ትግራይ፡ "ግጭቱ አጎቴን ሱዳን ውስጥ ስደተኛ እንዲሆን አደረገው"

ወደ ሱዳን እየተሻገሩ ያሉ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Rex Features

በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ አጎታቸው ወደ ሱዳን የተሰደዱበትን ሁኔታ የቢቢሲ ሪፖርተር ፅፈዋል።

በንግድ ሥራና የእርሻ መሬት ባለቤት የሆነው አጎቴ በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ ወደ ሱዳን ከተፈናቀሉ መካከል አንዱ ሆነ።

ጨርቄን ማቄን ሳይል ነው የሸሸው፤ ጫማ እንኳን አላደረገም። ንብረቱን በግጭቱ ያጣው አጎቴ ነፍሴን ላድን ብሎም ነው በእግርና በጀልባ ወደ ሱዳን የተሰደደው።

በጭራሽ ግጭት ይፈጠራል ብሎም አላሰበም። ለዚያም ነው ጥቅምት መጨረሻ ላይ አድዋ ያሉትን ሚስቱንና ልጆቹን ተሰናብቶ ወደ ግብርና ማዕከሏ ሁመራ ያቀናው።

ሁልጊዜም በየዓመቱ የሚያደርገው ጉዞ ነው። ሁመራ ያለው እርሻው የሄደውም የሰሊጥና የማሽላ ምርቶቹ የሚሰበበሰቡበት የመኸር ወቅትም በመሆኑ ነው።

ከዚህ ቀደም ምርቱን ሰብስቦ በትግራይና ሱዳን ገበያዎች ይሸጣል። በዚህ ዓመት ግን ያልተጠበቀው ሆነና የአጎቴ ህይወት ብቻ ሳይሆን በትግራይ ክልል ያሉ በስምንት ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ግልብጥብጥ አለ።

የኢንቨስትመንት መሸጋገሪያዋ በግጭቱ ተጎዳች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የህወሓት ኃይሎች በክልሉ ባለው የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ጥቃት በመፈፀም "ቀዩን መስመር" አልፈዋል በማለትም ወታደራዊ ተልዕኮ እንዲካሄድ ትዕዛዝ ሰጡ።

በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል ውጥረት ከነገሰ ሰነባብቷል። በተለይም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ፓርላማው ምርጫው በሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲራዘም ያፀደቀ ቢሆንም የትግራይ ክልል በተናጠል ምርጫ ማድረጉ የበለጠ ነገሩን አክርሮታል።

በትግራይ ክልል የተደረገው የተናጠል ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ክልላዊው ምርጫ ሕገወጥ ነው በማለት ያወገዙ ሲሆን ህወሓት በበኩል ድግሞ የፌደራል መንግሥቱ ስልጣን ማብቂያ በመሆኑ ሕጋዊ ባልሆነ ሁኔታ ነው ስልጣን ላይ ያሉት ብሏል።

ግጭቱ ከተነሳበትት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም አንድ ሳምንት በኋላ መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ በመታገዝ የሁመራን ከተማን ከትግራይ ክልል መንግሥት ኃይሎች ጋር በመዋጋት ተቆጣጠረ።

30 ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ያላት ሁመራ ልማትን ለማፋጠን በሚል የኢንቨስትመንት ኮሪደር (መተላለፊያ) ከሆኑት ከተሞች መካከል አንዷ ናት።

ከፍተኛ የሰሊጥና ጥጥ ምርቷንም ወደ አሜሪካና ቻይና ወጪ ንግድ ይደረጋል።

በዚህ ዓመትም ምናልባት ምርቶች ላይላኩ ይችላሉ። አጎቴ በግጭቱ ማሳዎች በእሳት ሲጋዩ የተመለከተ ሲሆን የእሱ እርሻ ከዚህ ውስጥ መካከል መሆኑን እስካሁን አያውቅም።

"አጎቴ በምሽት ነው የተሰደደው"

ወታደራዊው ግጭት የብሔር ውጥረቱንም ያጋጋለው ሲሆን፤ ከተማዋን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግልም አማራና ተጋሩ ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ተጋሩው አጎቴ እንደሚለው በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ከፍተኛ ዘረፋና ግድያ ነበር።

ህይወቱም ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደገባ የተረዳው ከእነሱ ጋር ሲኖሩና አብረው ሲሰሩ የነበሩ ወዛደሮች ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያዎች በሁመራ ውስጥ የሚኖሩ ተጋሩዎችን መጠቆም ሲጀምሩ ነው ይላል።

2px presentational grey line

በተለይም ከኤርትራ በኩል የከባድ መሳሪያ ድብደባ የተፈፀመ እንደሆነ ቢናገርም የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትግራይ ክልል ላይ በተደረገው ወታደራዊ ውጊያ የኤርትራ ሠራዊት ከመከላከያ ጋር ተጣምሮ ክልሉን ወግቷል የሚለውን አይቀበሉትም።

