እውቁ የሬጌ አቀንቃኝ በኒ ዌይለር በ73 ዓመቱ አረፈ

በኒ ዌይለር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኒ ዌይለር

በሬጌ ሙዚቃ እጅግ እውቅ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው በኒ ዌይለር በ73 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ከኪንግስተን ጀማይካ የተገኘው ይህ ሙዚቀኛ ከአብሮ አደግ ጓደኛው ቦብ ማርሌ ጋር በመሆን 'ዘ ዌይለርስ' (The Wailers) የተሰኘውን የሙዚቃ ቡድን መስርቷል።

ሁለቱ ሙዚቀኞች 'ሲመር ዳውን' (Simmer Down) እና 'ሰቲር ኢት አፕ' (Stir It Up) በተሰኙት ሙዚቃዎቻቸው ዓለም አቀፍ እውቅናን ማትረፍ ችለው ነበር። ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 1974 ላይ በኒ ዌይለር ከቡድኑ በመለየት ለብቻው ሙዚቃ መስራቱን ቀጥሎ ነበር።

ከዚህ በኋላ በነበሩት ዓመታት እጅግ ስኬታማ የሚባል የሙዚቃ ዘመን ያሳለፈው በኒ ሶስት የግራሚ ሽልማቶችን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2017 ላይ ደግሞ የጃማይካ ከፍተኛ ሽልማትን ማግኘት ችሏል።

በኒ ሕይወቱ ማለፏ ይፋ የተደረገው በማናጀሩ ማኢን ስቶው እና የጀማይካ ባህል ሚኒስትር ኦሊቪያ ግሬንጅ አማካይነት ነው።

ለበኒ ህይወት ማለፍ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ የታወቅ ነገር የለም። ነገር ግን ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ በደም ግፊት ምክንያት ሆስፒታል አልጋ ላይ ተኝቶ ነበር።

የሙዚቀኛውን ህልፈተ ሕይወት ተከትሎ በርካቶች ሀዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። አድናቂዎቹ እና የሙዚቃ ባለሙያዎች ዓለም ትልቅ የሙዚቃ ባለሙያዋን አጣች በማለት ሀዘናቸውን ገልጸዋል።

የጀማይካ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሪው ሆልነስም በሙዚቀኛው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ''ለጀማይካ እና ለሬጌ ሙዚቃ ትልቅ የነበረ ሰው አጥተናል'' በማለት ገልጸዋል።

የበኒን ሞት ተከትሎ ዘ ዌይለርስ የሚባለው የሙዚቃ ቡድን ከመሰረቱት ሙዚቀኞች መካከል በሕይወት የቀረው 'ዘ ስታር' በሚል ስሙ የሚታወቀው ኔቪል ኦራይሊ ሊቪንግስተን ብቻ ነው።

ሊቪንግስተን ለመጀመሪያ ጊዜ ከቦብ ማርሌ ጋር የተዋወቀው ገና በልጅነቱ ሲሆን በስቴፊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሆነው ነበር በጋራ ሙዚቃ መስራት የጀመሩት።

በአውሮፓውያኑ 1955 ላይ የቦብ ማርሌ አባት መሞታቸውን ተከትሎ የቦብ ማርሌ እናት ልጇን ይዛ ከሊቪንግስተን አባት ጋር መኖር ጀመረች። ይህ ተከትሎም ሁለቱ ጓደኛማቾች በአንድ ቤት ውስጥ እንደ አድገዋል።

ሁለቱ ጓደኛማቾች ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በመሆን ነበር ዘ ዌይለርስ የተሰኘውን የሙዚቃ ቡድን ማቋቋም የቻሉት። ምንም እንኳን ለታዳጊዎቹ በወቅቱ ከነበረው ድህነትና የጸጥታ ችግር የተነሳ ሙዚቃ መስራት ከባድ የነበረ ቢሆንም የዘመኑ ታዋቂ የሬጌ አቀንቃኝ ጀ ሂግስ እርዳታን አጊንተው ነበር።

በእርሱ እርዳታም የሙዚቃ ችሎታቸውና እውቀታቸው መዳበር ችሏል።

1993 ላይ ደግሞ ቦብ ማርሌ እና ጓደኞቹ ስቱዲዮ ገብተው ሲመር ዳውን የተሰኘውን ሙዚቃ አቀነቀኑ። ሙዚቃው በዋነኝነት በኪንግስተን ከተማ የነበሩ የወንጀለኛ ቡድኖች መጣላታቸውን አቁመው ሰላም እንዲሰፍን የሚጠይቅ ነበር።

የዚህን ሙዚቃ መለቀቅ ተከትሎ ቦብ ማርሌ እና በኒ ዌይለር እውቅና በመላው ጃማይካ አስተጋባ። ብዙም ሳይቆዩ ደግሞ የተለያዩ ሙዚቃዎችን ለማቅረብ በአሜሪካና እንግሊዝ መጓዝ ጀመሩ።

ነገር እውቅናቸውን ተከትለው የመጡት ነገሮች ብዙም ያላስደሰተው በኒ 1973 ላይ እራሱን ከሙዚቃ ቡድኑ በመለየት ለብቻው ሙዚቃን መስራት ጀመረ። ለዚህም ያቀረበው ምክንያት በጉዟቸው ላይ የሚያደርጓቸው ነገሮች ከራስተፈሪያኖች አስተምህሮትና አኗኗር ጋር የማይጣጣሙ ነገሮችን ስላስተዋልኩኝ ነው ብሎ ነበር።

ከዚህ በኋላ ነገር 1981 ላይ 'ሮክ ኤን ግሩቭ (Rock 'n' Groove) የለቀቀው አልበምና እና ሌሌች ስራዎቹም ከፍተኛ ተቃይነትና ተወዳጅነት አስገኝተውለታል። በ1990ዎቹ ደግሞ በምርጥ የሬጌ አልበም ዘርፍ ሶስት ጊዜ የግራሚ ሽልማትን ማግኘት ችሏል።