ተጣብቀው የተወለዱት ታንዛኒያውያን ሕይወታቸው አለፈ

ተጣብቀው የተወለዱት ታንዛኒያውያን አለፉ

ማሪያና ኮንሶላታ ይባላሉ። ላለፉት 21 ዓመታት ጉበትና ሳንባን በጋራ ነበር የሚጠቀሙት። የየራሳቸው ልብ፣ ጭንቅላትና ክንዶች ነበሯቸው።

መስከረም አካባቢ ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ ሆስፒታል ገብተው ነው ያለፈው ቅዳሜ ሕልፈታቸው ከወደ ታንዛኒያ የተሰማው።

መንትያዎቹ በታንዛዊያን ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የነበሩ ሲሆን የሞታቸው ዜና ሲሰማ አገር አንብቶላቸዋል።

እጅግ በርካታ የአገሬው ዜጎች ትናንት ዕሑድ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን መሪር ሐዘናቸውን ሲገልጹ ውለዋል።

ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት የመንትዮቹ ዜና እንዳሳዘናቸውና እህትማማቾቹ ሐገራቸውን ለማገልገል ጽኑ ፍላጎት እንደነበራቸው አውስተዋል።

መንትዮቹ ባለፈው ዓመት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ የዩኒቨርስቲ ቆይታቸውን እንዳጠናቀቁ በመምህርነት ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው ነበር።

ማሪያና ኮንሱሌት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት በቀዶ ጥገና መለያየት እንደማይፈልጉና ሲያድጉ አንድ ባል አግብተው መኖር እንደሚሹ ተናግረው ነበር።

ወላጆቻቸው የሞቱት እነርሱ ገና ሕጻን ሳሉ በመሆኑ በካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት በማደጎነት ተሰጥተው ራሳቸውን ለመቻል ጫፍ ደርሰው ነበር።

ባለፈው ዓመት ከ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲመረቁ በርካታ የአገሬው ዜጎች እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቶችን በመላክ ደስታቸውን ገልጸውላቸው እንደነበር ይታወሳል።