የሩሲያ ፀረ-ሳተላይት ሚሳኤል ሙከራ ከየአቅጣጫው ውግዘት እያስተናገደ ነው

ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩሲያ "አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው" የሚሳኤል ሙከራ በማድረግ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ (አይኤስኤስ) የሚገኙ ሠራተኞችን አደጋ ላይ ጥላለች ስትል አሜሪካ አወገዘች።

ሙከራው ከሩሲያውያን ሳተላይቶች መካከል አንዱን ያፈነዳ ሲሆን በተፈጠረው ስብርባሪ ምክንያትም የጣቢያው ሠራተኞችን መጠለያ እንዲፈልጉ ያስገደዳቸው ነበር ተብሏል።

ጣቢያው በአሁኑ ጊዜ ሰባት አባላት አሉት። አራቱ አሜሪካውያን ሲሆኑ ሁለት ሩሲያውያን እና አንድ ጀርመናዊ ናቸው።

የጠፈር ጣቢያው በ420 ኪሜ ከፍታ ላይ ይዞራል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እንደተናገሩት "የሩሲያ ፌዴሬሽን በግዴለሽነት በቀጥታ ወደ ላይ በሚወጣ ፀረ-ሳተላይት ሚሳኤል በራሱ ሳተላይት ላይ አጥፊ የሳተላይት ሙከራ አድርጓል" ብለዋል።

"ሙከራው እስካሁን ድረስ ከ1 ሺህ 500 የሚበልጡ ክትትል የሚደረግባቸው የምኅዋር ስብርባሪዎችን ፈጥሯል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ትናንሽ የምኅዋር ስብርባሪዎች የፈጠረም ሲሆን እነዚህም የሁሉንም አገራት ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው" ብለዋል።

የናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን በድርጊቱ መናደዳቸው ገልጸዋል።

"በሰው ልጅ የጠፈር በረራ ውስጥ ካላት ረዥም ታሪክ አንጻር ሩሲያ በጣቢያው ላይ የአሜሪካ እና ዓለም አቀፍ አጋር ጠፈርተኞችን ብቻ ሳይሆን የራሳቸው እና የቻይናን የጠፈር ጣቢያ አደጋ ላይ ይጥላሉ ብሎ ማሰብ የማይቻል ነው" ብለዋል በመግለጫቸው።

የሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ ሮስኮስሞስ ድርጊቱን በቀላሉ ገልጾታል።

ኤጀንሲው በትዊተር ገፁ ላይ "ዛሬ ሠራተኞቹ በመደበኛ አሠራር መሰረት ወደ ጠፈር መንኮራኩር እንዲገቡ ያስገደዳቸው ቁስ ከጣቢያው ምኅዋር ርቋል። ጣቢያው በአረንጓዴ ዞን ውስጥ ነው" ሲል አስፍሯል።

የጠፈር ስብርባሪዎችን የሚከታተለው እና ሊዮላብስ የተሰኘው ኩባንያ በኒውዚላንድ ያለው የራዳር ማዕከሉ ጊዜ ያለፈበት የጠፈር መንኮራኩር መኖር በነበረበት ቦታ በርካታ ዕቃዎችን እንዳገኘ ተናግሯል።

ኔድ ፕራይስ የሩሲያን ድርጊት "አደገኛ እና ኃላፊነት የጎደለው ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

"አሜሪካ ከአጋሮቿ ጋር በመተባበር ለሚያደርጉት ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ምላሽ ለመስጠት እንሠራለን" ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ በበኩላቸው ሙከራው "የጠፈር ደኅንነትን እና ዘላቂነትን ሙሉ በሙሉ ችላ መባሉን ያሳያል" ብለዋል።

"በዚህ ሙከራ ምክንያት የሚፈጠረው ስብርባሪ የሳተላይቶችን እና የሰዎችን የጠፈር ጉዞ አደጋ ላይ በመጣል ምኅዋር ውስጥ ለብዙ ዓመታት ይቆያል" ሲሉም አክለዋል።

አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ሕንድን ጨምሮ በርካታ አገራት ሳተላይቶችን ከመሬት ላይ የማምጠቅ አቅም አላቸው።

እንደዚህ አይነት ሚሳኤሎችን መሞከር ብዙም አልተለመደም። ይህ ድርጊት ለሁሉም አገራት ከባቢውን ስለሚበክል በተሞከረ ቁጥርም ሰፊ ውግዘትን ያስከትላል።

ቻይና በአውሮፓውያኑ 2007 አገልግሎቷን ከጨረሰች የአየር ሁኔታ መከታተያ ሳተላይቶች መካከል አንዷን ከጥቅም ውጪ ስታደርግ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስብርባሪዎች ተፈጥረዋል። ይህ ስብርባሪ ለቻይና ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ጭምር የህዋ ተልዕኮዎች ላይ ቀጣይነት ያለው አደጋ አስከትሏል።