ተጣብቀው የተወለዱት መንትዮች በእንግሊዝ ከሕይወት ጋር እየተላመዱ ነው

በተወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይሞታሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት የተጣበቁ መንትዮች በሕይወት ኖረው ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ትምህርት ቤት መሄዳቸው ተሰምቷል።
የሚማሩበት ትምህርት ቤቱ የሚገኘው በእንግሊዝ ካርዲፍ ግዛት ነው።
ማሪየም እና ንዴዬ ንዲይ በጎርጎሮሳዊያኑ 2017 ነበር በአባታቸው ኢብራሂም አማካኝነት ከሴኔጋል ወደ ለንደን እንግሊዝ ወደሚገኘው ግሬት ኦርሞንድ ሰትሪት ሆስፒታል ለህክምና የተወሰዱት፡፡
ሴቶቹ አሁን በአራት ዓመታቸው መቆምን እየተማሩ ሲሆን አባታቸው ዕድገታቸውን "እጅን በአፍ የሚያስጭን ስኬት" ነው ሲል ገልጾታል።
ርዕሰ መምህራቸው ልጆቹ ጓደኛ አፍርተው "እየሳቁ፣ እየተጫወቱ ነው" ብለዋል።
ሁለት ልብ እና አከርካሪ ያላቸው ልጆቹ ጉበት፣ ፊኛ እና የምግብ መፍጫ ስርዓትን የሚጋሩ ሲሆን ለኮቪድ ተጋላጭ የሚሆኑባቸው ሁኔታዎች አላቸው።
አባታቸው ለዕድገታቸው መቀጠል በሚል ትምህርት እንዲጀምሩ መፈለጉን ተናግሯል።
"ሁኔታውን መለስ ብሎ ለተመለከተው የማይሳካ ህልም ነበር" ይላል የልጆቹን ሁኔታ ሲያስታውስ።
"ከአሁን በኋላ ወደፊት ያለው ሁሉ ለእኔ ተጨማሪ ነገር ነው። ልቤ እና ነፍሴ ጮክ ብለው እየጮኹ "በሉ ሴቶች ሂዱ! የበለጠ አስገረሙኝ' እያሉ ነው፡፡
ንዲይ በሴኔጋል ቀዳማይ እመቤት ማሪየም ፋዬ ሳል በሚተዳደረው የበጎ አድራጎት ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ወደ እንግሊዝ ካቀና በኋላ ጥገኝነት ጠይቋል።
ጥገኝነት ጠያቂዎች በየትኛውም እንግሊዝ ውስጥ ሊንቀሳቀሱ ስለሚችሉ በጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ቤተሰቡ በአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ አማካኝነት ወደ ካርዲፍ ተዛውሯል። እናም በአገሪቱ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችልም ፈቃድ አግኝተዋል።
በ 2019 የታላቁ ኦርሞንድ ስትሪት የቀዶ ጥገና ሐኪሞች መንትዮቹን ለመለያየት ቢያስቡም ከሚከሰቱ አደጋዎች የተነሳ አባታቸው ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
በኋላ ላይም ሐኪሞቹ የልጆቹ የደም ዝውውር ሥርዓቶች ቀደም ሲል ከታሰበው በላይ በጣም የተሳሰሩ ሆነው በማግኘታቸው አንዳቸው ካለ ሌላኛቸው በሕይወት የማይኖሩ ሆነው በመገኘታቸው የማለያየት እቅዱ ለጊዜው በዚህ ቆሟል።
ርዕሰ መምህሯ ሄለን ቦርሊ ከመስከረም ወር ጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እየተማሩ መሆናቸውን እና አዳዲስ ጓደኞችን አፍርተዋል ሲሉ ተማግረዋል።
'የተለያዩ ባህሪያት'
"ልጆች ወይ 'የማሪየም ጓደኛ ነኝ' ወይም 'የንዴዬ ንዲይ ጓደኛ ነኝ' ይላሉ እንጂ 'እኔ የመንትዮቹ ጓደኛ ነኝ' አይሉም፡፡ ልጆች የአንዷ ጓደኛ እንደሆኑ ያሳያሉ። ምክንያቱም ልጃገረዶቹ በጣም የተለያየ ባህሪ አላቸው" ብለዋል።
"ብዙ ጊዜ ይስቃሉ። ይህ ሁልጊዜ ጥሩ ምልክት ነው አይደል? ብዙ የሚስቅ ልጅ ደስተኛ ልጅ ነው" ሲሉ አክለዋል።
ለመንትዮቹ ትምህርት ከሆስፒታሉ ቀጠሮዋቸው ጋር መጣጣም አለበት፡፡

