ጎርባቾቭ በመጨረሻ ፕሬዝዳንትንት የመሯት ሶቭየት ኅብረት እንድትፈርስ ያደረጉ አምስት ምክንያቶች

የዛሬ 30 ዓመት ታለቋ ሶቪየት ኅብረት ከሰመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዛሬ 30 ዓመት ታለቋ ሶቪየት ኅብረት ከሰመች

የመጨረሻው የሶቭየት ኅብረት ፕሬዝዳንት የነበሩት ሚካይል ጎርባቾቭ በ91 ዓመታቸው ማክሰኞ ነሐሴ 24/2014 ዓ.ም. አርፈዋል።

ኃያሏ ሶቭየት ኅብረት ህልውናዋ ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት ሲያበቃ ወደ 15 አገራት የተከፋፈለች ሲሆን፣ ሁሉም እራሳቸውን የቻሉ ነጻ አገራት ሆነዋል።

ዓለም በሁለት የርዕዮተ ዓለም ጎራዎች በተከፈለችበት ወቅት የሶሻሊስቱን ዓለም በመምራት የዩናይትድ ስቴትስ ተገዳዳሪ ሆና የቆየችነው ሶቭየት ኅብረትን በመምራት ጎርባቾቭ የመጨረሻው መሪ ሆነዋል።

በርካቶች ጎርባቾቭ ምድራችንን ከኒውክሌር ጦርነት የታደጉ የሰላም መሪ እያሉ ሲያሞካሿቸው፣ ሌሎች ግን ሶቭየት ኅብረት እንድትፈርስ በማድረስ ዓለም በምዕራቡ ተጽእኖ ስር እንዲወድቅ አድርገዋል በማለት ይወቅሷቸዋል።

በእርግጥ ለሶቭየት ኅብረት መፍረስ ጎርባቾቭ ሚና ነበራቸው?

Short presentational grey line

የዛሬ ሰላሳ ዓመት ታኅሣሥ 25/1991 (እአአ) ሚካይል ጎርባቾቭ ከሶቭየት ኅብረት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸው ለቀቁ።

በማግስቱ ታኅሣሥ 26 የአገሪቱ ምክር ቤት ፓርላማ (ሱፕሪም ሶቪየት) ከታላቋ ሶሻሊስት አገር ተለይተው እራሳቸውን ለሚችሉት ለ15 አዳዲስ አገራት ነጻነት በይፋ ዕውቅና ሰጥቶ የሶቪየት ኅብረትን ህልውና አከተመ።

በአንድ ወቅት ከዓለም ኃያላን አገራት መካከል አንዱ ምልክት የነበረው ማጭድና መዶሻ ያረፈበት ቀዩ የሶቪየት ኅብረት ሰንደቅ አላማ ከክሬምሊን ሰማይ ላይ ወረደ።

ጎርባቾቭ ወደ ሥልጣን የመጡት በ1985 ሲሆን በወቅቱ 54 ዓመታቸው ነበር። ለዓመታት በተመሳሳይ ሥርዓት ውስጥ የቆየችውን አገር አዲስ ህይወት እንድትዘራ ተከታታይ የለውጥ ማሻሻያዎችን አደረጉ።

ፔሬስትሮይካ (መልሶ ግንባታ እና መልሶ ማዋቀር) እንዲሁም ግላስኖስት (ግልጽነት እና የመናገር ነፃነት) በመባል የሚታወቁት ማሻሻያዎች፣ የአገሪቱን ውድቀት አምጥተዋል ብለው ብዙዎች ይከራከራሉ። ሌሎች ደግሞ የሶቪየት ኅብረት ለመለወጥ ዝግጁ አለመሆን አገሪቱን ለማዳን አክብዶት ነበር ይላሉ።

ሶቪየት ኅብረት ራሷን ታእበት ስለነበረውና ከሌላው ዓለም ጋር በነበራት ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስላሳደሩት የውድቀቷን ዋና ዋና ምክንያቶች መለስ ብለን እንመለከታለን።

1. ምጣኔ ሀብት

ከሶቪየት ኅብረት ችግሮች ሁሉ ዋነኛው የኢኮኖሚው ውድቀት ነው። ከሌሎች አገራት የገበያ መር ኢኮኖሚ በተቃራኒ አገሪቱ ከማዕከል የሚመራ ምጣኔ ሀብት ነበራት።

በሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፐብሊክ ግዛት ውስጥ ሁሉም ነገር ምን ያህል መመረት እንዳለበት በመንግሥት ይወሰናል። በዚህም ከሚመረቱ የመኪናዎች ብዛት አስከ ጥንድ ጫማዎች ወይም ዳቦ ብዛት ድረስ ውሳኔው ከማዕከል የሚመጣ ነው።

በተጨማሪም እያንዳንዱ ዜጋ ከተመረቱት ነገሮች ውስጥ ምን ያህሉ እንደሚያስፈልገው፣ ምን ያህል ወጪ እንደሚያስፈልግ እና ሰዎች ምን ያህል መከፈል እንዳለባቸው ይወስናል።

ይህ የአሰራር ሥርዓት ቀልጣፋ እና ፍትሃዊ ይሆናል የሚል ንድፈ ሃሳባዊ እሳቤን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ በተግባር ላይ ግን በተቃራኒው ሆኖ ተንገዳግዷል።

በዚህም ሳቢያ በአገሪቱ ውስጥ አቅርቦት ፍላጎትን ማሟላት ካለመቻሉም በላይ ብዙ ጊዜ ገንዘብ ትርጉም የለሽ ነበር።

በሶቪየት ኅብረት ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ድሆች አልነበሩም። ነገር ግን በቂ ዕቃ ስለማያገኙ በቀላሉ መግዛት አይችሉም ነበር።

መኪና ለመግዛት ለዓመታት በተጠባባቂ ዝርዝር ውስጥ ይቆያሉ። ኮት ወይም ጥንድ የክረምት ቦት ጫማዎችን ለመግዛት ለብዙ ሰዓታት ወረፋ ይዘው ይጠብቃሉ። ተራቸው ሲደርስ ደግሞ የሚሆናቸው የጫማ ቁጥር ተሽጦ ማለቁ ይነገራቸዋል።

በሶቪየት የመጨረሻ ቀናት የመሠረታዊ ሸቀጦች እጥረትና በየሱቆች ወረፋዎችን ማየት የተለመደ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሶቪየት የመጨረሻ ቀናት የመሠረታዊ ሸቀጦች እጥረትና በየሱቆች ወረፋዎችን ማየት የተለመደ ነበር

በሶቪየት ኅብረት ሰዎች አንድ ነገርን ስለመግዛት አይናገሩም (ኩፒት ይሉታል)። የሚናገሩት በእጃቸው ስለማስገባት ነገር ብቻ ነው (ዶስታት ይባላል)።

ነገሩን የከፋ ያደረገው በሶቪየት ኅብረት እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ የተጀመረው የጠፈር ጉዞ እና የጦር መሣሪያ ግንባታ ፉክክር የፈለገው ከፍተኛ ወጪ ነው።

በዚህም ሶቪየት ሰውን ወደ ምህዋር የላከች የመጀመሪያዋ አገር ስትሆን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እና ከፍተኛ ተወንጫፊ የባለስቲክ ሚሳኤሎች ባለቤትም ነበረች። ይህ ሁሉ ግን በጣም በውድ ዋጋ የተገኘ ስኬት ነው።

ሶቪየት ኅብረት ለዚህ ውድድር ነዳጅና ጋዝ በመሳሰሉት የተፈጥሮ ሀብቶቿ ላይ ብትተማመንም በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነዳጅ ዋጋ አሽቆለቆለ። ይህም ቀድሞውንም እያሽቆለቆለ የነበረውን ምጣኔ ሀብቷን ከድጡ ወደ ማጡ ወሰደው።

የጎርባቾቭ ፔሬስትሮይካ ፖሊሲ አንዳንድ የገበያ መርሆችን አስተዋውቋል። ሆኖም የሶቪየት ኅብረት ምጣኔ ሀብት በፍጥነት ለመሻሻል የማይመች ዓይነት ነበር።

የእቃዎች እጥረት ባለበት ሲቀጥል የዋጋ ግሽበትም ናረ።

ባለሥልጣናት እአአ በ1990 በአገሪቱ የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ አደረጉ። ይህ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የነበራቸውን ውስን ቁጠባን እንዲያጡ አደረገ።

በመንግሥት ላይ የነበረው ምሬትና ሮሮ እየተባባሰ ሄደ።

ዛሬስ?

