አወዛጋቢው የህንዱ ፀረ-እምነት መቀየር "የፍቅር ጂሃድ" ህግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ አንዲት የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆነች ግለሰብ በግድ ከሙስሊም ባለቤቷ ጋር እንድትለያይ መደረጓ እንዲሁም ከዚያ በኋላም በደረሰባት መንገላታት የተሸከመችው "ፅንስ ተጨናግፏል" ማለቷ በቅርብ አገሪቷ ፀረ-እምነት መቀየር ላይ ያወጣችውን ህግ አወዛጋቢ አድርጎታል።
በያዝነው ወር ነው ብርቱካናማ ቀለም ያለው የአንገት ሻርፕ የጠመጠሙ በርከት ያሉ ወንዶች፣ ይህችኑ የሂንዱ እምነት ነበረች ያሏትን ሴት ሲሰድቧት፣ ሲጎነትሏትና ሲያሰቃዩዋትም የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቷል።
በሰሜናዊ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ሞራዳባድ ከተማ ነዋሪ የሆነችውን ይህችን ሴት ከእምነትሽ ውጭ ለምን አገባሽም በሚልም ነው ግለሰቦቹ ሲያንገላቷት የታየው።
"እንደ አንቺ ባሉ ሴቶች ምክንያት ነው ይሄ ህግ የወጣው" በማለትም አንደኛው ሲጎነትላት ይታያል።
አነዚህ ግለሰቦች ፅንፈኛና አክራሪ ሂንዱዎች ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ናሬንድራ ሞዲ ባህራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) ቀንደኛ ደጋፊዎች ናቸው።
ህጉ በአክራሪ ሂንዱዎች "የፍቅር ጂሃድ" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሙስሊም ወንዶች ሂንዱ ሴቶችን በጋብቻ ውስጥ እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያደርጓቸዋል የሚለውንም ለማመላከት የሚጠቀሙበት ነው።
የሚያወሩለትም ህግ በቅርቡ የፀደቀና "የፍቅር ጂሃድና የእምነት ቅየራን መታገል ላይ ያነጣጠረ ነው።
ክስተቱ የተፈጠረው ከሁለት ሳምንታት በፊት ሲሆን የባጃራንግ ዳል ነዋሪዎች የ22 አመቷን ግለሰብ፣ ባለቤቱንና ወንድሙን ለፖሊስም አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። ፖሊስም እሷን ወደ መንግሥት መጠለያ ካደረሳት በኋላ ባለቤቷንና የባለቤቷን ወንድም አስሯቸዋል።
የሰባት ወር ነፍሰ ጡር የነበረችው ይህችው ግለሰብ ፅንሷ እንደተጨናገፈም አስታውቃለች።
በዚህ ሳምንትም ፍርድ ቤት ቀርባ የነበረ ሲሆን እሷ እንደምትለው በግድ ሳይሆን በፈቃዷ ሙስሊም ወንድ እንዳገባች አስታውቃለች። ፍርድ ቤቱም ወደ ባሏ መንደር እንድትመለስ በነፃ አሰናብቷታል። ባለቤቷም ሆነ የባለቤቷ ወንድም አሁንም በእስር ላይ ናቸው።
ከሚዲያዎች ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ በመጠለያው ያሉ ሰራተኞች አያያዝ ለፅንሱ መጨናገፍ ምክንያት ሆኗል ብላለች። በከፍተኛ ሁኔታ ሆዷ ላይ ህመም እንደሚሰማት ብትናገርም ችላ እንዳሏትም አሳውቃለች። መጠለያው በበኩሉ ግለሰቧ የምትለውን አስተባብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Gajanfar Ali
"የጤናዬ ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየባሰና በከፍተኛ ሁኔታ እየባሰ ሲመጣም ነው ወደ ሆስፒታል የወሰዱኝ። የደም ምርመራ ከተደረገልኝ በኋላ ሆስፒታል አስተኙኝ። በወቅቱም መርፌም ወጉኝ፤ ከዚያ በኋላም ነው ከፍተኛ ደም ይፈሰኝ የጀመረው"
ከሁለት ቀናትም በኋላም እንዲሁ ተጨማሪ መርፌዎች እንደወጓት ትናገራለች። ይፈሳት የነበረው ደምም እየጨመረና የጤናዋ ሁኔታም እየከፋ በመጨረሻም የ7ወር ፅንሷም ተጨናገፈ "ልጄንም አጣሁ" በማለት ትናገራለች።
ሆን ተብሎ የተከሰተ ይሁን ግልፅ አይደለም፤ ሆስፒታልም ውስጥ የተፈጠረው ነገርም እንደተድበሰበሰ ነው።
ግለሰቧ በቁጥጥር ስር እንዳለች ባለስልጣናቱ "ፅንሱ ተጨናግፏል" መባሉ ሃሰት ነው የሚል ሪፖርት አውጥተው ነበር።
ሪፖርቱ የባለቤቷን እናት በዋነኝነት አናግሬያለሁ፤ የፅንሱንም ደህንነት ተረድቻለሁ ይላል።
የህፃናት ደህንነት ጥበቃ ኮሚሽን ሊቀመንበር ቪሸሽ ጉብታ ፅንሱ ተጨናግፏል የሚሉ ሪፖርቶችን በሙሉ የካዱ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ "ልጁ በሙሉ ጤነንነት ላይ ነው" ለማለትም ደፍረዋል።
ግለሰቧ ህክምና ያገኘችበት ሆስፒታል የማሕፀን ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር "የሰባት ወር ፅንስ" እንደተሸከመች በአልትራሳውንድ ያሳይ ነበር።
