የአሜሪካ ግዛቶች የኮቪድ-19 ክልከላዎችን ማንሳት ጀመሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቴክሳስ፣ ሚሺጋን፣ ሉዊዚያና እና ሚሲሲፒ ግዛቶች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ አይሆንም አሉ።
የግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች ከዚህ ውሳኔ የደረሱት ኮቪድ-19 በአሜሪካ ለአራተኛ ዙር ሊሰራጭ ይችላል የሚል ስጋት ባለበት ወቅት ነው።
ሪፓብሊካኑ የቴክሳስ ገዢ ግሬግ አቦት፤ “ቴክሳስን 100% ለመክፈት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል። ቴክሳስ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ አይደለም በማለት ያወጀች ትልቋ የአሜሪካ ግዛት ነች።
በዚህም መሰረት ከአንድ ሳምንት በኋላ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ አይሆንም። ዜጎችም በመንግሥት ተቋማት ማስክ ሳያደርጉ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፤ በገበያ ስፍራዎችም ማስክ ሳያደርጉ መገበያየት ይችላሉ።
የሚሲሲፒ ገዢ በበኩላቸው በቀጣይ ቀናት የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ አይሆንም ብለዋል። ታቴ ሪቭስ፤ “ማስክ የማድረግ ግዴታ እናነሳለን። የንግድ ተቋማትም ከነገ ጀምሮ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
የባይደን አስተዳደር ግን አሁንም ቢሆን የኮሮናቫይረስ ክልከላዎች መተግበር አለባቸው የሚል ጽኑ አቋም አለው።
የኮሮናቫይረስ ክትባት በአሜሪካ በስፋት በመከፋፈሉ፤ በርካታ አሜሪካውያን ክትባቱን በመውሰዳቸው ሕይወት ወደቀደመ መልኩ ለመመለስ ፍላጎት እንዲጨምር አድርጓል ተብሏል።
ባይደን ትናንት አሜሪካ ለሁሉም አዋቂ አሜሪካውያን እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ የኮቪድ-19 ክትባት ማቅረብ ይቻላታል ብለዋል።
በቅርብ ሳምንታት በቫይረሱ የሚያዙ እና የሚሞቱ አሜሪካውያን ቁጥር ቀንሷል።
ይሁን እንጂ የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ) አገሪቱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ የማታደርግ ከሆነ ወረርሽኙ ለ4ኛ ዙር ሊከሰት ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
አሜሪካ እስካሁን 28 ሚሊዮን ሕዝቧ በቫይረሱ መያዙን በምርመራ ያረጋገጠች ሲሆን፤ 516 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን አጥተዋል።