የፍጆታ እቃዎች እጥረት በድኅረ ሶቪየት ህዝብ አስተሳሰብ ላይ ዘላቂ ተጽእኖ ነበረው።

ከአንድ ትውልድ በኋላም መሠረታዊ ፍላጎቶች አይኖሩም የሚል ፍራቻ በሕዝቡ ዘንድ አሁን ድረስ አለ።

በምርጫ ቅስቀሳዎች ወቅት በቀላሉ ስሜትን ለመግዛት የሚያስችል ጭምር ነው።

2. ርዕዮተ ዓለም

ሰዎች ያሰቡትን ለመናገር፣ ለመጠየቅ ወይም ለማጉረምረም በጣም በሚፈሩበት ጨቋኝ አገዛዝ ውስጥ አስርር ዓመታትን ባሳለፈች አገር ውስጥ የጎርባቾቭ ግላስኖስት ፖሊሲ የተሻለ የመናገር ነፃነትን ለመፍቀድ ያለመ ነበር።

በጆሴፍ ስታሊን (እአአ ከ1924 እስከ 1953 መካከል ባለው ጊዜ የሶቪየት መሪ የነበረ) ዘመን የተፈጸመውን የጭቆና መጠን የሚያሳዩ ታሪካዊ ማኅደሮች መከፈት ጀመሩ።

ስለ ሶቪየት ኅብረት የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ የሥልጣን አወቃቀር፣ ወደፊት ለመራመድ እንዴት ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት የሚመክር ክርክር አበረታቱ።

ፀረ ጎርባቾች የተቃውሞ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጎርባቾች በዓለም ዙሪያ አድናቆትን ቢያገኙም በአገራቸው ውስጥ ግን ተወዳጅ አልነበሩም

የኮሚኒስት ፓርቲን የበላይነት በመሞገትም የመድበለ ፓርቲን ሥርዓት ሃሳብ ላይ እስከመወያየት ደርሰዋል።

ይህም የሶቪየትን ሃሳብ ከማስተካከል ይልቅ ብዙዎች አገሪቱ ውስጥ የነበሩ የኮሚኒስት ፓርቲ አመራሮች (ሁሉም ባለሥልጣናት ወይ ተሹመው ነው ወይም በይስሙላ ምርጫ ያሸነፉ ናቸው) ሥርዓቱ ውጤታማ ያልሆነ፣ አፋኝ እና ለሙስና ክፍት ነው ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል።

የጎርባቾቭ መንግሥት አንዳንድ ነጻነት እና ፍትሃዊነትን በምርጫ ሂደቱ ውስጥ ለማስተዋወቅ ቢሞክርም ጊዜው በጣም ዘግይቶ ነበር።

ዛሬስ?

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የጠንካራ አገራዊ ሃሳብ አስፈላጊነትን በተለይም ሙሉ በሙሉ ግልጽ እና ዲሞክራሲያዊ ላልሆነ መንግሥት ያለውን አስፈላጊነት ተረድተውታል።

ፕሬዚዳንትነቱ የተከበረ አገራዊ ሃሳብን ለመፍጠር በተለያዩ የሩሲያ እና የሶቪየት ዘመናት የተፈጠሩ ሃሳቦችን ተጠቅመዋል።

እነዚህም የኢምፔሪያል ሩሲያ ሀብት እና ዝና፣ በስታሊን ስር የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀግንነት እና የድል መስዋዕትነት እንዲሁም በ1970ዎቹ የነበረው መረጋጋት፣ የሶቪየት ዘመን ኩራትን እና የአገር ፍቅርን ለማነሳሳት በዛሬዋ በሩሲያ ጥቅም ላይ ውለዋኀዕ።

3. ብሔርተኝነት

የሶቭየት ኅብረት የሩሲያ ኢምፓየር ወራሽ የሆነች ኅብረ ብሔርዊ አገር ነበረች።

ሶቪየት ኅብረት 15 ሪፐብሊኮችን ያቀፈች ስትሆን በንድፈ ሃሳብ ደረጃ እያንዳንዳቸው እንደ ወንድማማች ግዛቶቸ እኩል መብት ያላቸው ነበሩ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ሩሲያ እጅግ በጣም ግዙፍ እና ኃያልም ነበረች። የሩሲያ ቋንቋ እና ባህል ብዙ አካባቢዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር።

ግላስኖስት በ1930ዎቹ የነበረውን የዩክሬን ረሃብ፣ የባልቲክ ግዛቶች እና ምዕራባዊ ዩክሬን በሶቭየት ናዚ የወዳጅነት ስምምነት መሠረት መያዙን፣ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የበርካታ ጎሳዎች በግዳጅ መፈናቀልን እና በሌሎች ሪፐብሊኮች ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ያሳለፉትን የጎሳ ጭቆና እንዲገነዘቡ አድርጓል።

