን ይጠበቃል።
የቻይና ሕዝባዊ ነጻ አውጪ ሠራዊት የቀድሞ ኮሎኔል እና በቤይጂንግ የሚገኘው የሲንጉዋ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዡ ቦ ቻይና ያጋጠማትን ባሕር ላይ ያነጣጠሩ ስጋቶችን ለመከላከል የባሕር ኃይሏን ማጠናከር "በጣም አስፈላጊው ነው" ብለው ያምናሉ።
"እኛ የሚያጋጥመን ዋነኛው ችግር አሜሪካውያን በቻይና ውሃ ክልል ላይ የሚቀሰቅሱት ጠብ ጫሪነት ነው" ይላሉ።
የአሜሪካ የባሕር ኃይል ባስቀመጠው ትንበያ መሠረት እአአ ከ2020 እስከ 2040 ባለው ጊዜ ውስጥ የቻይና የባሕር ኃይል መርከቦች ቁጥር በ40 በመቶ ጨምሯል።
የማይታወቀው ነገ
ቻይና ከግጭት ከመራቅ ወጥታ ወደ አጥቂነት እየተሸጋገረች ነው?
አሁንም የቻይናውያን አካሄድ "ያለ ውጊያ ማሸነፍ ነው" ብለዋል ዶ/ር ሊዮኒ። ለወደፊቱ ግን ይህን ስትራቴጂ ሊለውጠው ይችላል ሲሉ አክለዋል።
"ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ ሆነ የባሕር ኃይል መያዝ አንድ ጠቃሚ ነጥብ ሊሆን ይችላል።"
ኮሎኔል ዡዩ ግን የምዕራባውያን ፍርሃት መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ አጥብቀው ይከራከራሉ።
"ከዩናይትድ ስቴትስ በተለየ መልኩ ቻይና ዓለምን የመቆጣጠር ሐሳብ የላትም። ቻይና አንድ ቀን የዓለማችን ጠንካራ አገር ብትሆን እንኳን መሠረታዊ ፖሊሲዋን ጠብቃ ትዘልቃለች" ብለዋል።
እአአ 1979 ከቬትናም ጋር ከገጠመችበት ጦርነት ወዲህ ቻይና ወደ ግጭት አምርታ አታውቅም። ወታደራዊ አቅሟ በአብዛኛው ያልተፈተነ ነው።
በምዕራቡ ዓለምም ሆነ በቻይና የሚገኙ ብዙ ሰዎች በዚሁ እንደምትቀጥል ተስፋ ያደርጋሉ።












