ቻይና የኒውክሌር አቅም ያለው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል አልሞከርኩም አለች

ቻይና በወታደራዊ ትዕይነት ላይ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን አሳይታለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቻይና በወታደራዊ ትዕይነት ላይ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን አሳይታለች

ቻይና በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የኒውክሌር አቅም ያለው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሞክራለች የሚለውን ዘገባ ውድቅ አድርጋ የተለመደው የጠፈር መንኮራኩር ፍተሻ ነው ስትል ገልጻለች።

በፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ላይ የቀረበው ዘገባ በዋሽንግተን ስጋት ከመፍጠር ባለፈ የአሜሪካ የስለላ ተቋምንም አስገርሞ ነበር ተብሏል።

የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ከተለመዱት ሚሳኤሎች በጣም ፈጣን እና ቀልጣፋ በመሆናቸው ለመከላከል ከባደ ያደርጋቸዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን ሰኞ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ የተለያዩ ዓይነት በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ የጠፈር መንኮራኩር ቴክኖሎጂ ላይ በሐምሌ ወር መደበኛ ሙከራ ተደርጓል።

"ሚሳኤል አልነበረም። የጠፈር መንኮራኩር ነበር። ይህ የጠፈር መንኮራኩር አጠቃቀም ዋጋን ለመቀነስ ትልቅ ትርጉም አለው" ብለዋል።

ዣኦ አክለውም በርካታ አገራት ተመሳሳይ ሙከራዎችን ከዚህ በፊት አከናውነዋል። የፋይናንሻል ታይምስ ዘገባ ስህተት ስለመሆኑ ተጠይቀውም "አዎ" ሲሉ መልሰዋል።

ፋይናንሻል ታይመስ ቅዳሜ በወጣው ሪፖርቱ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል መሞከሩን ስማቸው ያልተጠቀሰ አምስት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። ወደ ታች ከመውረዱ በፊት በዝቅተኛ ምህዋር ላይ ማለፉን እና ዒላማውን ለጥቂት አጥቷል ይላል ዘገባው።

"ሙከራው ቻይና በሃይፐርሶኒክ መሣሪያዎች ላይ አስደናቂ ዕድገት እንዳደረገች እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ካሰቡት እጅግ የላቀ እንደሆነ" ሪፖርቱ ያሳያል።

የአሜሪካ የትጥቅ ማስፈታት አምባሳደር ሮበርት ዉድ አሜሪካ "ስለጉዳዩ በትኩረት አድንደምታስብ" እና ዋሽንግተን ለዚህ ቴክኖሎጂ ወታደራዊ ጥያቄዎችን ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳለች ተናግረዋል።

ሆኖም ቻይና እና ሩሲያ ወታደራዊ መጠቀሚያዎችን "በጣም በንቃት" ሲያካሂዱ ነበር። ይህ ማለት አሜሪካ "በአይነት ምላሽ መስጠት አለባት" ማለት ነው።

የሪፐብሊካኑ የምክር ቤት የጦር መሣሪያ አገልግሎት ኮሚቴ አባል የሆኑት ማይክ ጋላገር ቀደም ሲል ዋሽንግተን አሁን ባለው አካሄዷ ከቀጠለች በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ከቻይና ጋር አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ ገብታ ትሸነፋለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት በውጥረት የተሞላ ሆኗል። ቤጂንግ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ጠላት ነው ስትል ትከሳለች።

ቻይና በቅርቡ ያሳየችው ወታደራዊ ኃይል እንዳሳሰባቸው በርካታ የምዕራባውያን አገራትም ገልጸዋል።

በአውስትራሊያ ስትራቴጂክ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የመከላከያ፣ ስትራቴጂ እና የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር የሆኑት ሚካኤል ሾብሪጅ በበኩላቸው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ከተሞከረ "የኒውክሌር እና የሌሎች የጥቃት መሣሪያዎች ፉክክር ዘይቤ" ይገጥማል ብለዋል።

ቻይና በቅርቡ ባደረገችው ወታደራዊ ትዕይንት ላይ "ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል" የሚመሰል መሣሪያ አሳይታለች።

ከቻይና በተጨማሪ አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቢያንስ አምስት ሌሎች አገራት በሃይፐርሶኒክ የሚሳኤል ቴክኖሎጂ ላይ እየሠሩ ናቸው።

ሚሳኤሎቹ ከድምፅ ፍጥነት ከአምስት እጥፍ በላይ መፍጠን የሚችሉ ሲሆን ልክ እንደ ባልስቲክ ሚሳኤሎች ኒውክሌር አረር መሸከም ይችላሉ።

ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ወር አዲስ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን በተሳካ ሁኔታ መሞከሯን ገልጻለች።