ፖለቲካዊ ቀውሱ ሲባባስ በሶቪየት ግዛቶች ውስጥ የብሔረተኝነት ስሜት ጠንክሮ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፖለቲካዊ ቀውሱ ሲባባስ በሶቪየት ግዛቶች ውስጥ የብሔረተኝነት ስሜት ጠንክሮ ወጣ

እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች የብሔርተኝነት ስሜት እና የራስን እድል በራስ የመወሰን ጥያቄዎችን አስነሳ።

የሶቪየት ኅብረት አገራት እንደደስተኛ ቤተሰብ ናቸው የሚለው ሀሳብ ሊሞት ከጫፍ ደርሶ የነበር እና ለሪፐብሊኮቹ የበለጠ የራስ ገዝ አስተዳደር በመስጠት እንደገና ለማሻሻል የተደረገው የጥድፊያ ሙከራም ትንሽ እንደዘገየ ታይቷል።

ዛሬስ?

ማዕከላዊ ሚናዋን እና የተፅዕኖ ቦታዋ ለመጠበቅ እየታገለች ባለችው ሩሲያ እና ከሶቪየት በኋላ በተፈጠሩ ብዙ አገራት መካከል አሁንም ውጥረት አለ።

በሞስኮ እና በባልቲክ ግዛቶች፣ በጆርጂያ እና በቅርብ ጊዜ ደግሞ በዩክሬን መካከል ያለው ግንኙነት የአውሮፓን እና በሌሎች አካባቢዎችም ያለውን የጂኦፖለቲካ ገጽታ ላይ ተፅዕኖውን እያሳረፈ ቀጥሏል።

4. ፍላጎት መሟጠጥ

የሶቪየት ሕዝብ ለዓመታት የምዕራባውያኑ ሥርዓት "እየበሰበሱ" እንደሆነ እና ሕዝቡም በካፒታሊስት መንግሥታት ስር በድህነት እና በውርደት እንደሚሰቃይ ተነግሮታል።

በ1980ዎቹ መገባደጃ ጀምሮ በግለሰቦች መካከል የሚደረግ ጉዞ እና ቀጥተኛ ግንኙነት እያደገ ሲመጣ ይህ ሃሳብ ይበልጥ ጥያቄ ውስጥ መግባት ጀምሮ ነበር።

የሶቪየት ዜጎች በሌሎች በርካታ ሃገራት ውስጥ ያለውን የኑሮ ደረጃ፣ የግል ነጻነት እና ደኅንነት በአገር ቤት ካለው እጅግ የላቀ መሆኑን ማየት ችለዋል።

ባለሥልጣናትም ዓለም አቀፍ ጉዞን በመከልከል፣ የውጭ አገር የመገናኛ ብዙኃንን (እንደ ቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ያሉትን) በማፈን፣ ወደ ሶቭየት ኅብረት እንዲገቡ የተፈቀደላቸውን የውጭ አገር ጽሑፎችንና ፊልሞችን ሳንሱር በማድረግ ለዓመታት የቻሉትን ሞክረዋል።

ጎርባቾቭ የቀዝቃዛው ጦርነትን በማቆም እና ከምዕራባውያን ጋር ያለውን ግንኙነት በማሻሻል የኒውክሌር ግጭት ስጋትን በማስቆም ጥሩ መስራታቸው ይነገርላቸዋል።

ጎርባቾች ከወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጎርባቾች ከወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን ጋር

እነዚህ የተሻሻሉ ግንኙነቶች ያልታሰበ ውጤት በማምጣት የሶቪየት ኅብረት ሕዝብ ኑሮ ከሌሎች አገራት ጋር ሲወዳደር ምን ያህል ደካማ እንደሆነ እንዲገነዘቡ አድርጓል።

ጎርባቾቭ በአገር ውስጥ ብዙ ትችት ቢገጥማቸውም በውጭ አገር ግን ተወዳጅ ለመሆን ችለዋል።

ዛሬስ?

