ፊልም፡ አቫተር ከ12 ዓመት በኋላ ከፊልሞች ሁሉ የላቀ ገቢ አገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ገቢን ያስገኘው አቫተር ፣ ቻይና ውስጥ በድጋሚ እንዲታይ በመደረጉ ከየትኛውም ፊልም በላይ ከፍተኛ ገቢ ያስገኘ ፊልም በመሆን መሪነቱን ያዘ።
የሳንይንስ ልቦለድ ፊልም የሆነው አቫተር ከ10 ዓመት በፊት ለዕይታ የበቃ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት 'አቬንጀርስ፡ ኢንድጌም' የተባለው ሲኒማ ቦታውን እስኪረከበው ድረስ በዓለም አቀፉ የቦክስ ኦፊስ ሰንጠረዥ ላይ የመሪነቱን ቦታ ይዞ ለዓመታት ቆይቷል።
አቫተር የዓለማችን ከፍተኛ የሲኒማ ተመልካች ገበያ ባለባት ቻይና ውስጥ በድጋሚ እንዲታይ ከተደረገ በኋላ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሽያጩ ከ2.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ከተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ጋር ተያይዞ ቻይና በፊልሙ ዘርፍ ከፍተኛ ገበያ ያለባት አገር ሆናለች።
"እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሳችን ኩራት ይሰማናል። ነገር ግን እኔና ጄምስ ካሜሩን የበለጠ የተደሰትነው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አቫተር በድጋሚ በሲኒማ ቤቶች ለዕይታ በመብቃቱ ነው። ለዚህም ቻይናውያን አድናቂዎቻቸንን ማመስገን እንፈልጋለን" ሲል የፊልሙ ፕሮዲዩሰር ጆን ላንዱ ተናግሯል።
በቻይና በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ ሲኒማ ቤቶች ተከፍተው ሥራ ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል። በዚህ ጊዜ የአገር ውስጥ ፊልሞችም ከፍተኛ ሽያጭን ማስመዝገብ ችለዋል።
'አቫተር' ቻይና ውስጥ በድጋሚ እንዲታይ ከመደረጉ በፊት አሜሪካ ውስጥ 760 ሚሊዮን ዶላር ሲያስገኝ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ አስገኝቶ ነበር።
ዋልት ዲዝኒ ባወጣው መረጃ መሰረት በጄምስ ካሜሩን ዳይሬክት የተደረገው አቫተር ባለፈው ቅዳሜ ብቻ 4 ሚሊዮን ዶላሮችን በማስገባት 'ኢንድጌም' ከተሰኘው ፊልም ቀዳሚ ለመሆን ችሏል።
የአቫተርና ኢንድጌም ፊልሞች ባለቤት የሆነው ዲዝኒ ከፍተኛ ገቢን በማስገኘት በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የታይታኒክ ፊልም ባለቤት ነው።
ጄምስ ካሜሩን በአሁኑ ጊዜ የአቫተር ተከታይ የሆነውን ፊልም በመስራት ላይ ሲሆን፤ በተከታታይ የሚወጣበት ጊዜ እንዲዘገይ ሲደረግ የነበረው ቀጣይ ፊልሙ ከዓመት በኋላ ወደ ሕዝብ ይደርሳል ተብሏል።












