አሜሪካ በጦር መሳሪያ ንግድ ቀዳሚነቷን ስታስጠብቅ ሽያጯም ከፍ ብሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት አምስት ዓመታት አሜሪካ ለሌሎች አገራት የምታቀርበው የጦር መሳሪያ መጠን በ37 በመቶ መጨመሩን አንድ በስዊዲን የሚገኝ የምርምር ተቋም አስታወቀ።
ከአሜሪካ በተጨማሪ ፈረንሳይና ጀርመን ለሌሎች አገራት በሽያጭ የሚያቀርቡት የጦር መሳሪያ መጠን መጨመር በሩሲያና በቻይና አቅርቦት ምክንያት የተፈጠረውን ክፈተት የሚሞላ ነው ተብሏል።
በአሁኑ ጊዜ የአገራት የጦር መሳሪያ ግዢና ሽያጭ መጠን ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ ከሚባለው ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፤ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሰበብ ለውጥ ሊኖር ይችላል ተብሎ ይገመታል።
በዓለም ላይ ከታየው የጦር መሳሪያ ግዢ ውስጥ ከፍተኛው የተመዘገበው በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ነው ተብሏል።
የጦር መሳሪያዎች ግዢና ሽያጭን በተመለከተ ምርምሩን የሰራው የስቶክሆልም የሠላም ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፒተር ዊዝማን "ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የታየው ፈጣን የጦር መሳሪያ ግብይት አብቅቷል ለማለት ጊዜው ገና ነው" ብለዋል።
ባለሙያው ጨምረውም የኮሮናቫይረስ የሚያስከትለው የምጣኔ ሀብት ተጽዕኖ አገራት በቀጣይ ዓመታት ውስጥ የሚገዙትን የጦር መሳሪያ መጠን መለስ ብለው እንዲቃኙ ሳያደርጋቸው አይቀርም።
"ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ባለፈው ዓመት እንኳን፣ በርካታ አገራት ወሳኝ የሚባሉ ጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት ከፍተኛ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።"
የጥናት ተቋሙ እንዳመለከተው ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ቀደም ሲል ከነበረው ዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ጋር ሲነጻጸር በነበረበት የመርጋት ሁኔታ አሳይቶ ነበር።
አሜሪካ ወደ ውጭ ከምትልከው የጦር መሳሪያ ወደ ግማሽ የሚጠጋው፣ ማለትም 47 በመቶው፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የቀረበ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥም ሳዑዲ አረቢያ ብቻዋን ከአጠቃላዩ የአሜሪካ የመሳሪያ ሽያጭ 24 በመቶውን ትወስዳለች።
ባለፉት አምስት ዓመታት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ድርሻ በጨመረበት ጊዜ 96 አገራት ደንበኞቿ ሆነዋል።
ከአሜሪካ በመከተል የፈረንሳይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ በ44 በመቶ ሲጨምር የጀርመን ደግሞ በ21 በመቶ ከፍ ብሏል።
ከእነዚህ በተጨማሪም እስራኤልና ደቡብ ኮሪያ ምንም እንኳን ከዋነኞቹ ጋር ሲነጻጸር የሚያቀርቡት የጦር መሳሪያ መጠን ዝቅተኛ ቢሆንም በዚህ ወቅት ሽያጫቸው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
ግጭትና ውጥረት በማይለየው መካከለኛው ምሥራቅ የጦር መሳሪያ ግዢ ፍላጎት በፍጥነት እያደገ ይገኛል። በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ወደዚህ አካባቢ የተሸጠው የጦር መሳሪያ መጠን ቀደም ሲል ከነበሩት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በ25 በመቶ ከፍ ብሏል።
ከፍተኛው የጦር መሳሪያ ግዢ የተከናወነውም በሳዑዲ አረቢያ ሲሆን በዚህም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከተላከው 61 በመቶውን ገዝታለች። በተከታይነት ግብጽና ኳታር ይጠቀሳሉ።
የእስያና የኢዢያ አገራት ቀደም ሲል 42 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ መጠን ያለውን ዋነኛ የጦር መሳሪያዎችን በመሸመት ቀዳሚ ነበሩ።
በአካባቢው ሕንድ፣ አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያና ፓኪስታን ዋነኞቹ የጦር መሳሪያ ሸማች አገራት ነበሩ።
ምንም እንኳን አሁንም ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት ዋነኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢዎች ቢሆኑም፤ ቀደም ሲል ከዋነኞቹ የጦር መሳሪያ ላኪዎች መካከል የነበሩት ሩሲያና ቻይና ሽያጫቸው ቀንሷል።
በዚህም ሳቢያ ሩሲያ ወደ ውጭ አገራት የምትልከው መሳሪያ በ22 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ ሕንድ የምትልከው 53 በመቶ የሚሆነው ነበር።
የዓለም ትልቋ አምስተኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢ የሆነችው ቻይና ሽያጯ በ7.8 በመቶ ቀንሷል።
ፓኪስታን፣ ባንግላዲሽና አልጄሪያ ዋነኞቹ የቻይና ጦር መሳሪያ ገዢዎች ነበሩ።