የሩሲያ መንግሥት የሚዲያ መልዕክቶችን ለራሱ ጥቅም በማዋል ረገድ የተካነ ነው።

ከተቀረው ዓለም ጋር የማይመች ንጽጽርን ለማስወገድም ብዙውን ጊዜ ሩሲያ በባህልም ሆነ በታሪክ ልዩ እንደሆነች ተደርጋ ትቀርባለች። በተጨማሪም በጠላት የተከበበች ብቻዋን ጸንታ የቆመች እንደሆነም ይገለጻል።

ሳይንሳዊ ግኝቶች፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተመዘገበው ድል እና የባህል ቅርስ ያለማቋረጥ በመገናኛ ብዙኃን እየቀረቡ ብሔራዊ ልዩ የመሆን መልዕክትን ለዜጎች ሲያስተላልፉ የሩሲያውያንንም ትኩረት ከዕለት ተዕለት ችግሮች ዞር እንዲሉ አድርጓል።

5. አመራር

ጎርባቾቭ የሶቪየትን ምጣኔ ሀብት እና የሕዝቡን ሞራል መውደቅን ለመግታት ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልግ አውቀው ነበር። ይህንን እንዴት ማሳካት እንደሚቻል ያላቸው ራዕይ ግን ምናልባትም ግልጽነት የጎደለው ነበር።

የቀዝቃዛውን ጦርነት በማስቆም በውጭው ዓለም ጀግና ሆነዋል። በአገር ውስጥ ደግሞ ለውጥ አራማጆች መነሳሳትን አልፈጠሩም ሲሏቸው፣ ወግ አጥባቂዎች በበኩላቸው ያለልክ ተጓዙ በሚል ይነቅፏቸው ነበር።

በዚህ ምክንያት በሁለቱም ቡድኖች ተገለሉ።

ወግ አጥባቂዎች ጎርባቾቭን ከሥልጣን ለማውረድ ነሐሴ 1991 ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ሞከሩ።

ጎርባቾቭ ከሥልጣን ሲሰናበቱ በተደረገ ግብዣ ላይ የመጨረሻ ጽዋቸውን ሲያነሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጎርባቾቭ ከሥልጣን ሲሰናበቱ በተደረገ ግብዣ ላይ የመጨረሻ ጽዋቸውን ሲያነሱ

ያልተሳካው መፈንቅለ መንግሥት ሶቪየት ኅብረትን ከማዳን ይልቅ ጥፋቱን አፋጠነው። ሦስት ቀን ሳይሞላ የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች ከአገር ለመሸሽ ሞከሩ። ይህን ተከትሎ ጎርባቾቭ ወደ ሥልጣን ቢመለሱም ለአጭር ጊዜ ነበር።

ሩሲያ ውስጥ ቦሪስ የልሲን በተቀረው ሶቪየት ውስጥ ደግሞ የየአካባቢው መሪዎች ወደ ፊት መጡ።

በቀጣዮቹ ወራት ብዙዎቹ የሶቪየት ሪፐብሊኮች የነጻነት ሕዝበ ውሳኔ አድርገው በታኅሣሥ ወር የታላቋ ሶሻሊስታዊት አገር የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ተወሰነ።

ዛሬስ?

ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ለረዥም ጊዜ ካስተዳደሩ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ለረዥም ዓመታት እንዲመሩ ካስቻሏቸው ምስጢሮች አንዱ ሩሲያን ቀዳሚ ማድረግ፣ ወይም ቢያንስ እንደዚያ እንዲመስል ማድረግ ነው።

ሚኻይል ጎርባቾቭ በሶቪየት ኅብረት ዘመን በብዙ ድካም የተገኙ ነገሮችን መልቀቃቸው (ለምሳሌ የሶቪየት ጦርን ከምሥራቅ ጀርመን በችኮላ ማውጣታቸው) ሲያስተቻቸው፣ ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ የሩሲያ ጥቅም ነው ብለው ያመኑበትን ለመፈጸም ባለበሌለ ጉልበታቸው የሚችሉትን ያደርጋሉ።

ፑቲን የበርሊን ግንብ ሲፈርስ በምሥራቅ ጀርመን የኬጂቢ (የሶቪየት የደኅንነት አገልግሎት) መኮንን ነበሩ። በዚህም የሶቭየት ኅብረትን መውጣት ያስከተለውን ምስቅልቅል በዓይናቸው አይተዋል።

ከሠላሳ ዓመታት በኋላ ኔቶ ወደ ሩሲያ ድንበር መቅረቡን አጥብቀው ይቃወማሉ። ይህንንም በኃይል ለመግታት በመዘጋጀትም በቅርቡ በዩክሬን ደንበር አቅራቢያ ያለውን የሩሲያ ጦር ቁጥር ከፍ ማድረጋቸው ታይቷል።