በየመን ተጣብቀው የተወለዱትን መንትዮች ለማዳን ጥሪ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በየመኗ መዲና ሰንዓ ተጣብቀው የተወለዱ መንትዮችን ህይወት ለማዳን ዶክተሮች እየተማፀኑ ነው።
በዚህ ሳምንት ረቡዕ በአል-ሳቢያን ሆስፒታል ተጣብቀው የተወለዱት መንትዮች ህይወታቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ እንዳለና ቀዶጥገናውም ውጭ አገር ብቻ መካሄድ እንደሚችልም የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
በየመን ባለው የርስበርስ ጦርነት ምክንያት ሰንዓ አየር ማረፊያ ተዘግቷል። የአገሪቷ የጤና ስርአትም ባለው ጦርነትም ዳሽቋል።
ሳዑዲ አረቢያ የሚገኝ የእርዳታ ማዕከል የእርዳታ እጁን ለመለገስ ሁኔታዎችን እየገመገምኩ ነው በማለት አስታውቋል።
"የህክምና መረጃዎች እንደሚያሳዩት መንትዮቹ የየራሳቸው ልብ አላቸው። ሆኖም የአንደኛው ልብ አቀማመጥ ትክክል እንዳልሆነ ያሳያል" በማለት የአል ሳቢን ሆስፒታል ዳይሬክተር ማጅዳ አል ካቲብ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ዳይሬክተሯ እንደሚሉት የመንትዮቹ የትኞቹ አካላት ተጣብቀው እንዳሉ ለማወቅ የሚያስፈልጉት የህክምና መሳሪያዎች በሆስፒታሉ የሉም።
ለዶክተሮቹም ጥሪ የንጉስ ሳልማን ሰብዓዊ እርዳታ ማዕከልም በበኩሉ የመንትዮቹን ሁኔታ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዶክተሮች ለመገምገምና መንትዮቹን ለመነጣጠል ዝግጁ ነን በማለት በትዊተር ገፁ አስታውቋል።
ሰንዓ በአሁኑ ወቅት በሁቲ አማፅያን ስር ቁጥጥር ናት። በሳዑዲ ከሚመራ ወታደራዊ ጥምር ኃይል የሚመራውንም ቡድን እየታገለ ይገኛል።
ባለፈው አመት በየመን ተጣብቀው የተወለዱ መንትዮች በተወለዱ በሁለት ሳምንታቸው ህይወታቸው አልፏል።
ተጣብቀው የተወለዱ መንትዮች፦
- ከአንድ እንቁላል ስለሚወለዱ ፍፁም ተመሳሳሳይ ናቸው
- ተጣብቀው የሚወለዱ መንትዮች ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም አይደለም። ከ200 ሺህ ውልደቶች አንድ ጊዜ የሚያጋጥም ነው።
- አብዛኛውን ጊዜ ደረታቸው፣ ሆዳቸው ወይም በታፋቸው ላይ ተጣብቀው ይወለዳል።
- ተጣብቀው ከሚወለዱት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።












