ጆን ኤፍ ኬኔዲ፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከአፍሪካ የነፃነት አባቶች ጋር እንዴት ተገናኙ?

የፎቶው ባለመብት, JFK Presidental Library
ከአፍሪካ ጋዜጠኞች በተከታታይ ከተጻፉት ደብዳቤዎች አንዱ በሆነው የሴራ ሊዮን-ጋምቢያዊው ጸሐፊ አዴ ዳራሚ አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ስላላት ግንኙነት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲን የሚያሳዩ ፎቶዎችን ሰንዶ አዘጋጅቷል።
ኬኔዲ በጎርጎሮሳዊያኑ 1961 ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት አገራቸው አሜሪካ በአፍሪካ እየተካሄደ የነበረውን ፈጣን ለውጦች ለመረዳት ብዙም ሙከራ አላደረገችም ነበር።
1963 ላይ በተገደሉ ወቅት ግን ይህ ምስል በከፍተኛ ደረጃ ተለውጧል።
ኬኔዲ በሥልጣን በቆዩበት አጭር ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው ከሁለት ደርዘን በላይ ነፃ የአፍሪካ ሀገር መሪዎችን ወይም አምባሳደሮቻቸውን በኋይት ሃውስ ተቀብለው አነጋግረዋል።
ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው ከአንድ ዓመት በፊት 17 የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ገዥዎቻቸው ነፃነታቸውን አግኝተዋል። ይህን ተከትሎም ዓለም እየተለወጠ መሆኑን የተገነዘቡት ኬኔዲ አዲስ ግንኙነት መመስረት እንደሚያስፈልግ አውቀዋል።
ግንኙነቱ የተመሠረተውም አዲሶቹን የአፍሪካ አገራት በመደገፍ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, JFK Presidential Library
በ 1960 በተካሄደው የምርጫ ዘመቻ ኬኔዲ የአይዘንሃወርን አስተዳደር "የአፍሪካን ህዝብ ፍላጎት እና ምኞት ቸል ብሏል" በማለት ደጋግመው በመተቸት አሜሪካ ከቅኝ ገዥዎች ጎን ሳይሆን ከፀረ-ቅኝ አገዛዝ እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጎን መሆን እንዳለባት ሲናገሩ ነበር።
ኬኔዲ ስልጣን ከያዙ በኋላ ቀዩን ምንጣፍ ዘርግተው የአፍሪካ መሪዎችን ለጉብኝት ጋብዘዋል።
በቀዳማዊት እመቤት ጃኪ ኬኔዲ ታጅበው የኢትዮጵያውን ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴን እና የሞሮኮውን ንጉሥ ሐሰን አራተኛን ጭምሮ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች አሜሪካ ሲገቡ አቀባበል አድርገዋል።
እንዲሁም የክብር ዘበኞች፣ የተትረፈረፈ እራት እና የባሌ ዳንስ፣ ቲያትር እና ታሪካዊ ጉብኝት ተካተዋል።
ሁሉም ጉብኝቶቹ በመገናኛ ብዙሃን ጎልተው የታዩ ሲሆን ህዝቡም በደስታ እንዲወጣ ተበረታቷል።
ኬኔዲ እና እንግዶቻቸው በእንኳን ደህና መጣህ ጽሑፎች እና በደስታ በተሞላ ህዝብ በተጌጡ ጎዳናዎች እንዲሁም የአየር ሁኔታው ከፈቀደም ክፍት በሆነ መኪና ይጓዛሉ።
በእርግጥ በዚህ ሁሉ ውስጥ የፖለቲካ ፍላጎት ነበር። ሶቪዬት ህብረት ከቀድሞ የቅኝ ገዥዎች ራሳቸውን ለማራቅ ከሚፈልጉ የአፍሪካ መንግስታት ጋር ተመሳሳይ ሽርሽር እያደረገች ነበር።
ኬኔዲ ስልጣኑን እንደተረከቡ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት በፍጥነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, JFK Presidential Library
"አምናለሁ ... የራሳችንን አብዮት የምንመጥን ከሆንን በቀጣዮቹ አስርት ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ አብዮት አካሄድ ወደ ዴሞክራሲ እና ነፃነት ይሆናል። ወደ ኮሚኒዝም በጣም የከፋ የቅኝ ግዛት ዓይነት ወደ ሆነው ኮሙኒዝም አይሆንም" ሲሉም ተናግረዋል።
ከበዓለ ሲመታቸው ከአንድ ወር በኋላም የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሃገሮችን ከጎናቸው ለማሰለፍ እንደ ቁልፍ አጋር ያዩቸውን ፕሬዝዳንት ሊዮፖል ሴዳር ሴንጎርን እንዲያገኙ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ሊንደን ጆንሰንን ወደ ሴኔጋል ልከዋል።
ከአንድ ወር በኋላ ኬኔዲ ወጣት አሜሪካውያንን በዓለም ዙሪያ የላከውን የሰላም ጓድ አስጀመሩ። በጎርጎሮሳዊያኑ ነሐሴ 1961 ወደ ጋና እና ታንጋኒካ ለመሄድ የተዘጋጀውን የመጀመሪያውን በጎ ፈቃደኞች ቡድን ወደ ኋይት ሃውስ ጋብዘው ነበር።
ኬኔዲ ስልጣን ከመያዛቸው ከሦስት ቀናት በፊት የኮንጎ የነፃነት ጀግና ፓትሪስ ሉሙምባ የሲአይኤ እጅ አለበት ተብሎ በሚጠረጠርበት ሂደት መገደሉ ከሶቪዬት ህብረት ጋር ቀዝቃዛውን ጦርነት በአህጉሪቱ እየተጫወቱ እንደነበር ያመላክታል።
ኬኔዲ ለአህጉሪቱ ልማትና ዕድገት ከልብ የመነጨ ፍላጎት ነበረው ብዬ እከራከራለሁ።
ተተኪያቸው የነበሩት ጆንሰን ግንኙነቶችን ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ባለመጋራታቸው ያለጊዜ መሞታቸው ወላፈኑ አፍሪካ ውስጥ እንዲሰማ ምክንያት ሆኗል።
ከ 60 ዓመታት በኋላም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለአፍሪካ ያላቸውን ፖሊሲ መቅረፅ ጀምረዋል።












