ቴክኖሎጂ የጦር ሜዳ አሰላለፍን ይቀይራል? ቀጣይ ውጊያዎችስ ምን ሊመስሉ ይችላሉ?

ሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ተምዘግዛጊ ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, GIANCARLO CASEM/US AIR FORCE

ጦርነት የሚካሄድበት መንገድ ከዘመን ዘመን እየተቀየረ ነው። ባለንበት ጊዜ ለውጊያ የሚውሉ መሣሪያዎች ቴክኖሎጂን ያማከሉ ሆነዋል።

ለምሳሌ አምና ዩናይትድ ኪንግደም በመከላከያ እና ደኅንነት መዋቅሯ ላይ ባደረችው ለውጥ ለሰው ሠራሽ ልህቀት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ክፍል ከፍተኛ ገንዘብ መድባለች።

በተቃራኒው ለወታደሮች እንዲሁም ዘመን ላለፈባቸው መሣሪያዎች የሚመደበው በጀት ተቀንሷል።

ወታደራዊ ፍጥጫዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ስጋት ሆነዋል።

የሩሲያ እና የዩክሬን ውጥረት ተጠቃሽ ነው። ሩስያ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ከአንዳንድ አባላቱ ግዛት እንዲወጣ አስጠንቅቃለች።

ቻይና ካስፈለገ ኃይል ተጠቅማ ታይዋንን የግዛቷ አካል እንደምታደርግ እየዛተች ነው።

ኢትዮጵያም ከዓመት በላይ ጦርነት ውስጥ ናት።

በሶሪያ የታጣቂዎች ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ኢስላሚክ ስቴት ሽብር መፍጠሩን ቀጥሎበታል።

ዓለም እንዲህ በግጭቶች በተወጠረችበት ወቅት፤ ባለንበት ዘመን ጦርነት ምን ቅርጽ ሊይዝ ይችላል? የሚለው ጥያቄ ይነሳል።

በተለይም ኃያላን አገራት እጃቸው ያለበት ጦርነት ምን መልክ ይኖረው ይሆን?

ቻይና እና ሩሲያ እንዲሁም የምዕራቡ ዓለም አገራትም ጦርነትን ካዘመኑ ሰነባብተዋል።

ሩሲያ ያሳለፍነው ጥቅምት ወደ ህዋ ሚሳኤል አስወንጭፋ የራሷን ሳተላይት መታለች።

ቻይና እጅግ ዘመናዊና ከድምጽ ጋር በሚቀራረብ ፍጥነት የሚምዘገዘግ የሚሳኤል ሙከራ እያደረገች ነው።

በበይነ መረብ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። እንዲያውም የሳይበር ስርሰራ ራሱን የቻለ ውጊያ ሆኗል ማለት ይቀላል።

የቻይናው ዶንግ ፈንግ 17 ሚሳኤል ቤጂንግ ውስጥ ለእይታ ቀርቦ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይናው ዶንግ ፈንግ 17 ሚሳኤል ቤጂንግ ውስጥ ለእይታ ቀርቦ

በክሊንተን እና በኦባማ አስተዳደር ወቅት የአሜሪካ የፔንታገን የፖሊሲ ኃላፊ የነበሩት ሚሼል ፍላርኖይ እንደሚሉት፤ የምዕራቡ ዓለም ባለፉት ሁለት አሥርታት መካከለኛው ምሥራቅ ላይ ትኩረታቸውን አድርገዋል።

የምዕራቡ ዓለም ተቀናቃኝ አገራት ግን ዘመነኛ መሣሪያዎች ማምረትም ጀምረዋል።

"አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎችም አጋር አገሮች ለ20 ዓመታት በፀረ ሽብር እንዲሁም በኢራቅና አፍጋኒስታን ላይ ነበር ትኩረታችን። አሁን ግን ኃይላችንን የሚገዳደሩ አገራት ገጥመውናል" ብለዋል።

