የግራሚ ሽልማት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተላለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ2021 የግራሚ ሽልማት ሥነ ሥርዓት በኮሮናቫይረስ ስጋት ሳቢያ ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉን የሽልማቱ አዘጋጆች አሳወቁ።
በዓለማችን የሙዚቃ ኢንደስትሪ ውስጥ ታላቅ ከሚባሉት ሽልማቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ሽልማት ከሦሰት ሳምንት በኋላ ነበር ሊካሄድ የታሰበው።
ነገር ግን በአሜሪካዋ የሎስ አንጀለስ ከተማና በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ በኮሮረናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ሥነ ሥርዓቱ ከሁለት ወር በኋላ መጋቢት አጋማሽ ላይ እንዲደረግ ተወስኗል።
በዚህ ዓመት ሊካሄድ ለታቀደው ሽልማት በኅዳር ወር ይፋ የተደረገው የዕጩዎች ዝርዝርን ቢዮንሴ፣ ቴይለር ስዊፍትና ዱዋ ሊፓ የቀዳሚነቱን እየመሩ ነው።
"ከሙዚቃው ማኅበረሰብና ይህንን የሽልማት ሥነ ሥርዓት ለማዘጋጀት ያለድካም እየሰሩ ካሉት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሠራተኞች ጤናና ደኅንነት በላይ የሚያሳስበን ምንም ነገር የለም" ይላል የግራሚ ሽልማትን ከሚያዘጋጀው ተቋም የወጣው መግለጫ ያለውን የጤና ስጋት በማመለከት።
የዚህን ዓመት የግራሚ ሽልማት መድረክ ይመራዋል ተብሎ የታሰበው ታዋቂው ኮሚዲያን ትሬቨር ኖዋ ይሳተፍ እንደሆነ አስካሁን ግልጽ አይደለም።
ምንም እንኳን እንዴት እንደሚሆን ዝርዝሩ ባይገለጽም ቀደም ሲል የሽልማቱ አዘጋጅ ድርጅት የዚህ ዓመቱ የግራሚ ሥነ ሥርዓት በአብዛኛው በኢንተርኔት አማካይነት የሚካሄድ እንደሚሆን መግለጹን ኤኤፍፒ ዜና ወኪል ዘግቦ ነበር።
ባለፈው ዓመት አሜሪካ ውስጥ የኮሮናቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ከግራሚ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሽልማቶች በኢንተርኔት አማካይነት ለመካሄድ ተገደዋል።
የአሜሪካዋ የካሊፎርኒያ ግዛት በተለይ በወረርሽኙ መስፋፋት ክፉኛ በመመታቷ የአምቡላንስ ሠራተኞች የታመሙ ሰዎችን ወደ ሆስፒታል እንዳያመጡ ታዘዋል።