በጥቅምት ወር ልጃገረዶቹ በታላቁ ኦርሞንድ ስትሪት ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሕክምና ክፍል ይፈልጋሉ፡፡
በካርዲፍ ዌልስ የሕፃናት ሆስፒታል፣ የሕፃናት ሕክምና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ጊሊያን ቦዲ አደጋዎቹ ቢኖሩትም ህክምናው አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"ልጃገረዶቹ ውስብስብ የአካል ክፍሎች ያሏቸው ሲሆን ይህም ለበሽታዎች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል"ብለዋል።
"ካጋጠሙን ችግሮች መካከል አንዱ አንቲባዮቲኮችን በፍጥነት ወደ እነሱ ማስገባት ነበር፣ እናም ይህ ቱቦ ለልጆቹ ያለ ችግር በፍጥነት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል" ብለዋል።
በየሪየም ልብ ውስብስብ እና ያልተለመዱ ነገሮች ስላሉት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ስታደርግ መተንፈስ ሊያስቸግራት ይችላል።
'ሚዛኑን ማግኘት'
በሆሊ የህፃናት ሆስፒታል ውስጥ ልጆቹ እንዴት መቆም እንዳለባቸው ሲማሩ ቆይተዋል።
በልዩ ዘዴ እንዲቆሙ እና እግራቸው እንዲጠነክር እየተደረገ ነው።
የፊዚዮቴራፒ ባለሙያዋ ሳራ ዋዴ-ዌስት ከባድ ሆኖባቸው እንደነበር ተናግረዋል።
"ቁጭ ማለት በጣም ሲለመድ በእውነቱ የተለየ ስሜት ነው። ቀና ማለት አስፈሪ ሊሆን ይችላል" ብለዋል፡፡
"ሲጀምር በተለይም ንዴዬ ብዙም ፍላጎት አልነበራትም፤ ስልጠናውን ከጨዋታ ጋር እንሞክራለን። ትንሽ ተግተው እንዲሰሩ ለማድረግ ወደ መጫወቻዎች እንዲደርሱ እናበረታታቸዋለን። ግን ቴራፒ መሆኑን ካወቁ በጣም አስደሳች አይደለም" ሲሉ ይገልጻሉ።
"በልባቸው ምክንያት ብዙ ልንገፋቸው አንችልም። ስለዚህ ሚዛኑን እየጠበቅን ነው መሥራት ያለብን። ጠንካራ እንዲሆኑ ግን እንዳያደክማቸው በማድረግ" ብለዋል፡፡

ለአባታቸው ልጆቹ ቆመው ማየት አንድ ለውጥ ብቻ አይደለም፡፡
"ለመኖር ብቻ ሳይሆን ንቁ ሆነው በኅብረተሰቡ ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ እያሳዩ ነው" ይላል።
"እነዚህ ሁሉ ስኬቶች ለወደፊቱ ብርሃን እና ተስፋን ያመጣሉ። ሆኖም ህይወታቸው ምን ያህል ደካማ፣ ውስብስብ እና የማይገመት ሊሆን እንደሚችል አውቃለሁ" ብሏል።
ንዲይ "ብዙ ጊዜ ወደ መጥፎው ከበጎው የተጠጋ ነው። ስኬታቸው ከፍርሃቴ ጋር ትይዩ ነው" ብሏል፡፡
"ለልጆቹ ማድረግ የምችለው በጣም አነስተኛ ነገር፣ በእነሱ ላይ ያለኝ ተስፋ ምን እንደሆነ ማሳወቅ ነው።"
"እኔ ማድረግ የምችለው ከጎናቸው መሆን እና በዚያ ተስፋ ውስጥ መኖር ሲሆን ያንን ተስፋ እንዲነጥል በጭራሽ አለመፍቀድ ነው" ሲል ይገልጻል።
"እነሱ ተዋጊዎቼ ናቸው፡፡ ያለ ውጊያ በጭራሽ እጅ እንደማይሰጡ አረጋግጠዋል፡፡ ገና አልተጠናቀቀም" ሲል ያጠናቅቃል።