እነዚህ የምዕራባውያንን ኃይል የሚገዳደሩ አገራት ቻይና ሩሲያ ናቸው።

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት "ከባድ ስጋቶች" እና "የምዕራቡ ዓለም ተቀናቃኞች" ሲል ይገልጻቸዋል።

አሜሪካ፣ ዩኬና ሌሎችም አገራት መካከለኛው ምሥራቅን በቅርብ ርቀት ሲከታተሉ ሩሲያ እና ቻይና ዘመነኛ የጦር መሣሪያ ማከማቸት ያዙ።

ዋነኛ ትኩረታቸው የምዕራቡን ዓለም የሚያናጋ የበይነ መረብ ጥቃትና የመረጃ ዘረፋ ነው።

በምዕራቡ ዓለም ምርጫ ጣልቃ እስከመግባትም ደርሰዋል።

በሩሲያ እና ዩክሬን ፍጥጫ ሳቢያ ሩሲያ ከምዕራቡ ዓለም ብትገጥም ወይም በቻይና እና ታይዋን ውጥረት ሳቢያ ቻይና ከአሜሪካ ጋር ብትዋጋ ጦርነቶቹ ምን ሊመስሉ ይችላሉ?

በዓለም አቀፉ የስትራቴጂ ጥናት ተቋም ስለ ቻይና መረጃ-ተኮር ወታደራዊ አካሄድ የሚመራመሩት ማያ ኑዌንስ እንደሚሉት፤ እነዚህ ጦርነቶች ቢነሱ ዋነኛ ዘዋሪ የሚሆነው የመረጃ ውጊያ ነው።

ቻይና በህዋ እና በበይነ መረብ ላይ ያተኮረ አዲስ ተቋም መሥርታለች።

ታዲያ ቻይና ከምዕራቡ ዓለም ጋር ጦርነት ብትገጥም የመጀመሪያው እርምጃዋ የበይነ መረብ ጥቃት ይሆናል።

ሳተላይትን ጨምሮ ሌሎችም የግንኙነት መስመሮችን በመቁረጥ ጦርነቱ ይፋፋማል።

የአሜሪካ አየር ኃይል ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, GIANCARLO CASEM/US AIR FORCE

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ አየር ኃይል ሚሳኤል

ለወደፊት የሚነሱ ጦርነቶችን የሚያጠኑት ፍራንዝ-ስቴፈን ጌዱ እንደሚሉት፤ የመረጃ ጦርነት ሲነሳ የእያንዳንዳችን ስልክ የሚቋረጥበት፣ ነዳጅ ማደያ ባዶ የሚሆንበት፣ የምግብ እጥረት የሚከሰትበት ዕድል ሰፊ ነው።

"ለወደፊት የሚነሱ ጦርነቶች የሚያነጣጥሩት በወታደሮች ብቻ ሳይሆን ዜጎች ላይ ጭምርም ነው" ይላሉ።

የሳተላይት ግንኙነት ተጠልፎ ቆመ ማለት አንድ አገር መረጃ መለዋወጥ አትችልም ማለት ነው።

ይህም ምን እየተከናወነ እንደሆነ፣ በቀጣይ ምን እንደሚመጣም ለማወቅ ከባድ ያደርገዋል።

ማያ ኑዌንስ እንደሚሉት፤ የመረጃ ጥቃት የደረሰበት አገር መልሶ ሲያጠቃ፤ ከተቃጣበት ጥቃት የበለጠ ወይም ያነሰም ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

የመረጃ ጦርነትን ለመጨበጥ አስቸጋሪ ስለሚሆን ውጊያው እየተባባሰም ሊሄድ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል።

