በእንግሊዝ ተወልደው ያደጉ ጥቁር መንታዎች ወደማያውቋቸው አገራት እንዲባረሩ ተወሰነ

ዳሬልና ዳሬን ሮበርትስ እናታቸው በ13 አመታቸው ሞታለች

የፎቶው ባለመብት, Family photo

በለንደን ተወልደው በመንግሥት ይዞታ ስር ባለ ማደጎ ቤት ያደጉ መንታ ጥቁር ወንድማማቾች ወደተለያያዩ የማያውቋቸው የካሪቢያን አገራት እንዲባረሩ ተወስኗል።

የሃያ አራት አመት ወንድማማቾቹ ዳሬልና ዳሬን ሮበርትስ በፈፀሙት ወንጀል እስር ተፈርዶባቸው የነበረ ሲሆን አንደኛው ወንድሙ ከእስር ሲለቀቅም ውሳኔው ተፈፃሚ ይሆናል ተብሏል።

የዳሬል ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው የተፈረደበትን እስር እንዳጠናቀቀና እንግሊዛዊ ዜግነትም እንዳለው በመግለፅ ተከራክረዋል።

ይሄንን ጉዳይ የሚመለከተው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአገር እንዲወጡ ውሳኔ አለማስተላለፉን ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል።

ሁለቱም ወንድማማቾች ከሃገር ለማስወጣት ትዕዛዝ እንዳልተላለፈ ቃለ አቀባዩ ቢናገሩም ቢቢሲ ለአንደኛው ልጅ ከዚሁ መስሪያ ቤት ከአገር እንዲወጣ የተላለፈለትን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አግኝቷል።

መንታዎቹ የተወለዱት በምዕራብ ለንደን ሲሆን ወላጆቻውም ስደተኞች ሲሆኑ የመጡትም ከካሪቢያን ደሴቶች ከሆኑት ዶሚኒካና ግሬኔዳ ነው። ወላጆቻቸው እንግሊዛዊ ዜግነት የላቸውም ተብሏል።

እናታቸው በ13 አመታቸው መሞቷን እንዲሁም አባትየውም ወደ ዶሚኒካ መመለሱን ተከትሎ በመንግሥት ይዞታ ስር ባለ የእንክብካቤ ማእከል ተወስደው በዚያው ነው ያደጉት።

ዳሬል በአንድ ግለሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ በ17 አመቱ የስድስት አመት እስር ተፈርዶበት ነበር። ከእስር ሲለቀቅም ወደ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ እንዲሄድ ትዕዛዝ እንደደረሰውም ተገልጿል።

ባለስልጣናቱ አባቱ አለበት ወደተባለበት ዶሚኒካ ደሴት ለመላክ በሚል ተሳስተው ወደ ዶሚኒካን ሪፐብሊክም እንዲሄድ ማድረጋቸውንም ተናግሯል። አባቱም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውም አስታውቋል።ወንድሙ ዳሬን በበኩሉ በተለየ ወንጀል እስር ቤት ይገኛል።

ከእስር ሲወጣም የእናቱ ትውልድ ቦታ ወደሚባለው ግሬናዳ እንዲሄድ ትእዛዝ ደርሶታል።

ዳሬልና ዳሬን ሮበርትስ እናታቸው በ13 አመታቸው ሞታለች

የፎቶው ባለመብት, Family photo

ከመንትዮቹ በተጨማሪም የእንግሊዝ ዜግነት ከሌላቸው ቤተሰቦች የተወለዱና ከአመት በላይ እስር የተፈረደባቸው ልጆች ከአገር እንዲባረሩ ተወስኗል።

የሌላ አገር ዜጎች ልጆች ሆነው በእንግሊዝ መወለዳቸው ዜግነት እንዲያግኙ ቢያግዛቸውም በመወለዳቸው ብቻ ወዲያው ዜግነት የሚያገኙበት ሁኔታ የለም።

የመንታዎቹ እህት ፍሬያ ቫሊ ሮበርትስ ይህ ሁኔታ በጣም ያበሳጫት ሲሆን "አገር አልባ አድርጓቸዋል" ብላለች።

"ይሄ ስድብ ነው። ለምን ሁለት ወንድሞቼን ብቻ፤ አስራ አንድ ነን ሁላችንንም ከአገር ያባርሩን" ብላለች።

ፍሬያ አይተውት የማያዉቁት አገር መላካቸውና መመለስም አለመቻላቸውም እንዳስጨነቃትም አልደበቀችም።

የዳሬል ጠበቃ አንድሪው ስፔርሊንግ ይህንን ሁኔታም በጎርጎሳውያኑ 18ኛውና 19ኛው ክፍለ ዘመን ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች ወደ አውስትራሊያ ግዞት የሚፈፀምበትን ሁኔታ ያስታውሰኛል ብለዋል።

ደንበኛው እንግሊዛዊ መሆኑንም በመግለፅ እስሩን እንዳጠናቀቀና በተሃድሶ የሚያምን ማህበረሰብ እንደመሆኑ መጠን ድጋፍ ሊሰጠው ይገባልም በማለት ከአገር እንዲባረሩ መወሰኑ ኢ-ፍትሃዊ ነው ብለዋል።

ሌሎች የቤተሰብ አካላትም መንትዮቹ እንግሊዝ እንዲቆዩና ውሳኔው እንዲቀለበስ ለማድረግ ፊርማ እያሰባሰቡ ነው።