ቢዮንሴ እና ቴይለር ስዊፍት በ2021 የግራሚ ሽልማት ታሪክ ሰሩ

ቴይለር ስዊፍትና ቢዮንሴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቢዮንሴ ለ28ኛ ጊዜ የግራሚ ሽልማትን በማግኘት እንዲሁም ቴይለር ስዊፍት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የዓመቱ ምርጥ አልበም ሽልማትን በመውሰድ ታሪክ አስመዘገቡ።

በአሁኑ ጊዜ ቢዮንሴ በግራሚ ሽልማት ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሽልማት ያሸነፈች ሴት ድምጻዊት በመሆን ቀዳሚነቱን ይዛለች።

ከዚህ ቀደም ይህንን ክብረወሰን ጨብጣ የነበረችው አሊሰን ክራውስ ነበረች።

63ኛው የግራሚ ሽልማት በሎስ አንጀለስ የተካሄደ ሲሆን በተለምዶ "የሙዚቃ ትልቁ ምሽት" በመባል ይታወቃል።

በዚህ ዓመት በኮሮናቫይረስ ወርሽኝ የተነሳ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የሽልማት ሥነ ሥርዓቶች በተለየ ምንም ዓይነት እንግዳ ሳይገኝ ዝግጅቱ ተካሂዷል።

ቢዮንሴ በምርጥ የአር ኤንድ ቢ ሙዚቃ አቀራረብ ተመርጣ ሽልማቱን ስትቀበል "ታላቅ ክብርና ደስታ ይሰማኛል" ብላለች።

ቴይለር ስዊፍትም እንዲሁ ሦስት ግዜ የዓመቱ ምርጥ አልበምን በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ሴት በመሆን ታሪክ ሰርታለች።

ድምጻዊቷ ሽልማቱን ያገኘችው በኮሮናቫይረስ ውሸባ ውስጥ ሆና በሰራችውና "ፎክሎር" የሚል መጠሪያ በሰጠችው አልበሟ ነው።

ከዚህ ቀደም ፊርለስ በተሰኘው አልበሟ በ2010 እና 1989 የሚል መጠሪያ ባለው አልበሟ ደግሞ በ2016 ማሸነፏ ይታወሳል።

ከዚህ ቀደም ሦስት ድምጻውያን፤ ፍራንክ ሴናትራ፣ ፖል ሳይመን እንዲሁም ስቲቪ ወንደር ብቻ የዓመቱ ምርጥ አልበምን ሦስት ጊዜ አሸንፈው ያውቃሉ።

ቢዮንሴ 28ኛዋን የግራሚ ሽልማት ያሸነፈችበት ሥራዋ ለጥቁሮች ኃያልነትና ጽናትን ለማሰብ ባለፈው ዓመት ሰኔ 10 ያቀረበችው ነው።

"እንደ የጥበብ ሰው ያለሁበትን ዘመን ማንፀባረቅ ሥራዬ ነው ብዬ አምናለሁ፤ እናም ደግሞ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር" ብላለች ቢዮንሴ ሽልማቷን በተቀበለችበት ወቅት።

"ስለዚህ ሁሉንም ጥቁር ንግሥቶችና ንጉሦች እኔን እንዲያነሳሱ፣ ዓለምን እንዲያነቃቁ ማበረታታና ሞራላቸውን ከፍ ማድረግ ፈለግሁ" ብላለች ከሥራዋ ጀርባ የነበረውን ምክንያት ስታስረዳ።

በርና ቦይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሌላ ዜና ናይጄሪያውያኑ በርና ቦይና ዊዝ ኪድ የ2021 ግራሚ አዋርድን አሸንፈዋል።

በርና ቦይ በምርጥ ዓለም አቀፍ ሙዚቃ አልበም ዘርፍ ሲያሸንፍ፣ ዊዝኪድ በበኩሉ በምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ተሸልሟል።

ዊዝኪድ ቪዲዮውን የሰራው ከቢዮንሴ ጋር ሲሆን፣ ሙዚቃውም ብራውን ስኪን ገርል ይሰኛል።

የቢዮንሴ ልጅ የሆነችው ብሉ አይቪ በዚህ ሙዚቃ አሸናፊ ሆናለች።

የበርና ቦይ ትክክለኛ ስሙ ዳሚኒ ኦጉሉ ሲሆን ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ዕጩ ነበር።

በዘንድሮው የግራሚ ሽልማት የኮሮናቫይረስ ምክንያት አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ ሲባል የሙዚቃ ሥራዎች የቀረቡት በአምስት የተለያዩ መድረኮች ላይ ነው።

ኸር በቤተር ዛን አይ ኢማጂን በተሰኘው የአር ኤንድ ቢ ሙዚቃ አሸናፊ ሆናለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጥቁሮች ሕይወት ዋጋ አለው በሚል ስሜት ከተቀነቀኑ መካከል ሌላ ሽልማት ያገኘው ሥራ በአር ኤንዲ ቢ አቀንቃኟ ኸር (H.E.R.) የተዘፈነው ነው።

ድምጻዊቷ ስለሥራዋ ስትናገር ሙዚቃውን እናቷ ቤት ሆና ራሷ እንደቀረፀችው ተናግራለች።

ይህ ሙዚቃ ባለፈው ዓመት ጆርጅ ፍሎይድ የተባለው ጥቁር አሜሪካዊ አንገት ላይ አንድ ነጭ ፖሊስ ቆሞበት ሕይወቱ ከማለፉ በፊት 'መተንፈስ አልቻልኩም' ሲል የተናገረውን በመውሰድ የተሰራ ነው።

ኸር ትክክለኛ ስሟ ጋብሬላ ዊልሰን ሲሆን ባለፈው ዓመት ከሪያራ ቶማስ ጋር በመሆን ሙዚቃውን መጻፋቸው ይታወሳል።

ድምጻዊቷ በዚህ ሥራዋ አሸናፊ ሆና ሽልማት ስትቀበል "ፍርሃቴ እና ብሶቴ እንዲህ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አስቤ አላውቅም" ስትል ተናግራለች።

አክላም "ለዚያ ነው ሙዚቃ የምጽፈው፤ ደግሞ በጣም አመሰግናለሁ" ብላለች።