ሰው ሠራሽ ልህቀት ለወደፊት የሚነሱ ጦርነቶችን በእጅጉ ይቀይራል ተብሎ ይታመናል።

መረጃ በፍጥነት ለመለዋወጥ እንዲሁም በአስቸኳይ እርምጃ ለመውሰድም ይረዳል።

አሜሪካ በዚህ ረገድ ከተቀረው ዓለም የተሻለ ርቀት ተጉዛለች።

የተቀረው የምዕራቡ ዓለም ግን በቻይና እየተፈተነ ነው።

"ሰዎችና ማሽኖችን በማጣመር ከባድ ጥቃት መሰንዘር ይቻላል" ይላሉ ሚሼል ፍላርኖይ።

አንድ ሰው 100 ማሽኖችን እንዲቆጣጠር ሲመደብ በሰው ኃይል እና በስምሪት የበላይነት ይረጋገጣል።

ቻይና እና ሩሲያ የምዕራቡን ዓለም በሀይፐርሶኒክ ሚሳኤል ይበልጣሉ።

እነዚህ ሚሳኤሎች ከድምጽ ከ5 እስከ 27 እጥፍ ይፈጥናሉ። ኒውክሌር ተሸካሚም ናቸው።

ሩሲያ ዚክሮን የተባለውን ሀይፐርሶኒክ ሚሳኤሏን በተሳካ ሁኔታ ሞክራለች። በየትኛው የዓለም ክፍል ጥቃት መሰንዘር የሚችል መሣሪያ መሆኑንም አስታውቃለች።

የቻይና ዶንግ ፌንግ 17 እአአ በ2019 ነበር ይፋ የተደረገው። በከባቢ አየር ውስጥ ያለ ምንም መሰናክል ተምዘግዝጎ ይጓዛል።

ይህንን መሣሪያ ለመጥለፍም አስቸጋሪ ነው።

አሜሪካ በዚህ ረገድ ያደረገቻቸው ሙከራዎች እምብዛም ስኬታማ አልሆኑም።

ቻይና ያሏትን መሣሪያዎች ከግምት በማስገባት አሜሪካ ወደ ውጊያ መግባትን ላትፈልግ ትችላለች።

ቻይና ታይዋንን ብትወር እንኳን አሜሪካ ምን ድረስ ጣልቃ ትገባለች? የሚለው የሚወሰነው ቻይና ባሏት መሣሪያዎች ልክ ነው።

ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ላይ የምታደርገው እንቅስቃሴ ዓለምን አስግቷል።

ከተለመው የጥይት ጦርነት ባሻገር የበይነ መረብ ጥቃትም ሊሰነዘር ይችላል።

ምናልባት ከታንክ እና ከእግረኛ ጦር ባልተናነሰ ሁኔታ ውጊያው የመረጃ ሊሆንም ይችላል።

ሳተላይት ጫኝ የስፔስ ኤክስ ሮኬት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሳተላይት ጫኝ የስፔስ ኤክስ ሮኬት

ፍራንዝ-ስቴፈን ጌዱ እንደሚሉት፤ ዩኬ ከመከላከያ በጀቷ ለመረጃ ደኅንነት ከፍተኛውን ድርሻ መስጠቷ በቀጣይ 20 ዓመታት ውስጥ አዋጭ ውሳኔ ነው።

"ቀጣዩቹ 5 እና 10 ዓመታት ፈታኝ ነው የሚሆኑት። ገና በጅምር ላይ ባሉ ቴክኖሎጂ-መር የጦር መሣሪያዎች ላይ መተማመን አይቻልም" በማለት የወደፊቱን ስጋት ያስረዳሉ።

የምዕራቡ ዓለም አገራት እርስ በእርስ ከተባበሩ ስጋታቸውን መመከት እንደሚችሉ የአሜሪካ የፔንታገን የፖሊሲ ኃላፊ የነበሩት ሚሼል ፍላርኖይ ይናገራሉ።

"በትክክለኛው ቴክኖሎጂ ላይ ገንዘባችንን ካፈሰስንና ከተረዳዳን የጦርነት ስጋቶችን እንቀርፋለን። የሕንድ ውቅያኖስ ዙርያን ነጻ አድርገን በጋራ መበልጸግ እንችላለን" ይላሉ።