ቢቲኤስ የሙዚቃ ቡድን በአልበም ሽያጭ ቴይለር ስዊፍትን እና ድሬክን በለጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሪያው የወንዶች የሙዚቃ ቡድን ቢቲኤስ እአአ በ2020 በአልበም ሽያጭ ቴይለር ስዊፍትን መብለጡ ተነገረ።
እነዚህ የኮሪያ ፖፕ ሙዚቃ ኢንደስትሪ የከባድ ሚዛን ሻምፒዮና አሸናፊዎች፣ ተብለው የሚወደሱት የቡድኑ አባላት በአውሮፓና በአሜሪካ በአገራቸው ቋንቋ አቀንቅነው የበርካቶችን ልብ ማሸነፍ የቻሉ ናቸው።
ቴይለር ስዊፍት በእአአ 2019 በምርጥ አልበም ሽያጭ ቀዳሚ የነበረች ሲሆን፣ በ2020 ቢቲኤስ የደረጃ ሰንጠረዡን በቀዳሚነት እንደመራ ተገልጿል።
ቢቲኤስ በእንግሊዘኛ ያቀነቀኑት እና ዳይናማይት ሲሉ የጠሩት ነጠላ ዜማቸው አሜሪካውያን የሙዚቃ አድናቂዎችን ለሸመታ በገፍ ያስወጣ እነርሱንም ከእነ ሌዲ ጋጋ በአቻነት ለሽልማት ያሳጨ ነበር።
እኤአ በ2019 በአልበም ሽያጭ ቀዳሚ የነበረችው ቴይለር ስዊፍት በ2020 የሁለተኛነት ደረጃ ላይ ወርዳለች።
የዓለም አቀፉን የሙዚቃ ኢንደስትሪ ሽያጭ የሚመዘግበው ኤኤፍፒአይ፣ የኮሪያው የፖፕ ቡድን ቢቲኤስ በ2020 ምርጥ ሽያጭ ያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልጿል።
ቢቲኤስ በ2020 ሁለት ምርጥ የሙዚቃ አልበሞችን ለአድናቂዎቻቸው አድርሷል። ማፕ ኦፍ ዘ ሶል፡7 እና ቢ የተሰኙት እነዚህ አልበሞች በአድናቂዎቻቸው ዘንድ ተወድውላቸዋል።
2020 በዓለማችን በሚገኙ 20 አገራት በአንደኝነት የተደመጠ ነጠላ ዜማ ያበረከቱበት ዓመትም ሆኖ ተመዝግቧል።
ማፕ ኦፍ ዘ ሶል፡7 የተሰኘው አልበማቸውም ታትሞ ከመሰራጨቱ በፊት በብዛት በመታዘዝ ቀዳሚነቱን የያዘ አልበም ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሙዚቃ ስራዎቻቸው ጋር በተያያዘ ሰባቱም የቡድኑ አባላት ቢሊየነር ሆነው ተመዝግበዋል።
የቢቲኤስ አባላት ዓለም አቀፍ የአልበም ሽያጩን በበላይነት ሲቆናጠጡ የመጀመሪያው ምዕራባውያን ያልሆኑ የሙዚቃ ቡድኖች ናቸው።
ይህ ብቻ ሳይሆን ሙዚቃቸውም ሙሉ በሙሉ በእንግሊዘኛ ያልተዘፈነ መሆኑም ከሌሎች የደረጃ ሰንጠረዡን ከተቆጣጠሩ ድምጻውያኖች ለየት ያደርጋቸዋል።
የዓለም አቀፍ ሽያጩ የሚሰላው በመላው ዓለም ያለው የሙዚቃው ሰንዱቅ ሽያጭ፣ ከኢንተርኔት ላይ ገዝተው የሚያወርዱና የሚያዳምጡ አድናቂዎች ቁጥር እንዲሁም በኦንላየን በቀጥታ እያጫውቱ የሚያዳምጡ አፍቃሪዎች ብዛት ተሰልቶ ሲሆን፣ እንዲሁም የእነርሱን ዘፈኖች ለመጫወት ፈቃድ ጠይቀው ክፍያ የሚፈጽሙ ሙዚቀኞችም ቀመሩ ውስጥ ይካተታሉ።
በ2020 የምርጥ አልበሞች ሽያጭ ድሬክ ሶስተኛ፣ ዘዊኬንድ አራተኛ፣ ቢሊ ኤሊሽ ደግሞ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ቢቲኤስ በሌላ ስማቸው ባንግተን ቦይስ በመባል የሚጠሩ ሲሆን የተመሰረቱት እአአ በ2013 ላይ ነው።
ሰባት አባላት ያሉት ይህ ቡድን ከመላው ደቡብ ኮሪያ የተወጣጡ ወጣት ወንዶችን አቅፎ ይዟል።
ለኮሪያ የፖፕ የሙዚቃ ስልት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አልበሞችን እና የኮንሰርት ቲኬቶችን በመሸጥ፣ በቢሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎች በኦንላየን ቀጥታ ስራዎቻቸውን በማድመጥ የኮሪያን ፖፕ ኢንደስትሪ ሚዛን አክብደውታል፤ የደረጃ ልኬቱንም አርቀው ሰቅለውታል ተብሏል።
ቡድኑን ከሃሳብ ጀምሮ ፀንሶ ያዋለደው ቀድሞ በኬፖፕ መዝናኛ ውስጥ የተለያዩ ቡድኖችን በማደራጀት እና በመምራት ልምድ የነበረው ፀኃፊ እና ፕሮዲውሰር ባንግ ሺ ሂውክ ነው።
ባለፈው ዓመት ብቻ በኮርያ የአክስዮን ገበያ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ በማፍሰስ የቢቲኤስ አባላት 108 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንዲችሉ አድርጓል።
ባለፈው ዓመት በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በተለያዩ መድረኮችና ስታዲየሞች ማቅረብ እንዳይችሉ ያደረጋቸው ቢቲኤሶች ሁለተኛ አልበማቸውን ቀርፀው ለአድማጮቻቸው አቅርበዋል።
ይህ አልበም ዳይናማይት የተሰኘ የሙዚቃ ስራቸው የተካተተበት ሲሆን፣ የመጀመሪያው በእንግሊዘኛ የተዘፈነና የተለቀቀ ነጠላ ዜማቸው ነበር።
በአሜሪካ ይህ ስራ እንደተለቀቀ የደረጃ ሰንጠረዦችን መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን በኦንላየን በቀጥታ በብዛት በመደመጥም ቀዳሚ ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ ዳይናማይት የተሰኘው ስራቸው ቢቲኤሶችን ከነ ሌዲ ጋጋ እና ቴይለር ስዊፍት ተርታ ለግራሚ አሳጭቷቸው ነበር።