ለህይወቱም በመስጋት፤ ነፍሱንም ለማትረፍ በሚል ምንም ነገር ሳይዝ ከቤቱ ወጣ። ረዘም ያለ መንገድም በእግሩ ተጉዞ ተከዜ ወንዝ ደረሰ። እዚያም በርካታ ተጋሩዎችን አገኘ። ወደ ሱዳንም ለመሻገር በጀልባው ላይ ወጣ።

በሞትና ህይወት ስጋት ላይ የነበረው አጎቴ እፎይታ ተሰማኝ የሚለው የተባበሩት መንግሥታት የተፈናቃዮች መጠለያ ማዕከል ሲደርስ ነበር። የነበሩት ድንኳኖች በተፈናቃዮች በመጨናነቁም ውጭ ለማደርም ተገደደ።

በመጠለያ ማዕከሉም ከሰው ተውሶ በሱዳን የስልክ ቁጥር ደወለልኝ።

ከሁለት ሳምንት በፊት በስልክ አውርተን የነበረ ቢሆንም እስከዚያ ወቅት ድረስ የት እንዳለ አላውቅም ነበር።

እኔ ብቻ አይደለሁም ግጭቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ ሚስቱና ልጆቹም ቢሆን ያለበትን አያውቁም፤ እስካሁንም ድረስ በሱዳን ስደተኛ መሆኑን አላወቁም።

"የአየር ጥቃቱ ቤተሰቤን ከቤታቸው አስወጣቸው"

አድዋ ያሉት የእሱም ቤተሰቦች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አላውቅም። የመከላከያ ሠራዊት የትግራይ ክልል ዋና ከተማን መቀለን ከመቆጣጠሩ በፊት አድዋን መቆጣጠሩን አስታውቋል።

ወላጆቼና እህት ወንድሞቼ መቀለ ነው የሚኖሩት- እኔ ደግሞ ልክ እንደ ሌሎቹ ዲያስፖራዎች በውጭ አገር በመኖሬ በከተማዋ ከተደረገው ከፍተኛ ድብደባና ጥቃት ተርፈው ይሁን አላውቅም።

1px transparent line

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል የመቀለ አይደር ሆስፒታል የቆሰሉትን ለማከም በህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም በአስከሬኖች ማስቀመጫ እጥረት መቸገሩን አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በነበረው ጥቃት በመቀለ ብቻ 19 ንፁሃን ዜጎች እንደተገደሉና 30 ሰዎችም እንደቆሰሉ ህወሓት የገለፀ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በበኩላቸው ወር ባስቆጠረው ግጭት አንድም ንፁህ ዜጋ አልተገደለም ብለዋል።

ስለ ቤተሰቤ የሰማሁት አንድ ከማውቀው ሰውና የስልክ አገልግሎት ማግኘት ከቻለ ሰው ነበር። የፌደራል መንግሥት ህዳር 7/2013 ዓ.ም መቀለ ዩኒቨርስቲ አካባቢ የአየር ጥቃት ባደረሰበት ወቅትም ነው።

በህይወቴ ፈታኙ ወቅት

ቤተሰቦቼና ወንድም እህቶቼ ጥቃት የደረሰበት የመቀለ ዩኒቨርስቲ ካምፓስ አካባቢ ነበር የሚኖሩት እናም ይህንንም ተከትሎ ቤተሰቦቼ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍና ለዘመናት የኖሩበትን ቤት ትተው ሄዱ።

በከተማም ሌላ ሰፈር ጎዳኞቻቸው ጋር ለመኖር ተገደዋል።

እስካሁንም ቤተሰቦቼን ማግኘት አልቻልኩም። በህይወቴ ውስጥ ፈታኙ የምለው ወቅት ነው። ከውጭ ሆኜም ማድረግ የምችለው ስለ ቤተሰቦቼም ሆነ ስለ ሌሎቹ ደኅንነት መፀለይ ነው።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግጭት በአብዛኛው ኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ነገር ግን በትግራይ ክልል መረጋጋት ነበር።

ይህ ሁኔታ ተቀይሯል። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መከላከያ መቀለን መቆጣጠሩን ተከትሎ ወታደራዊው ዘመቻ እንደተጠናቀቀ ቢገልፁም በተለያዩ የትግራይ ክፍሎች አሁንም ውጊያ እንዳለና የአየር ጥቃትም መኖሩን ሪፖርቶች እየወጡ ነው።

ይህ ቅዠትም ሆነ ስቃይ መቼ እንደሚያበቃ አናውቅም።

የደረሰው ጠባሳ መቼ እንደሚሽር፣ ቤተሰቦች መቼ እንደሚገናኙ፣ ለሞቱ ቤተሰቦች መቼ እርማቸውን እንደሚያወጡ፣ ትምህርት ቤቶች መቼ እንደሚከፈቱ፣ መቼ ትምህርት ቤትና የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚጀመር፣ ግብርናና ንግድ መቼ እንደሚጀምር- ህይወት በአጠቃላይ ወደቀደመው ሁኔታ እንደሚመለስ አናውቅም።

*በሪፖርቱ ላይ የግለሰቦቹ ስም ያልተጠቀሰው ለደንነታቸው ሲባል ነው