ህንዳዊው ሙስሊም የሂንዱ ሴት እምነት በመቀየር ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ዋለ

ህጉን የሚቃወሙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በህንዷ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት አንድ ሙስሊም ግለሰብ የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆነችን ሴት ወደ እስልምና ሊቀይር ሞክሯል በማለት ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎታል።

አገሪቷ ባወጣችው ፀረ- እምነት መቀየር ህግም ተጠርጥሮ የታሰረው የመጀመሪያው ግለሰብ ሆኗል።

ህጉ በአክራሪ ሂንዱዎች "የፍቅር ጂሃድ" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሙስሊም ወንዶች ሂንዱ ሴቶችን በጋብቻ ውስጥ እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያደርጓቸዋል የሚለውንም ለማመላከት የሚጠቀሙበት ነው።

ይህ ህግ በህንድ ውስጥ "ሙስሊም ጠል" ነው በሚልም ከፍተኛ ትችትን እያስተናገደ ነው።

ሆኖም ህጉ በተጨማሪ አራት ግዛቶች ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን "የፍቅር ጂሃድ"ን ለመቃወም በሚል ግዛቶቹ እያረቀቁት ነው ተብሏል።

የኡታር ፕራዴሽ ፖሊስ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር መዋሉንም በትዊተር ገፁ በትናንትናው ዕለት አሳውቋል።

ባለፈው ሳምንት የልጅቷ አባት እምነትሽን ካልቀየርሽ በሚል ጫናም እንዲሁም ማስፈራሪያ እያደረሰባት ነው በማለት ሪፖርት አድርገዋል።

ግለሰቧ ከሰውየው ጋር በፍቅር ግንኙነት ውስጥ እንደነበረችና ሌላ ሰውም እንዳገባች ተዘግቧል።

እምነት ልትቀይር ሞክረሃል የተባለው ግለሰብ ለአስራ ቀናት ያህል ቀጠሮ የተጠየቀበት ሲሆን ከሴትዮዋ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውና ንፁህ እንደሆነም ለሪፖርተሮች ተናግሯል።

ዋስ የሚከለክለው አዲሱ ህግ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ አስር አመትም ያስቀጣል።

"የፍቅር ጂሃድ ህግ ምንድን ነው?

ኡታር ፕራዴሽ ግዛት በግድ ወይም በማጭበርበር የሚደረግን የእምነት ቅየራ ለመታገል በሚል አዲሱን ህግ በማፅደቅ የመጀመሪያዋ ሆናለች።

ግዛቷ ግን የመጨረሻ አትሆንም ቢያንስ አራት ግዛቶች "የፍቅርን ጂሃድ" እንዋጋለን በሚል ህጉን ለማፅደቅ እቅድ ይዘዋል።

ኡታር ፕራዱሽን ጨምሮ አምስቱ ግዛቶችን የሚመራው ባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ ሲሆን ከዚህ ቀደምም በፀረ- እስልምና አመላካከቶቹ ወቀሳ ሲደርስበት ነበር።

"የፍቅር ጂሃድ" የቀኝ ክንፍ አክራሪ ሂንዱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት የነበረና በህንድ ህገ መንግሥትም እውቅና የሌለው ነው በማለትም "አስነዋሪ" በማለት ተችዎች ይናገራሉ።