የእስራኤል ምክር ቤት አባላት ፓርላማውን ለመበተን የድጋፍ ድምፅ ሰጡ

ቤንጃሚን ኔታንያሁና ቤኒ ግራንትዝ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤል ምክር ቤት አባላት ፖርላማውን ለመበተን የሚያስችለውን ከፍተኛ የድጋፍ ድምፅ ሰጥተዋል።

ፓርላማው እንዲበተንም የመጀመሪያ ዙር ከፍተኛ ድምፅ ተገኝቷል ተብሏል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ጋር ስልጣን የመጋራት ስምምነት የገቡት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ግራንትዝ ድጋፍም ነው ውሳኔው ያለፈው።

በትናንትናው ዕለት ውሳኔ የተላለፈበት የፓርላማ ይበተን ረቂቅ እንደገና ክንሴት ተብሎ ለሚጠራው የአገሪቷ ፓርላማ ለግምገማ መቅረብ አለበት።

ፓርላማውም ገምግሞ በአዲሱና ቀጣዩ ምርጫ ላይ ውሳኔ ያሳልፋል፤ በዚህም መሰረት እስራኤል በሁለት አመት ውስጥ አራተኛ ምርጫዋንም ልታካሂድም እቅድ ይዛለች።

የእስራኤል የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የአገሪቱን በጀት በተመለከተ መስማማት አቅቷቸው ለረዥም ጊዜ በማያፈናፍን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

በትናንትናው ዕለት በነበረው የድምፅ መስጫ ስነ ስርአት 61 ለ54 በሆነ ብልጫ ፓርላማው እንዲበተን ውሳኔ ተላልፏል።

ከምርጫው በፊት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ የአገሪቱን በጀት ስምምነት አዘግይተዋል በማለት "የምጣኔ ኃብት የሽብር ጥቃት" እየፈፀሙ ነው ሲሉ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ወቅሰዋቸዋል።

ቤኒ ግራንትዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበጀቱን ስምምነት ያዘገዩት ሆን ብለውና የስልጣን ጊዜያቸውንም ባልተገባ ሁኔታ ለማራዘም ነው ይላሉ።

"ኔታንያሁ እኔን ብቻ አይደለም የዋሸኝ፤ እናንተንም ዋሽቷችኋል። የእስራኤልን ህዝብ አጭበርብሯል" በማለትም ወርፈዋቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በበኩላቸው ወቅቱ "የምርጫ አይደለም። የአንድነት ጊዜ ነው" ብለዋል።

በስልጣን የመጋራቱ ስምምነት መሰረት ናታንያሁ በጠቅላይ ሚኒስትርነት 18 ወራት ካገለገሉ በኋላ ለቤኒ ግራንትዝ ማስተላለፍ አለባቸው።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የበጀቱ ስምምነት ወደየትም ባለመሄዱ ስልጣናቸውን ለማስረዘም ክፍተት እየፈለጉ ናቸው በማለት ተንታኞች መናገራቸውን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።

አገሪቷ በአውሮፓውያኑ 2018 በፀደቀ በጀት እየሰራች ያለች ሲሆን ከዚያም በኋላ ሶስት ምርጫዎችን አካሂዳለች።

የቀኝ ክንፉ ሊኩዊድ ፓርቲ መሪ የሆኑት ናታንያሁ በሙስና ወንጀልም የፍርድ ሂደታቸው እየታየ ነው።

ጉቦ በመክፈል፣ በማጭበርበርና እምነት በማጉደል ውንጀላ የቀረበባቸው መሪው በጭራሽ እንዳልፈፀሙ ይናገራሉ።