ነገር ግን ዶክተሩ እንደሚሉት የማህፀን ምርመራ ብታደርግ የህፃኑ ደህና መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል ይላሉ።
ነገር ግን ከእስር ከተለቀቀች በኋላ "ፅንሱ ተጨናፈግፏል" በማለት ስለተናገረችው ጉዳይ ባለስልጣናቱ አስተያየት አልሰጡም።
በሆስፒታሉ ውስጥ ያደረገጋቸውን የአልትራሳውንም ምርመራዎችን ጨምሮ የተወጋቻቸውን መድሃኒቶች ማስረጃ ሊሰጧት አልቻሉም።
ሆስፒታል ከገባች ከአምስት ቀናት በኋላ ግለሰቡ ፅንሱ በህይወት ይኑር አይኑር እርግጠኛ የሆነ ነገር የለም። በርካታ ጥያቄዎችንና ጥርጣሬዎችንም አስነስቷል።
ሆኖም ግለሰቧ ፅንሷ ተጨናግፏል የሚሉ ሪፖርቶች መላ ህንዳውያንን አስቆጥቷል። በርካቶችም ለዚህ ህይወት መታጣት ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው ባለስልጣናቱ ናቸው በማለት በማህበራዊ ሚዲያዎች እያወገዙ ይገኛሉ።
በህንድ የተለያዩ ሃይማኖት ተከተያዮች በፍቅር መጣመርም ሆነ መጋባት ከፍተኛ ውግዘትን የሚያስተናግድ ሲሆን በተለይም ቤተሰቦች በጭራሽ የሚቀበሉት ሁኔታም አይደለም።
ነገር ግን "የፍቅር ጂሃድ" የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ህግ አንድ ሰው ለማግባት በሚል እምነቱን መቀየር ከፈለገ ከግዛቲቱ ባለስልጣናት መጀመሪያ ፈቃድ ሊያገኝ ይገባል። ይህም ሁኔታ ሰዎች በነፃነት የማፍቀርና የህይወት አጋሮቻቸውን የመምረጥ መብታቸውን የሚጥስና ለመንግሥትም ሙሉ በሙሉ የዜጎችን መብት የመቆጣጠር ሁኔታንም ይሰጣል።
በዚህ ህግ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ግለሰብ የዋስ መብቱ አይከበርለትም፤ እስከ አስር አመት የሚያደርስም እስር ይጠብቀዋል። ኡታር ፕራዴሽ ግዛት በግድ ወይም በማጭበርበር የሚደረግን የእምነት ቅየራ ለመታገል በሚል አዲሱን ህግ በማፅደቅ የመጀመሪያዋ ሆናለች።
ግዛቷ ግን የመጨረሻ አትሆንም ቢያንስ አራት ግዛቶች "የፍቅርን ጂሃድ" እንዋጋለን በሚል ህጉን ለማፅደቅ እቅድ ይዘዋል።
ኡታር ፕራዱሽን ጨምሮ አምስቱ ግዛቶችን የሚመራው ባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ ሲሆን ከዚህ ቀደምም በፀረ- እስልምና አመላካከቶቹ ወቀሳ ሲደርስበት ነበር።
ተችዎች ህጉ አስፀያፊና አስነዋሪ ነው በማለት የጠሩት ሲሆን የተለያየ እምነት ተከታይ ባለትዳሮችን ለማጥቃት ያነጣጠረ ነው ብለውታል።
በተለይም የቀኝ ክንፍ አክራሪ ሂንዱ ቡድኖች በሴት የሂንዱ እምነት ተከታዮችና በሙስሊም ወንዶች መካከል የሚደረገውን ጋብቻም ለመቃወም ያለመና ፀረ-ሙስሊምም ነው በማለት ተችዎች ይናገራሉ። ህጉም እንዲቀየር የሚጠይቅም ፊርማም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ገብቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ህጉ በፀደቀ በአንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በርካቶች በዚህ አወዛጋቢ ክስ መከሰሳቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ።
በፈቃዳቸው የተጋቡ እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸውም ጭምር ፈቃድ ያገኙ በርካታ በተለያየ እምነት መካከል የሚደረጉ የትዳር ጥምረቶች በህጉ ከተጠየቁት መካከል ናቸው። ሙስሊም ሙሽሮቹም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ዴህራዱን በምትባል ከተማ የምትኖር የ22 አመት ግለሰብ እምነቷን ወደ እስልምና ቀይራ ሙስሊም ባሏን ያገባችው በሃምሌ ወር ነበር። አቅራቢያቸው ወዳለች ሞራዳባድ በምትባል ግዛትም ጋብቻቸውን ለማስመዝገብ በሚመጡበት ወቅት በቁጥጥር ስር ውለዋል።
"የእንደዚህ አይነት ህጎች ዋነኛ ችግር በተለያዩ እምነቶች መካከል የሚደረግ የፍቅር አጋርነትንም ሆነ የትዳር ጥምረትን እንደ ወንጀል ነው የሚቆጥረው" በማለት የታሪክ ተመራማሪው ቻሩ ጉብታ ይናገራሉ።
"የሴቶችን በራሳቸው የመወሰን መብት የሚጥስ ነው። ነፃ ፈቃዷ ጋርም የሚቃረን ነው። ማግባት የምትፈልገውን ማግባት የሴት ምርጫዋ አይደለም እንዴ? እምነቷን መቀየር ብትፈልግ ወይም ቀይራ ማግባት ብትፈልግ ችግሩ ምኑ ላይ ነው?" በማለት ይጠይቃሉ።
"ህጉ በጣም ሰፊና በርካታ አወዛጋቢ ነገሮችንም የሚጠቀልል ስለሆነም የተከሰሱትም ሰዎች ንፁህ መሆናቸውን እንዲያስመሰክሩም ይጠበቅባቸዋል። ይህም አደገኛ ነው" ይላሉ።












