ቻይና ከ1970ዎቹ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጨረቃ ላይ የአለት ስብርባሪዎችን ልታመጣ ነው

ጨረቃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ከ1970ዎቹ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጨረቃ ላይ የአለት ስብርባሪዎችን ለማምጣት ጥረት እንደምታደርግ አስታወቀች።

ነገ ማክሰኞች ዕለት ወደ ጨረቃ ጉዞውን የሚያደርገው መንኩራኩር ከጨረቃ ላይ ከተለያዩ ቦታዎች የአለት ስብርባሪዎችን ይዞ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

ከጨረቀ የሚመጡ ስብርባሪዎች የጨረቃን አፈጣጠር ለመረዳት ይጠቅማልም ተብሏል።

ለመጨረሻ ጊዜ የሰው ልጅ ከጨረቃ ላይ የአለት እብርባሪ ለማምጣት መንኩራኩር የላከው በ1976 የሶቪየት ሕብረት ስትሆን በወቅቱ ስራው በስኬት እንደተጠናቀቀ ተገልጾ ነበር።

ቻይና ይህ እቅዷ የሚሳካላት ከሆነ ከአሜሪካ እና ሶቪየት ሕብረት በመቀጠል ሶስተኛዋ አገር መሆን ትችላለች።

'ቻንግ-5' የተባለው መንኩራኩር በጥንታዊ የቻይና ጨረቃ አማልክት የተሰየመ ሲሆን በማርች 5 ሮኬት አማካይነት ወደ ጨረቃ እንደሚወነጨፍ ተገልጿል።

ቻይና በእቅዷ መሰረት ነገሮች የሚሄዱ ከሆነ እስከ 2 ኪሎግራም ድረስ የሚመዝን የአለት ስብርባሪ ለማምጣት አስባለቸው። አለቱን የሚመጣውም እስካሁን በሰው ልጅ ተጎብኝቶ ከማያውቅ የጨረቃ ክፍል እንደሆነ ተገልጿል።

በ1976ቱ የሶቪየት ህበረት ተልዕኮ 170 ግራም የአለት ስብርባሪ ነበር ወደ ምድር ተይዞ መመለስ የተቻለው። በአሜሪካው አፖሎ ሚሽን ደግሞ 382 ኪሎግራም የአለት ስብርባሪና አፈርም ጭምር ለማምጣት ተችሏል።

የቻይና የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በዚህ ተልዕኮ የሚመጣው የአለት ስብርባሪ ድንጋይ ጨረቃን በተሻለ መልኩ ለመረዳትና ወደፊት የሚደረጉ ጉዞዎችን ቀላል ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።

ቻይና ከጨረቃ ላይ የአለት ስብርባሪ ድንጋዮችን ለማምጣት እንደምትፈልግ የገለጸቸው በአውሮፓውያኑ 2013 ላይ ነበር።